“ሦስት ዋንጫን ያነሱ ወርቃማ እጆች” ትውስታ ከአፈወርቅ ኪሮስ ጋር

በኢትዮጵያ እግርኳስ ከታዩ ምርጥ የግራ እግር ተጫዋቾች መካከል አንዱ የነበረው እና በሁሉም ቦታዎች ሲጫወት የምናቀው የቀድሞ የመብራት ኃይል አንበል አፈወርቅ ኪሮስ የ1993ቱ የሦስትዮሽ ዋንጫን ስኬት አስመልክቶ በትውስታ አምዳችን ያስቃኘናል።

ለአንድ ክለብ ታማኝ ሆኖ መዝለቅ በማይታሰብበት በዚህ ዘመን ለብዙዎች ምሳሌ መሆን የሚችል የመልከም ስብዕና ባለቤት የሆነው አፈወርቅ ኪሮስ ለመብራት ኃይል ለረጅም ዓመታት በታማኝነት ያገለገለ ታታሪ፣ መሪ፣ ሁለገብ እና ለቡድኑ ያለውን በመስጠት የሚታወቅ ጠንካራ ተጫዋች ነበር። አፈወርቅ ሕይወቱ ከመብራት ኃይል ጋር የተቆራኘው ገና የ11 አመት ታዳጊ ሳለ ነበር፡፡ አባቱ አቶ ኪሮስ የመብራት ኃይል ሠራተኛ የነበሩ በመሆናቸው የሠራተኛ ልጆች የሚጫወቱበት የታዳጊ ፕሮጀክት ሲቋቋም በ1978 በመብራት ኃይል ‹‹D›› ቡድን በመግባት በአንበልነት ቡድኑን ገና በታዳጊነቱ መምራት ችሏል። በዚህ ቡድን መጫወት ጀምሮ ደረጃ በደረጃ ባሳየው ከፍተኛ እድገት በ1985 ዋናውን የመብራት ኃይል ቡድን ተቀላቅሏል፡፡ ከመብራት ኃይል ጋር ብቻ በዘለቀው የ14 ዓመታት የተጫዋችነት ዘመኑ 2 የሊግ፣ 1 የኢትዮጵያ ሻምፒዮና፣ 1 የጥሎማለፍ እንዲሁም 3 የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ ከቡድኑ ጋር አንስቷል፡፡ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም ከ 1988 እስከ 1995 ድረስ ተጫውቷል፡፡

በተለይ እስካሁን ለክለቡ የሰማይ ያህል ርቆበት መድገም ያልቻለው የ1993ቱ የሦስትዮሽ ዋንጫ በመብራት ኃይል እግርኳስ ታሪክ በግንባር ቀደምትነት ተጠቃሽ ከሚሆኑ ስኬቶች ውስጥ ትልቁን ድርሻ የሚወስደው ነው። አፈወርቅ እንደ ተጫዋች ከነበረው አስተዋፅኦ በተጓዳኝ ድርብ ኃላፊነት ይዞ ቡድኑን በአንበልነት በመምራበት የሀገሪቱን ሁሉንም ዋንጫ፤ የስፖርታዊ ጨዋነት ዋንጫንም ጨምሮ ያነሳ ባለ ታሪክም ነው። ኢትዮጵያዊው ማልዲኒ እየተባለ የሚጠራው አፈወርቅ ዳግም ወደ ኃላ አስራ ዘጠኝ ዓመት በትውስታ መልሶን ያኔ የነበረውን ጊዜ አስታውሶ የተፈጠረበት ስሜት ከሚኖርበት አሜሪካ ቺካጎ ከተማ አናግረነው እንዲህ አስታውሶናል።

” ሁልጊዜም የምለው ነው። ዘጠና ሦስት ለኔ ትልቅ ቦታ የምሰጠው ዘመን ነው። በኢትዮጵያ የሚገኙ ዋንጫዎችን በጠቅላላ በአንበልነት ማንሳት ለኔ ትልቅ ክብር ነው። ከዚህ በላይ ለኔ ክብር አለ ብዬ አላስብም። ይህን ስልህ ምን ማለቴ ነው። አንድ ሰው ለአንድ ክለብ በታማኝነት ከአስራ አምስት ዓመት በላይ አገልግሎ ቡድኑ በአንበልነት እየመራ በመጨረሻም በሀገሪቷ ያሉትን ሁሉንም ዋንጫ፣ የፀባይ ዋንጫንም ጨምሮ ጠቅልሎ ማንሳት እና ወደ ቡድንህ ማስገባት ከዚህ በላይ ደስታህን ሙሉ የሚያደርግልህ ነገር ያለ አይመስለኝም። እስካሁንም ድረስ ውስጤ ያለ ነገር ነው። ሁልግዜም ይህን ነገር ወደ ኃላ ሳስብ ደስታ ይሰማኛል። ለምወደው ክለቤ በህይወቴ አንድ ነገር ሰርቻለው ብዬ አስባለው። ለዚህ ሁሉ ስኬት የቡድኑ ጥንካሬ፣ የእያንዳንዱ ልምድ ካለው ተጫዋች አንስቶ ከታች ካደጉት ተጫዋቾቹ ጨምሮ የነበራቸው አቅም፣ ህብረት ይህን ታሪክ የማይረሳውን ስኬት እንድናስመዘግብ አስችሎናል። በጊዜው በክለቡ በኩል የተደረገውን ስታስብ፣ በትልቁ ቢልቦርድ የቡድኑ ፎቶ በክበብ ውስጥ ተሰቅሎ ስታይ ምን ያህል ትልቅ ነገር እንደሆነ ታስባለህ። ባለፈው እንደ አጋጣሚ ወደ ኢትዮጵያ መጥቼ ሰዎችን ሰላም ለማለት ወደ መብራት ኃይል ክበብ ሄጄ ነበር። ገና ወደ ግቢው ስገባ በትልቁ የተሰቀለው ጊዜውን የሚያስታውስ ፖስተር ስመለከት ውስጤ የተሰማኝ ነገር ከፍተኛ ነበር። ምንም እንኳ ረጅም ጊዜ እንደመሰቀሉ ፖስተሩ በፀሀይ እና በዝናብ ፌድ ቢያደርግም። መልሰው ይቀይሩታል የሚል ነገር በጊዜው ሰምቼ ነበር። አሁን ያለውን ነገር አላውቅም ይቀይሩት አይቀይሩት። ሆኖም ግን ያንን ፎቶ ስመለከተው የተሰማኝ ስሜት ቀላል አልነበረም። የዘጠና ሦስት ድል ለእኔ ትልቅ ቦታ የምሰጠው፣ ሁሌም የማይረሳኝ ትልቁ ታሪኬ ነው”።

በቀጣይ የፊታችን ዓርብ የዚህን የዘጠናዎቹ ድንቅ ተጫዋች አፈወርቅ ኪሮስን አጠቃላይ የእግርኳስ ህይወት የሚዳስስ ፁሑፍ ይዘን እንደምንቀርብ ከወዲሁ እንጠቁማለን።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ

ያጋሩ