ብሩክ አየለ የት ይገኛል?

“ዓምና በጥሩ ወቅታዊ ብቃት በነበርኩበት ጊዜ አግባብ ባልሆነ መንገድ የመሰለፍ ዕድል መነፈጌ ብዙ ነገር አበላሽቶብኛል”

በታዳጊ ቡድኖች ደረጃ ለቅዱስ ጊዮርጊስ እና ንግድ ባንክ ተጫውቷል። የዋና ቡድን እግርኳስ ሕይወቱን በባህርዳር ከተማ ጀምሮ ጥሩ ዓመታት ያሳለፈባቸው ሀዋሳ ከተማ እና ሲዳማ ቡናን ጨምሮ ለኢትዮ ኤሌክትሪክ፣ ወልዋሎ እና ደቡብ ፖሊስ ተጫውቷል።

በተለያዩ የአማካይ ቦታዎች ላይ መጫወት የሚችለው ብሩክ አየለ በስኬት ደረጃ በተይም በሀዋሳ እና ሲዳማ ቡና ያሳለፋቸው ዓመታት በልዩ ይጠቅሳል። ባለፈው የውድድር ዓመት ከደቡብ ፖሊስ ጋር ዓመቱን ካሳለፈ በኋላ ላለፉት ስድስት ወራት ከክለብ እግር ኳስ ርቆ የነበረው ይህ ተጫዋች አሁን ስላለበት እና ከእግር ኳስ የራቀበት ምክንያት አስመልክተን ያደረግነው ቆይታ እንደሚከተለው ይቀርባል።

አሁን ስላለበት ሁኔታ

ኮሮና ከመከሰቱ በፊት በግል ጠንካራ ልምምዶች እየሰራሁ ነበር፤ ከእግር ኳስም አልራቅኩም፤ በአንዳንድ ቦታዎች እጫወት ነበር። አሁን ግን ከወረርሽኙ ጋር በተያያዘ ስጋት የስፖርት እንቅስቃሴዎች ስለቆሙ ለትንሽ ጊዜ ወደ እምነት ቦታ ሄጃለው። የስፖርት እንቅስቃሴ በመቆሙ ጊዜውንም የፆም ወቅት ስለሆነ ነው የሄድኩት። በቅርቡ ደግሞ በግል ልምምዶች መስራት እጀምራለሁ። ወደዚ ከመምጣቴ በፊት ለሁለተኛ ዙር ወደ ክለብ እግር ኳስ ለመመለስ ስላሰብኩ ጠንካራ ዝግጅት እያደረግኩ ነበር በወረርሺኙ እግርኳስ ቆመ እንጂ። አሁን ግን ቅድም እንዳልኩህ በእምነት ቦታ ነው ያለሁት፤ በቅርቡ እመለሳለሁ።

ከእግር ኳሱ የራቀበት ምክንያት

ነገሩ ትንሽ ውስብስብ ነው፤ በአንዳንድ ስማቸው መግለፅ የማልፈልጋቸው ግለሰቦች ስራ ነው። አምና በደቡብ ፖሊስ ቆይታዬ በተሰለፍኩበት ጥሩ እንቅስቃሴ ነው ያሳየሁት። እንደውም በውድድር ዓመቱ አራት ለግብ የሆኑ ኳሶች አቀብያለሁ። በተሰለፍኩበት ጨዋታ ውጤታማ ነበርኩ፤ ግን በዛን ሰዓት እንደ ነበረው ጥሩ ወቅታዊ ብቃቴ የሚገባኝ የመሰለፍ ዕድል አልተሰጠኝም። በአጠቃላይ ግን ይህ ስድስት ወር ከእግር ኳስ የራቅኩበት ምክንያት በአንዳንድ ነገሮች አለመመቻቸት ነው። ግን ዓምና በጥሩ ወቅታዊ ብቃት በነበርኩበት ጊዜ አግባብ ባልሆነ መንገድ ዕድል መነፈጌ ብዙ ነገር አበላሽቶብኛል። አሁን ግን ጥሩ ዝግጅት እያደረግኩ ነው፤ በሽታው ከጠፋ ወደ እግር ኳስ እመለሳለሁ።

በእግር ኳስ ስኬታማ ጊዜዬ የሚለው

ብዙ ዓመታት በጥሩ ብቃት ተጫውቻለው ግን በሀዋሳ እና ሲዳማ ቡና ቆይታዎቹ የብቃቴ ጫፍ የነበርኩባቸው ናቸው። ሌላው በሁለቱም ቡድኖች ቆይታዎቼ በተመሳሳይ ክለቦቹ በዋንጫ ፉክክር ውስጥ ነበሩ እኔ በግልም ጥሩ ነበርኩ። በሀዋሳ ቆይታዬ አሪፍ ቡድን ነበረን። ሙልጌታ ምሕረት የመሰለ ተጫዋች ቡድናችን ውስጥ ነበር፤ እስከ መጨረሻው የዋንጫ ዕድል ነበረን። በሀዋሳ ከተማ እና ሲዳማ ቡና ጥሩ ጊዜ ነበረኝ ብዬ ነው የማስበው። ከዛ በኃላም በኢትዮ ኤሌክትሪክ ጥሩ ዓመት አሳልፌያለው። ዓምና በደቡብ ፖሊስም አሪፍ ጊዜ ነበረኝ።

ብሩክ በቀጣይ የት እንጠብቀው

ቅድም እንዳልኩህ በግል ጠንካራ ልምምድ እየሰራሁ ነው። ቀጣይ ዓላማዬ በቀጣይም በትላልቅ ቡድኖች መጫወት ነው አቅሙም አለኝ።

በመጨረሻ …

በቅድምያ እግዚአብሔር አምላክ ከዛ ቀጥሎ ደግሞ ቤተሰቦቼ ፣ ጓደኞቼን ፣ በተለያዩ ክለቦች አብረውኝ የነበሩ አሰልጣኞች እና ተጫዋቾች ማመስገን እፈልጋለው።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ