የፕሪምየር ሊግ ኩባንያው ውሳኔ ሲገለጥ..

የኢትዮጵያ ፕሪምየር የሊግ ኩባንያ በትናንትናው ዕለት ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ ከረጅም ክርክር በኃላ ያልተጠበቀ አዲስ አቅጣጫ አስቀምጦ ወጥቷል።

በሀገራችን የተከሰተውን በኮሮና ቫይረስ ምክንያት የሊግ ውድድሮች ሙሉ ለሙሉ መሠረዛቸውን ተከትሎ በ2013 ኢትዮጵያን በአፍሪካ መድረክ የሚወክሉ ክለቦች እነማን ይሁኑ የሚለው ጉዳይ ሲያከራክር መቆየቱ ይታወሳል። ይህን ተከትሎ የፕሪምየር ሊጉ የበላይ አካል የሆነው የሊግ ኩባንያ በትናንትናው ዕለት ከጠዋቱ ሦስት ሰዓት ጀምሮ ለረጅም ሰዓት የፈጀ እና ብዙ ክርክሮች አስተናግዶ በቀጣይ ሊጉ የሚመራበትን አዲስ መመርያ በማፅደቅ ተጠናቋል።

አስቀድሞ በነበረው የውድድር መመርያ መሰረት በሀገራችን አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቢታወጅ እና ያልታሰበ ድንገተኛ ችግር ተፈጥሮ ውድድር ቢቋረጥ በምን መልኩ ውጤት ይሰጥ የሚል የተቀመጠ መመርያ (ደንብ) አልተዘጋጀም። ይህም ማለት አሸናፊ፣ ወራጅ እና በአፍሪካ መድረክ ኢትዮጵያን የሚወክሉ ቡድኖች በምን መልኩ ይሳተፉ የሚል ህግ አልተቀመጠም ማለት ነው።

በዚህ መሠረት በቀጣይ የውድድር ዘመን በሀገራችን አሁን የተፈጠረው ለምሳሌ እንደ ኮሮና ቫይረስ አልያም ሌላ ከአቅም በላይ የሆነ ችግር ከዚህ በኋላ ቢከሰት እና ውድድር (ጨዋታዎች) ቢቋረጥ በምን መልኩ እንደሚስተናገድ የሚከተለውን ውሳኔ አሳልፏል።

ውሳኔ አንድ

ውድድሩ 75% ያህል ጨዋታው ተከናውኖ ከሆነ እና ውድድሩ ቢቋረጥ ባለው ውጤት መሠረት አንደኛ ደረጃ የያዘው በካፍ ቻምፒየንስ ሊግ እንዲሳተፍ፤ ሁለተኛ ደረጃ ይዞ ያጠናቀቀው ደግሞ የካፍ ኮፌዴሬሽን ዋንጫ እንዲካፈል እንዲሁም በወራጅ ላይ የሚገኙ ሦስት ቡድኖች በውጤታቸው መሠረት እንዲወርዱ እና በምትካቸው ከከፍተኛ ሊግ አዳጊ ቡድን እንዲኖር በመመርያው ተካቷል።

ውሳኔ ሁለት

ምን አልባት ውድድሩ ከ65% – 70% ደረጃ ላይ ደርሶ በተለያዩ ምክንያቶች ቢቋረጥና ውድድሩን በዛው ዓመት ለመቀጠል አስቻይ ሁኔታዎች ከሌሉ ምን መደረግ አለበት ለሚለው ተከታዩን ውሳኔ አሳልፈዋል።

-በባለፈው ዓመት በሚጠናቀቅ ውድድር አንደኛ እና ሁለተኛ ሆነው የሚያጠናቀቁ ቡድኖች ኢትዮጵያን በአፍሪካ መድረክ እንዲወክሉ ከውሳኔ ደርሰዋል። እንዲሁም በዚህ መመርያ መሠረት አሸናፊ፣ ወራጅ እና አዳጊ ቡድን የማይኖር መሆኑን በውሳኔያቸው አስቀምጠዋል።

በዚህ መሠረት በ2012 የውድድር ዘመን (የወቅቱ የተዘረዘው ውድድር ማለት ነው) 56% ላይ የተቋረጠ በመሆኑ እንዲሁም አስቀድሞ አጋዥ የሆነ በመመርያ የተደገፈ ደንብ ባለመኖሩ የሊግ ኩባንያው አስቀድሞ የወሰነው ኢትዮጵያን በ2021 በአፍሪካ መድረክ የሚወክላት ምንም አይነት ቡድን እንደማይኖር እና ወራጅም አዳጊም ቡድን እንደማይኖር ወስነው ወጥተዋል።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ