ኢንቨርቲንግ ዘ ፒራሚድ | ክፍል አስር – ክፍል አምስት

ጆናታን ዊልሰን Inverting the Pyramid: The History of Football Tactics የአማርኛ ትርጉም ምዕራፍ አስር ላይ ደርሷል። ይህ ምእራፍ በእግርኳስ ታክቲክ ታሪክ ውስጥ ትልቅ ሥፍራ ካገኙ የአጨዋወት አቀራረቦች አንዱ የሆነው ካቴናቺዮን ከስር መሠረቱ ጀምሮ ያለፈባቸውን መንገዶች ይመለከታል። የዛሬው መሰናዶም ካለፈው ሳምንት የቀጠለ ነው።


በ1960ዎቹ የኔሪዮ ሮኮ ቡድን ምንም ያህል በተቀናቃኞቹ ላይ ብልጫ ቢያሳይም ከጎረቤት ባላንጣው አኳያ ሲታይ ግን ለንጽጽር የሚቀርብ የበላይነት አልነበረውም፡፡ “ላ ግራንዴ ኢንተር” የተሰኘውና በሄሌኒዮ ሄሬራ የተመራው ቡድን እጅጉን ስል፣ ስኬታማና አይምሬ ነበር፡፡ ይህ ቡድን የካቴናቺዮ ዋነኛ ተግባሪ እንደነበር አሳይቷል፤ በእግርኳስ አግባብ እንዳልሆነ የሚታሰብ አጨዋወትን በመከተል ዝነኛ መሆንም ችሏል፡፡ በእርግጥ ይህ ለክለቡ ሊሰጥ የሚገባውን ክብር አይቀንስም፡፡ ለኢንተር የዘመኑ እግርኳሳዊ የበላይነት የተሰጠውን ክብር እንግሊዛውያኑ እንዲሁ በቀላሉ የሚቀበሉት አልሆነም፤ እንዲያውም ከፍተኛ ጉርምርምታ ያስከተለ ሆኖ አልፏል፡፡ በ1945 ገደማ ፈረንሳይ ውስጥ በተካሄደ ጨዋታ ከካርል ራፕን ተጽዕኖ ውጪ ሆኖ የጠራጊ-ተከላካይ (Sweeper) ሚናን በማስተዋወቅ ረገድ ሄሬራ ራሱ ፈር ቀዳጅ እንደሆነ ለመናገር ይሞክራል፡፡ እርሱ በጨዋታው በW-M (3-2-2-3) ፎርሜሽን በቀኝ መስመር ተከላካይነት (Left-Back) እንደተጫወተ ያስታውሳል፡፡ እስከ ጨዋታው ሶስት-አራተኛ ክፍለ ጊዜ ድረስ የሄሬራ ቡድን 1-0 መምራት ችሎ ነበር፡፡ ነገርግን የቡድኑ አባላት በከፍተኛ ጫና ውስጥ መሆናቸውን ሲረዳ ሄሬራ የግራ መስመር አማካዩ (Left-Half) ወደኋላ ተመልሶ የእርሱን ቦታ (Position) እንዲይዝ አዘዘው፤ ከዚያ ሄሬራ ከመሃል-ተከላካይ አማካዩ (Centre-Half) ጀርባ ሆኖ ለተከላካዮቹ ሽፈን መስጠት ጀመረ፡፡

 ” እኔ ተጫዋች እያለሁ የማስበው እንደዚያ ስለመከላከል ነበር፡፡ በዚያ ሲስተም ደግሞ አሸንፈናል፤ ልክ አሰልጣኝ ስሆን ያን አጨዋወት ለመተግበር ወጠንኩ፡፡” ይላል ሄሬራ፡፡ እንግዲህ ነገሩ እውነት ይሁን-አይሁን ተጨባጭ ማስረጃ ማግኘት አይቻልም፤ መቼም ሄሬራ የራሱን አፈታሪክ አይቀባባውም ተብሎ አይታሰብም፡፡ ከዚህ አከራካሪ ጉዳይ ጀርባ ያለውአብይ እውነት አርጀንቲናዊው አሰልጣኝ የካቴናቺዮ አጨዋወት ሥልት የጡት አባት መሆኑ እና በዚሁ የጨዋታ ሲስተም ሁለት የአውሮፓ ክለቦች ዋንጫ ማሸነፉ መቻሉ ነው፡፡ አጠር-ወፈር ባለ አካላዊ ቁመናው እንዲሁም ለወይን ባለው ፍቅር የሚታወቀው ሮኮ በካቴናቺዮ የአጨዋወት ሥርዓት ላይ እምብዛም የራሱ የሆነና የተለየ ልዩነት ሲፈጥር አልታየም፡፡ ዝነኛዋ ጣልያናዊት ጋዜጠኛ ካሚላ ካዴርና እንዳስቀመጠችው ቀጠን ያለ ሰውነት፣ ዘንካታ ቁመት እና የደማቅ ጥቁር ጸጉር ባለቤት የነበረው ሄሬራ ደግሞ በጠንካራ የስነ ምግባር አስከባሪነቱ ይታወቃል፡፡

ትክክለኛ ጊዜው መቼ እንደሆነ ባይታወቅም ሄሬራ የተወለደው በቦነስ አይረስ ነው፡፡ አባቱ ስፔናዊ ስደተኛ እንደነበር ይነገራል፤ የልጁን የትውልድ ዘመን በተገቢው ጊዜ ባለማስመዝገቡ ከሚደርስበት ቅጣት ለማምለጥ ሲልም የሄሬራን እድሜ ለማጭበርበር ተገዷል፡፡ ቆይቶ የሄሌኒዮ ሄሬራ ሚስት ባሏ የልደት ካርዱ ላይ የነበረውን የውልደት ዘመን ከ1910 ወደ 1916 እንደቀየረው አሳውቃለች፡፡ ሄሬራ ግለ-ታሪኩ ላይ አባቱ በአናጢነት ሙያ የተሰማሩ እንደነበሩ ገልጿል፡፡ የሥርዓት-አልበኛ ነጋዴዎች ህብረት አባልም ነበር፡፡ እናቱ ዘመናዊ ትምህርት ያልተማረችና የጽዳት ሰራተኛ ብትሆንም አስገራሚ ብልሃት የተላበሰች እንደነበረች ይናገራል፡፡

ሄሬራ የአራት ዓመት ህጻን ሳለ ቤተሰቦቹ የመንግስት ባለስልጣናቱን ሽሽት ወደ ሞሮኮ ኮበለሉ፡፡ በሰሜን አፍሪካዊቷ አገር ህጻኑ ሄሬራ በተላላፊ የጉሮሮ በሽታ(Diphtheria) ተጠቅቶ ከሞት ለጥቂት ተረፈ፡፡ ከዘመናት በኋላ ደግሞ የባርሴሎናን አሰልጣኝነት መንበር ለመረከብ ጥቂት ሲቀረው የአውሮፕላን አደጋ ገጥሞት በድጋሚ ከአሰቃቂ ሞት አመለጠ፡፡ እነዚህ ከሞት የመትረፍ አጋጣሚዎች ሄሬራ ራሱን የተለየ ፍጡር አድርጎ እንዲያይ አድርጎታል፤ ለጥቃቅን ነገሮችም ጥንቁቅ እንዲሆን ገፋፍተውታል፤ እርሱ “የተመረጠው ሰው” እንደሆነ እንዲቀበልም የልብ ልብ ሰጥቶታል፤ አላማ ያነገበ መሪ መሆኑንም አሳምኖታል፡፡ እነዚህ ሁሉ ውስጣዊ ባህርያቱ የመናኝ ህይወት በመሰለ የአኗኗር ዘይቤው ታይተዋል፡፡ በኢንተር የልምምድ ማዕከል በሚገኘው መልበሻ ክፍሉ ግድግዳ ላይ ይታይ የነበረው ብቸኛ ምስል ክርስቶስ የተሰቀለበት መስቀል ነበሬ፡፡ በልጅነቱ ከገጠመው የመተንፈሻ ቧንቧዎች መታወክ ችግር ሲያገግም በአስራዎቹ እድሜው አካላዊ ጥንካሬውን በማዳበር ግርማ-ሞገሳም የመስመር ተጫዋች (Full-Back) ለመሆን በቃ፡፡ ” ገና የአስራ አራትና አስራ አምስት ዓመት ታዳጊ ሳለሁ ከአረቦች፣ ከአይሁዶች፣ ከፈረንሳዮችና ስፔናውያን ጋር መጫወት አዘወትር ነበር፡፡ ይህ እንግዲህ የህይወት ት/ቤት ሆነ ማለት ነው፡፡” ሲል ከመሞቱ አምስት ዓመታት በፊት በ1997 ለሳይመን ኩፐር በሰጠው ቃለ-መጠይቅ ነግሮታል፡፡

መደበኛ የእግርኳስ ተጫዋችነት ህይወቱን የጀመረው ሬሲንግ ካሳብላንካ በተባለው ክለብ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ግለ-ታሪኩ ላይ እንዳሰፈረው
” በድሃ ሃገራት በተሰማሩ እና የንስር ዓይን ባላቸው መልማዮች” አማካይነት ተገምግሞ በፍጥነት ወደ ፓሪስ የመጓዝ ዕድል አገኘ፡፡ በፈረንሳይ ለ<ሬድ ስታር-93> እና ሬሲንግ ለተባሉ ክለቦች መጫወት ቻለ፡፡ ለሃገሪቱ ብሄራዊ ቡድንም በመስመር ተከላካይነት ሁለት ጊዜ ለመመረጥ በቃ፡፡ የእግርኳስ ህይወቱ መካከለኛ ደረጃ የሚሰጠው ተጫዋች ከመሆን የላቀ ተስፋ ባያሳይም ከባድ የጉልበት ጉዳት ካጋጠመው በኋላ በሃያ አምስት ዓመት ዕድሜው ከሚወደው እግርኳስ ሊለያይ ተገዷል፡፡ ዋነኛ እጣ ፈንታው በአመዛኙ ወዴት እንደሚያመራው ጠንቅቆ ቢረዳም የወጣትነት ጊዜውን ወደኋላ መለስ ብሎ ሲያይ አስቸጋሪዎቹን ሁኔታዎች እንኳ በአዎንታዊ ጎኑ ለመመልከት ይሞክራል፡፡ ” ተጫዋች ሳለሁ ትሁት የነበርኩ ይመስለኛል፡፡ የጨዋታ ዘመናቸውን ኮከብ ሆነው ያሳለፉ ተጫዋቾች ወደ አሰልጣኝነቱ ዓለም ሲቀላቀሉ ከፍተኛ ድፍረትና የራስ መተማመን ይዘው ይገባሉ፡፡ ሆኖም ተፈጥሮ የቸረቻቸውን ክህሎት ተጠቅመው በቀላሉ ሲሰሩ የከረሙትን ተዓምር በምን መልኩ ማስተማር እንዳለባቸው አያውቁትም፡፡ የኔ ልህቀት የተገኘው ከእነርሱ ድክመት አንጻር ሳይሆን አይቀርም፤ እነርሱ ጋር የሚስተዋለው ችግር እኔ ጋር አልነበረም፡፡” ይላል ሄሬራ፡፡

ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወደ ማብቃቱ ሲቃረብ
<ፐሾ> የተባለን አማተር ክለብ ለማሰልጠን ተስማማ፡፡ በዚህ ቡድን እድገት ላይ አመርቂ ጅምር ካሳየ በኋላ <ስታድ ፍራንሳስ> ወደ ተሰኘ ሌላ ክለብ አመራ፡፡ በተጓዳኝ በትርፍ-ጊዜው በጋስተን ባረው በሚመራው ብሄራዊ ቡድን ረዳት አሰልጣኝ ሆኖም ይሰራ ጀመር፡፡ “ለ-ሶርሲዬ” ወይም “ጠንቋዩ” የሚለውን ቅጽል ስም ያገኘውም ያኔ ሲሆን ኋላ ላይ በጣልያንኛው “ኤል ማጎ” ተብሎ ተተርጉሟል፡፡ ሄሬራ ግን መጠሪያው ስኬቶቹን እንደሚያንኳስስበት ስለሚያስብ አይወደውም፡፡ ” ከመጠንቆል ጋር የተያያዘው ቃል እግርኳስን አይመጥነውም፡፡ ሁነኛዎቹ የእግርኳስ ገላጭ ቃላት ጥንካሬ (Strength) እና ጥልቅ ስሜት (Passion) ናቸው፡፡ በህይወቴ የተሰጠኝ ትልቁ ሙገሳ በቀን ለሰላሳ ሰዓታት እንደምሰራ የተነገረልኝ ነው፡፡” ይላል ሄሬራ፡፡ አርጀንቲናዊው አሰልጣኝ እድል (Luck) በእግርኳስ ውስጥ የሚሰጠው ቦታም እንዲሁ አይዋጥለትም፡፡
” እኔ እድለኛ (Fortunate) ስለመሆን መጠየቅ አልወድም፡፡ ገድ (Good Luck) በሚባል ነገር አላምንም፡፡ አንድ ሰው በሃያ ዓመታት ውስጥ በርካታ ድሎችን መጎናጸፍ መቻሉ እድለኛነቱን ያሳያል?” በማለት ይጠይቃል-አስራ ስድስት ያህል ትልልቅ ዋንጫዎችን ያሸነፈው ሄሬራ፡፡ “እንደ ትምክህት አትዩብኝና እኔ በዓለም ላይ ካሉ አሰልጣኞች በሙሉ የላቀ ስኬት አግኝቻለሁ፡፡ የእኔ ገድል እኮ እንኳን ተደርጎ- ተሞክሮም የማይታወቅ ነው፡፡” ሲል በአሰልጣኝነት ዘመኑ ማብቂያ ላይ በነበሩት ጊዜያት ተናግሯል፡፡ ለሄሌኒዮ ሄሬራ ሁሉም ነገር የሚቻል ስለነበር ማንኛውም ነገር በተሻለ ደረጃ ሊሰራ እንደሚገባ ያምናል፡፡ ከዚህ መመዘኛ አንጻር እርሱ ፈር-ቀዳጁ አሰልጣኝ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ቤላ ጉትማን የኸርበርት ቻፕማንን የአሰልጣኝነት ሙያ ከፍታ ቢያስቀጥልም በግልጽ የአሰልጣኞችን ሚና የተለየ ክብር እንዲሰጠው ያደረገው ግን ሄሌኒዮ ሄሬራ ነው፡፡ አሰልጣኞች ለእግርኳሱ ትልቅ እሴት መሆናቸውን ያሳየው እና ክብራቸው ከፍ እንዲል ያስቻለውም ሄሬራ ነበር፡፡ ” እኔ የአሰልጣኝነት ሙያን ስጀምር አሰልጣኞች የቡድናቸውን ቦርሳ ይሸከሙ ነበር፡፡ እኔ መጥቼ አሰልጣኞቹ ተገቢው ቦታቸው ላይ እንዲቀመጥኩ አስቻልኩ፤ የሚገባቸውን ክብር አሰጠሁ፤ ሊያገኙ የሚገባውን ክፍያ እንዲያገኙ አደረግሁ፡፡” ሲልም ለሙያተኞቹ ያስገኘውን አበርክቶ ይዘረዝራል፡፡

ሄሬራ የእግርኳስ ታክቲክ ልሂቅ ብቻ አልነበረም፤
ምሉዕ እና እንከን የለሽ ሥራ በመከወን የሚረካ ሰው (Perfectionist) ነበር፡፡ በሥራው በሁሉም የቡድኑ ጉዳዮች ጣልቃ እየገባ የመሳተፍ ልማድ አሳይቷል፡፡ የተጫዋቾቹን አመጋገብ ይቆጣጠራል፤ ተጫዋቾች ከቀጣዩ ጨዋታ በፊት ባለው ምሽት በልምምድ ማዕከላቸው እንዲሰባሰቡ የሚያዘውን “ሪትሮ” የተባለ ሥርዓት እንዲለመድ አድርጓል፤ የስፖርት ሥነ-ልቦና አስፈላጊነትን ግንዛቤ በማስፈንና ተግባራዊ በማድረግም ረገድ ግንባር ቀደም መሆን ችሏል፡፡ ዘወትር ማለዳ ከአንድ ሰዓት በፊት ይነሳና መደበኛ የዮጋ ልምምዱን ያከናውናል-‘ጠንካራ ነኝ!’፤ ‘የተረጋጋሁ ነኝ!’፤ ‘አንዳች የሚያስፈራኝ ነገር የለም!’፤ ‘መልከመልካም ነኝ!’ የሚሉ ንግግሮችን ለራሱ በተደጋጋሚ ያነበንባል፡፡ በመልበሻ ክፍሉ ግድግዳዎች ላይ የማነቃቂያ መልዕክቶች ያሰፈረባቸውን ወረቀቶች ይለጥፋል፡፡ “መፋለም ወይስ መጫወት? “መፋለም እና መጫወት!” ይላል አንደኛው፡፡ ሌላኛው ደግሞ ” ለራሱ የሚጫወት ለተጋጣሚ ይጫወታል፤ ለቡድኑ የሚጫወት ግን ለራሱ ይጫወታል፡፡” ይላል፡፡ ሄሬራ የቡድኑ ተጫዋቾች በቀን እስከ አስራ ሁለት ሰዓት የሚደርስ ጊዜ በእንቅልፍ እንዲያሳልፉ ያበረታታል፡፡ እርሱ ራሱ አልፎአልፎ ካልሆነ በቀር ከምሽቱ ሶስት ሰዓት በፊት ወደ መኝታው ያመራል፡፡ እንዲያውም ብሬራ አሰልጣኙን ” አስቂኝ ተዋናይ እና ብልህ፣ ተራ ሰው እና መናኝ፣ የዕውቀት ጥማት ያለበት እና መልካም አባት፣ ገዢ እና አማኝ፣ ትምክህተኛ እና ብቁ፣ ራስን የማግነን አባዜ የተጸናወተው እና የጤና እክል ያለበት፣…..” ብሎ የባህርያት ተቃርኖውን ይዘረዝራል፡፡

በ1949 የስታደ ፍራንሲስ ክለብ ፕሬዘዳንት ክለቡን ሲሸጡት ሄሬራ ወደ ስፔይን ሄደ፡፡ በሪያል ቫያዶሊድ ጥቂት ጊዜያት ካሳለፈ በኋላ የአትሌቲኮ ማድሪድ አሰልጣኝ ሆኖ ተሾመ፡፡ በአትሌቲኮ ሁለት የሊግ ድሎችን ማሸነፍ ቻለ፡፡ ከዚያም በማላጋ፣ ዲፖርቲቮ ላ-ካሩኛ፣ ሲቪያ እና በፖርቹጋሉ ቤለኔንሰስ የተለያዩ ቆይታዎችን ካደረገ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የአውሮፓ ድል ወደ ተጎናጸፈበት ታላቁ ባርሴሎና አመራ፡፡ በእርግጥ ከእርሱ በፊት ቡድኑን ሲመራ የነበረው ዶምኔክ ባልማኛ ነበር ባርሴሎናን ለ<ፌይርስ ካፕ> ፍጻሜ ያደረሰው፡፡ ምንም እንኳ በመጀመሪያው ፍልሚያ የስፔኑ ክለብ በስታምፎርብሪጅ ከለንደን ምርጥ-አስራ አንድ ጋር ብልጫ አሳይቶ 2-2 የተለያየ ቢሆንም ደካማ የነበረው የሊግ አጀማመሩ ብዙ መሰናክሎች ደቀነበት፡፡ ዶምኔክ ባልማኛ ተሰናብቶ ሄሌኒዮ ሄሬራ ክለቡን ተረከበ፤ በፍጻሜው ቀሪ ጨዋታ የ6-0 ድል አስገኝቶ ዋንጫውን ወሰደ፡፡

ሄሬራ በባርሴሎና ከቀድሞው የክለቡ አሰልጣኝ
የተረከበው ቡድን እጅጉን ባለ ክህሎት ተጫዋቾች የተሰባሰቡበት እንደነበር ምስክርነቱን ይሰጣል፡፡
” ክለቡ ካሉት ተጫዋቾች ጥራት አንጻር ባርሴሎና በተሳተፈበት የትኛውም ውድድር ቡድኑን አሸናፊ እንዲሆን ማስቻል ማንም ሰው ሊያደርገው የሚችለው ነገር ነው፡፡” ይላል ሄሬራ፡፡ ” እስካሁን ድረስ ሪያል ማድሪድ በሃገር ውስጥና በአህጉር ደረጃ ያሳካቸው ድሎች ለባርሴሎና ስጋት ሆነውበታል፡፡” ብሎ የካታላኑን ክለብ ደካማ ጎን ይተነትናል፡፡ ስለዚህ የቡድኑን ስነ-ልቦናዊ ደረጃ ለማሻሻል እና የራስ መተማመን ከፍ ለማድረግ መስራት እንዳለበት አሰበ፡፡ ታዲያ ይህን ለማድረግ አነሳሽ ወይም አነቃቂ መፈክሮች ብቻ በቂ አልነበሩም፤ ስለዚህም ከባዕድ ሃገር የወረሳቸውን ተከታታይ መንፈሳዊ ሥርዓቶች ተጫዋቾቹ እንዲከተሉ ያደርግ ጀመር፡፡ ” በርካታ አሰልጣኞች በቡድን ውስጥ የሚኖራቸው ሚና ውስን ነው፡፡ ተጫዋቾቻቸው ወደ ሜዳ ሊገቡ ሲሉ ትከሻቸውን ቸብ-ቸብ በማድረግ ለማበረታታት ይሞክራሉ ካለዚያም የተለመደ የአርበኝነት ስሜት ቀስቃሽ ንግግሮች ያደርጋሉ፡፡ እነዚህ ድርጊቶች ምናልባት በተናጠል የተጫዋቾችን ወኔ ከፍ ለማድረግ ያስችሉ ካልሆነ በቀር የአንድን ቡድን የመፋለም ተነሳሽነት ያን ያህል የሚጨምሩ አይመስለኝም፡፡” ይላል ሄሬራ፡፡

በባርሴሎና ተጫዋቾች ከጨዋታ በፊት ከተለያዩ
ዕፅዋቶች በሚቀመም የሻይ ቅጠል የተሰራ ሻይ እንዲጠጡ ይደረጋል፡፡ ሻዩ በደቡብ አሜሪካ ወይም አረብ ሃገራት የተለመደና የተለያዩ ህመሞች ፈዋሽ መሆኑ ይነገርለታል፡፡ አሰልጣኙ ሌላም መደበኛ ልማድ አለው፡፡  ተጫዋቾቹ ወደ ሜዳ ከመግባታቸው በፊት አንድ ቦታ ላይ ይሰበስባቸውና ክብ ሰርተው እንዲቆሙ ያደርጋል፤  የእያንዳንዱን ተጫዋች አይን አተኩሮ እያየ ‘ እንዴት ነው ይህን ፍልሚያ የምንወጣው? ጨዋታውን የምናሸንፈው ለምንድን ነው?…..’ የሚሉ ጥያቄዎች እየሰነዘረ ኳሱን ወደ ግንባራቸው በየተራ ይወረውርና መልሳቸውን ይቀበላል፡፡ ሄሬራ ክብ ሰርተው የቆሙ ተጫዋቾችን እየዞረ ሲቃኝ እጆቻቸው የቡድን አጋሮቻቸው ትከሻ ላይ ማረፉንና በፍቅር መተቃቀፋቸውን ያረጋግጣል፡፡

” ተጋጣሚያችንን እንረታለን! የምናሸንፈው ደግሞ በጋራ ነው፡፡” የሚል መፈክር ያሰሙታል፡፡ የክለቡ አጥቂ የነበረው ሉዊስ ሱአሬዝ በገበታ ሰዓት ጥቂት ወይን ከፈሰሰ በቀጣይ ጨዋታው ግብ እንደሚያስቆጥር ያምናል፡፡ ሄሬራ ከወሳኝ ጨዋታዎች በፊት ቡድኑ እራት ወይም ምሳ  በሚመገብበት ሰዓት ወይን የያዘ ብርጭቆውን በማንኳኳት ጸጥታ ካሳፈነ በኋላ አጭር ንግግር ያደርጋል፡፡ ይኽን ጊዜ ሱአሬዝ ጣቶቹን በወይን የራሰ የጠረጴዛ ጨርቅ ያስነካና ጨርቁን ግንባሩንና እግሩን ይደባብስበታል፡፡

ሄሬራ ወደ ኢንተር ካመራ በኋላ መንፈሳዊ ድርጊቶቹ ይበልጡን ውስብስብ እየሆኑ ሄዱ፡፡ ጭራሽ ቀዝቃዛ የአየር ሁኔታ ክለቡ አካባቢ  ማንዣበብ በሚጀምርበት ሰዓት መሻሻል ማስፈለጉን ገላጭ ምልክት እንደሆነ ያስብ ጀመር፡፡ ማንኛውም ጨዋታ ከመጀመሩ አስቀድሞ ሄሬራ ኳሷን በእጁ ይዟት ወደ ማስጀመሪያው ስፍራ ይሄድና የሜዳው አጋማሽ ክቡ ቦታ ላይ ያስቀምጣታል፡፡ ተጫዋቾቹ በሙሉ ” እኔ ላገኛት ይገባል! እኔ ላገኛት ይገባል!” እያሉ ወደ ኳሷ ይከንፋሉ፡፡ ይህ ዕምነቱን በማስመልከት ሄሌኒዮ ሄሬራ ” ከየትኛውም ጨዋታ በፊት ኳሷን መንካት እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡” ሲል ያገልጻል፡፡ ” ተጫዋቾች በተፈጥሯቸው በጭንቀት የመርበድበድ ባህርይ ያሳያሉ፡፡ ትልቅ ግምት የሚሰጠው ጨዋታ እያካሄዱ ሊሆን ይችላል፤ በርካታ ተመልካቾች ፊት ይጫወቱም ይሆናል፤ ዋናው ግን ጨዋታው ነው፤ እግርኳስ የህይወታቸው አካል ሆኗል፡፡ ፍልሚያው ሲጠናቀቅ ሁሉም ተጫዋቾቼ እርስበ’ርስ እንዲተቃቀፉ አደርጋለሁ፡፡ መሳሳም አይደለም፥ መተቃቀፍ ብቻ! ከዚያ 

‘ሁላችንም በአንድ ጀልባ ውስጥ ሆነን እየቀዘፍን ነን፡፡’ እላቸዋለሁ፡፡ ይህንን ስላቸው ፊታቸው ላይ የአንድነት መንፈስ አነብባቸዋለሁ፤ ‘ እርስ’በርሳችሁ ተወያዩ! በደንብ ተከላከሉ፤ እስክትግባቡ ድረስ እርስ’በርሳችሁ አውሩ!’ ብዬ እነግራቸዋለሁ፡፡ (Une equipe! Une famille!)” በማለት በዝርዝር ከተጫዋቾቹ ጋር ስለሚፈጥረው ጥልቅ መስተጋብር ያስረዳል፡፡

ሄራሬ በባርሴሎና ያሳየው የአጨዋወት ሥልት አሰልጣኙ የነበረውን ትልቅ በራስ የመተማመን ከፍታ ፍንትው አድርጎ ያሳያል፡፡ ከመሃል አጥቂዎች (Centre-Forwards) ግራና ቀኝ የሚጫወቱትን የፊት መስመር ተሰላፊዎች (Inside-Forwards) ወደኋላ እንዲያፈገፍጉ አድርጎ ከመሃለኛው የሜዳ ክፍል እየተነሱ እስከ ተጋጣሚ የመከላከያ ሲሶ ድረስ በነጻነት የሚመላለሱ የመስመር አማካዮች (Wing-Halves) አደረጋቸው፡፡ እነዚህ ተጫዋቾች በመሃለኛው የሜዳ ክፍል የፈጠራ ምንጭ የሚሆኑበትን ኃላፊነት ጫነባቸው፡፡ በ1958-59  ባርሴሎናዎች በሰላሣ ጨዋታዎች ዘጠና ስድስት ግቦች አስቆጥረው በአራት ነጥቦች ልዩነት የሊጉን ዋንጫ ማንሳት ቻሉ፡፡ በቀጣዩ የ1959-60 የውድድር ዘመን ደግሞ ሰማንያ-ስድስት ግቦች አስቆጠሩና ከሪያል ማድሪድ በጎል ልዩነት በልጠው ተገኙ፡፡ ይሁን እንጂ ክለቡ በአውሮፓ ክለቦች ዋንጫ የሩብ ፍጻሜ ፍልሚያ ላይ በሪያል ማድሪድ በደርሶ-መልስ ጨዋታ 6-2 በሆነ ድምር ውጤት በመሸነፉ ሄሬራ የውድድር ዘመኑ ሳይገባደድ ለመባረር በቃ፡፡ እርሱ በሁለት የደርሶ-መልስ ጨዋታዎች መካከል ክለቡን ተረክቦ ባርሴሎና በ<ፌይር ካፕ> ለእንግሊዝ ቡድኖች  ፈተና እንዲሆን አስችሎታል፡፡ ከዚያ በኋላ ከካታላኑ ክለብ ጋር ተለያየ፡፡ ከአውሮፓ ክለቦች ዋንጫ ወድድር መሰናበት በኋላ ደጋፊዎች ሄሬራን በሚያርፍበት ሆቴል ሊተናኮሱት ሞከሩ፡፡ ከተባረረ በኋላ ደግሞ አርጀንቲናዊውን አሰልጣኝ ትከሻቸው ላይ አስቀምጠው በራምብላስ ጎዳናዎች ሲያዞሩት ዋሉ፡፡ በዚያ ዘመን ምናልባት ከቤላ ጉትማን ውጪ በአውሮፓ በተፈላጊነት ደረጃ ሄሌኒዮ ሄሬራን የሚተካከል አሰልጣኝ ማግኘት ከባድ ነበር፡፡

ይቀጥላል...


ጆናታን ዊልሰን ዝነኛ እንግሊዛዊ የስፖርት ጋዜጠኛ ሲሆን በተለያዩ ጋዜጦች፣ መጽሄቶች እና ድረገጾች ላይ ታክቲካዊና ታሪካዊ ይዘት ያላቸው የእግርኳስ ትንታኔዎችን የሚያቀርብ ጉምቱ ጸኃፊ ነው፡፡ ባለፉት አስራ ሦስት ዓመታትም አስር መፅሐፍትን ለህትመት አብቅቷል፡፡