የጣና ሞገዶቹ የተጫዋቾቻቸውን ውል ማደስ ጀምረዋል

ቡድኑን በማጠናከር ረገድ እስካሁን ምንም እንቅስቃሴ ያላደረጉት ባህር ዳር ከተማዎች የነባር ተጫዋቾቻቸውን ውል በማደስ ወደ ሥራ ገብተዋል።

ከአንድ ሳምንት በፊት የአሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝን ውል ያደሱት ባህር ዳር ከተማዎች አሁን ደሞ ፊታቸውን ወደ ተጫዋቾች በማዞር ውል እያደሱ ይገኛሉ። በዚህም የመሃል ሜዳ ተጫዋቻቸው ፍቅረሚካኤል አለሙን እና የመስመር ተጫዋቻቸው ዜናው ፈረደን ውል ለተጨማሪ ሁለት ዓመታት አድሰዋል።

ቡድኑን በአምበልነት እያገለገለ የሚገኘው ፍቅረሚካኤል በተለይ በአይደክሜ ባህሪው ቡድኑን ሲያገለግል ቆይቷል። ከምንም በላይ በማጥቃቱም ሆነ በመከላከሉ ጥሩ ተሳትፎ የሚያበረክተው ተጫዋቹ ውሉን ማደሱ ለፋሲል ተካልኝ እና ለቡድኑ ደጋፊዎች መልካም ዜና ነው።

በባህር ዳር ከተማ ውልደቱን ያደረገው ዜናው ፈረደ ሁለተኛው ውሉን ያደሰ ተጫዋች ነው። ፍጥነቱን ተጠቅሞ በሚያደርጋቸው የመስመር ላይ እንቅስቃሴዎች የሚታወቀው ዜናው በአንፃራዊነት በዘንድሮ የውድድር ዓመት ራሱን ከጉዳት ጠብቆ ግልጋሎት ሲሰጥ ቆይቷል። አሁን ደግሞ ግርማ ዲሳሳን ላጣው ቡድን የዜናው መፈረም በመስመር ላይ ቡድኑ አማራጭ እንዳያጣ ያደርገዋል።

አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ባቀረቡት ዝርዝር መነሻነት የነባር ተጨዋቾቻቸውን ውል ለማደስ ንግግር እያደረጉ የሚገኙት ባህር ዳሮች ውል የማደስ ስራቸውን ካገባደዱ በኋላ አዲስ ተጫዋቾችን ወደ ክለቡ ለማምጣት እንዳሰቡ ተሰምቷል።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ