ወልቂጤ ከተማ የአምስት ተጫዋቾቹን ውል አድሷል

ዛሬ አንድ ተጫዋች በእጁ ያስገባው ወልቂጤ ከተማ የአምስት ነባር ተጫዋቾቹን ውል ለማደስ ከስምምነት ደርሷል።

በተከላካይ ሥፍራ የሚጫወተው ቶማስ ስምረቱ ካደሱት ተጫዋቾች አንዱ ነው። በሱልልታ ከተማ፣ ወላይታ ድቻ እና ኢትዮጵያ ቡና የተጫወተውና በተሰረዘው የውድድር ዓመት ወደ ወልቂጤ ያመራው ቶማስ ለተጨማሪ ሁለት ዓመት በክለቡ ለመጫወት ተስማምቷል፡፡

ሁለተኛው ውሉን በክለቡ ያራዘመው አማካዩ ኤፍሬም ዘካርያስ ነው። የቀድሞው የኢትዮጵያ ቡና፣ ሀዋሳ ከተማ እና አዳማ ከተማ አማካይ በተሰረዘው የውድድር ዓመት በወልቂጤ ጥሩ ጊዜ ያሳለፈ ሲሆን በተመሳሳይ ለሁለት ዓመታት ውሉን አድሷል።

በቀኝ መስመር ተከላካይ ቦታ ላይ ለቡድኑ ጥሩ ግልጋሎት የሰጠው ይበልጣል ሽባባው ሌላው ውል ያራዘመ ተጫዋች ሲሆን ወልቂጤ በከፍተኛ ሊግ ወደ ፕሪምየር ሊግ ሲያድግ ትልቅ አስተዋፀኦ የነበረው መሐመድ ሻፊ እንዲሁም በተክለ ሰውነቱ አነስ ብሎ በአስገራሚ ክህሎቱ የሚታወቀውና ወልቂጤ ወደ ፕሪምየር ሊግ እንዲያድግ ትልቅ አስተዋፅኦ ያደረገው ወጣቱ አብዱልከሪም ወርቁ ውላቸውን በሁለት ዓመታት ያራዘሙ ተጫዋቾች ሆነዋል።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ