ቅዱስ ጊዮርጊስ ኢትዮጵያዊ አሰልጣኝ ይሾም ይሆን?

ያለፉትን አስራ ስድስት ዓመታት ከውጭ ሀገር በሚመጡ የተለያየ ዜግነት ባላቸው አሰልጣኞች ሲመሩ የቆዩት ፈረሰኞቹ ፊታቸውን ወደ ሀገር ውስጥ አሰልጣኝ ያዞሩ ይሆን?

የሊጉ የበርካታ ሪከርድ ባለቤት የሆኑት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ከለመዱት የፕሪምየር ሊግ ዋንጫ ከራቁ የዘንድሮው በኮሮና ቫይረስ ወረርሺኝ ምክንያት የተሰረዘውን ውድድር ጨምሮ ተከታታይ ሦስት ዓመታት አስቆጥረዋል። ከሀገር ውስጥ ዋንጫ ይልቅ በአፍሪካ መድረክ ስኬታማ በመሆን ረጅም ርቀት የሚጓዝ ጠንካራ ቡድን ለመስራት በማሰብ ያለፉትን አስራ ስድስት ዓመታት የሆላንድ፣ ሰርቢያ፣ ቦስኒያ፣ ጣሊያን፣ ጀርመን፣ ብራዚል፣ ፖርቱጋል እና እንግሊዝ ዜግነት ያላቸውን አሰልጣኞች በማስመጣት ጥረት ቢያደርጉም ክለቡ ያለመውን ግብ ማሳካት ሳይችሉ ከቀሩ ዓመታት አስቆጥረዋል።

ከ2012 መግቢያ ጀምሮ የሀገር ውስጥ አሰልጣኝ ለመቅጠር ፊታቸውን መለስ ያደረጉት ፈረሰኞቹ ከአሰልጣኝ ሠውነት ቢሻው፣ አብርሀም መብራቱ እና ውበቱ አባተ ጋር ስማቸው በተደጋጋሚ ሲነሳ እንደቆየ ይታወቃል። በተለይ ከአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ጋር የነበረው ሂደት ለመጠናቀቅ ተቃርቦ የነበረ ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች ሳይሳካ እንደቀረም ይታወሳል። ዳግመኛ አሁንም የሀገር ውስጥ አሰልጣኝ ለመቅጠር ከፍተኛ ፍላጎት እያሳዩ የሚገኙት የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ የበላይ ኃላፊዎች በቅርቡ የዝውውር ሒደቱ እንደተጠናቀቀ ይፋ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ቅዱስ ጊዮርጊስን ለማሰልጠን አሁንም አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ስሙ ተያይዞ በተደጋጋሚ እየተጠራ ሲገኝ የክለቡ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ አብነት ገብረ መስቀል ነገ ምሽት በሚኖረው “ምንግዜም ጊዮርጊስ የሬዲዮ ፕሮግራም” ላይ በመቅረብ የአሰልጣኝ ቅጥር ሁኔታ ላይ ፍንጭ ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ