አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ በባህር ዳር ከተማ ለተጨማሪ ጊዜ ለመቆየት ውላቸውን አራዝመዋል።
ባለፈው ክረምት ባህር ዳር ከተማን ለማሰልጠን የተረከቡት የቀድሞው የቅዱስ ጊዮርጊስ እና ብሔራዊ ቡድን ረዳት አሰልጣኝ በጣና ሞገዶቹ ቤት መልካም የውድድር ዓመት ያሳለፉ ሲሆን ሊጉ በኮቪድ-19 ምክንያት እስከተሰረዘበት ወቅት ድረስ በተለይ በሜዳው የማይበገር ቡድን በመስራት አራተኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ ችለው ነበር። ይህን ተከትሎም በክለቡ ለተጨማሪ ሁለት ዓመታት ለመቆየት የሚያስችላቸውን የውል ማራዘምያ በዛሬው ዕለት በተደረገ መርሐ ግብር ተፈራርመዋል።
አሰልጣኝ ፋሲል በመርሐ ግብሩ ላይ ባደረጉት ገለፃ በከተማው ያለውን የእግርኳስ መነቃቃት እና በቡድኑ ላይ የታየውን እድገት ለማስቀጠል በማሰብ ውል ማራዘማቸውን የተናገሩ ሲሆን ወደፊት ሊጉ መካሄድ ሲጀምር በተለይ ከሜዳ ውጪ የተመዘገበውን ደካማ ውጤት ለማሻሻል እንደሚሰሩ ገልፀዋል።
አሰልጣኙ የሚፈልጓቸውን አዳዲስ እና ውል የሚራዘሙላቸው ተጫዋቾችን በቀጣይ ሁለት ቀናት እንደሚያሳውቁ ሲጠበቅ ክለቡም ከቀጣይ ሳምንት ጀምሮ ወደ እንቅስቃሴ እንደሚገባ ተነግሯል።
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!
© ሶከር ኢትዮጵያ