ጊዜው እየሄደ ቢሆንም ምላሽ ያላገኘው የብሔራዊ ቡድኑ ጉዳይ

ለ2021 የሴቶች ከ20 ዓመት በታች የዓለም ዋንጫ የማጣርያ ጨዋታዎች ከተቋረጡበት ይቀጥላል በማለት ካፍ ቢያሳውቅም በኢትዮጵያ በኩል እስካሁን ምላሽ አላገኘም።

በ2020 ሊደረግ ታስቦ የነበረው የዓለም ዋንጫው ጥር 2021 ላይ በኮስታሪካ እና ፓናማ አዘጋጅነት እንደሚካሄድ የሚጠበቅ ሲሆን በቅድመ ማጣርያ የቡሩንዲ አቻዋን 7-1 በሆነ ድምር ውጤት አሸንፎ ወደ አንደኛ ዙር ያለፈው ከ20 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን በቀጣይ ዙር ከዚምባብዌ ጋር ግንቦት ወር ላይ ለመጫወት መርሐ ግብር ቢወጣለትም በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ላልተወሰነ ጊዜ መራዘሙ የሚታወስ ነው።

ካፍ ማጣርያው የሚቀጥልበትን አዲስ መርሐ ግብር የላከ ሲሆን ከነሐሴ 28-30 የመጀመርያው ጨዋታ፤ የመልሱ ጨዋታ ደግሞ ከጳጉሜ 5-መስከረም 2 እንደሚሆን ለኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ካሳወቀ አስራ አምስት ቀናት አስቆጥሯል። ሆኖም ፌዴሬሽኑ በስሩ የሚገኙ ብሔራዊ ቡድኖች አሰልጣኝን ውል እንደማያራዝም አሳውቆ የነበረ ቢሆንም ከ20 ዓመት በታች የዓለም ዋንጫ የውድድር መርሐግብርን ካፍ ማሳወቁን ተከትሎ የቡድኑ አሰልጣኝ ፍሬው ኃይለገብርኤል እና ረዳቶቹ ምናልባትም ውላቸው ሊታደስላቸው እንደሚችል ከዚህ ቀደም መዘገባችን ይታወቃል።

ምንም እንኳን ፌዴሬሽኑ በአሰልጣኞቹ የውል ማራዘም ጉዳይ ላይ የተለየ ነገር ባይኖረውም ጨዋታው የሚደረግበት ጊዜ አንድ ወር እየቀረው አምስት ወር ከሜዳ የራቁትን የብሔራዊ ቡድኑ አባላት ወደ ትክክለኛው አካል ብቃታቸው ለመመለስ የስድስት ሳምንት የዝግጅት ጊዜ እንደሚያስፈልገው እየታወቀ እስካሁን ቡድኑ ዝግጅት አለመጀመራቸው እና ፌዴሬሽኑ በዚህ ጉዳይ ላይ ዝምታ መምረጡ የብሔራዊ ቡድኑ ጨዋታን ፌዴሬሽኑ ሰረዘው ወይ? የሚል ጥያቄ አስነስቷል።

የብሔራዊ ቡድኑ ሁኔታን አስመልክቶ ምላሽ እንዲሰጡን የፌዴሬሽኑን ዋና ፀኃፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን ጠይቀናቸው ተከታዩን ሀሳብ ሰጥተውናል።

“ውድድሩን ለማድረግ የሚያስችል ፍቃድ ለማግኘት ለመንግሥት እና የሚመለከታቸው አካላት ጥያቄ ካቀረብን ረጅም ቀናት አስቆጥሯል። በትናንትናው ዕለት ምላሽ እንደሚሰጡን ቀጠሮ ቢይዙልንም ተገቢውን ምላሽ አላገኘንም። የውድድሩ ቀን እየተቃረበ መምጣቱን እንረዳለን፤ በቅርቡም ከመንግስት ምላሽ
እናገኛለን የ።” ብለዋል።

ኢትዮጵያ ዙሩን ካለፈች በሁለተኛው ዙር ጥቅምት ወር ላይ ከቦትስዋና እና ደ/አፍሪካ አሸናፊ የምትጫወት ይሆናል።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ