በታዳጊ ተጫዋቾች የስልጠና ሒደት አጠቃላይ የምልመላ ሥርዓቱ ልዩ ትኩረት የሚሻና ረዘም ያለ ጊዜ የሚፈልግ ነው፡፡ የዘርፉ ስልጠና የነገዎቹን ብቁ ተጫዋቾች የማዘጋጀት ሂደት እንደመሆኑ ምልመላ ዋነኛው የትኩረት ማዕከል ይሆናል፡፡ በታዳጊ ተጫዋቾች ምልመላ ውስጥ ተስጥዖን መቃኘት፣ መለየት እና መምረጥ ወሳኝ ተግባራት ናቸው፡፡ በሃገራችን እግርኳስ ምልመላ እምብዛም ተገቢ ቦታ የማይቸረው ገቢር እንደመሆኑ መጠን በዚህ በዛሬው አስተያየቴ ተስጥኦን ስለመለየት (Talent Scouting) ጥቂት ነገር ማንሳት ፈልጌያለሁ፡፡
እግርኳስ በጣም ተያያዥና ሰንሰለታማ በሆነ መዋቅራዊ ሂደት ውስጥ የሚያልፍ የስፖርት ዓይነት መሆኑ ይታወቃል፡፡ ዘርፉ በውስን ባለድርሻዎች ብቻ የሚዘወር ወይም በጥቂት ባለሙያዎች ብቻ የሚመራ እንዳልሆነም እሙን ነው፡፡ ስለዚህም የአንድ እጅ ጭብጨባ አጠቃላይ የሃገሪቱን እግርኳስ እንደማያሳድገው ሊታወቅ ይገባል፡፡ የተጫዋቾች ምልመላ ሥርዓታችን ላይ የተሰገሰጉትን ችግሮች ብንቀርፍ እንኳ ምንአልባት ኢምንት አዎንታዊ ተፅዕኖ እንፍጥር ይሆናል እንጂ አሁን ያለንን የእግርኳስ መልክ መለወጥ አዳጋች ይሆንብናል፡፡ በተወዳጁ ጨዋታ ዙሪያ ላያችን ላይ የተከመሩ ተግዳሮቶችን ለመቀነስ ማስተካከል ከሚገቡን ጉዳዮች አንዱ ይኸው የምልመላ ጉዳይ ነውና እዚሁ ርዕስ ላይ በመጠኑ የምሙው ይኖረኛል፡፡
ክለቦቻችን በዋናው ቡድናቸው የተፈለገውን ያህል ጠንካራ ቢሆኑ እንኳ ተሰጥዖ ያላቸውን ተጫዋቾች በብዛት የሚያገኙበት የታዳጊዎች ማሰልጠኛ ማዕከላት ሊኖራቸው ይገባል፡፡ አለበለዚያ የልፋታቸው ውጤት ዘላቂነቱ አሳሳቢ፤ ህልውናቸውም አጠያያቂ ይሆናል፡፡ በስልጠናው መስክ የአቅማችንን ያህል ለመሥራት ብንጥር ለስልጠና የሚመች መሰረተ ልማት ካላሟላን በቀጣይ የምንጋፈጠው ኢኮኖሚያዊ ፈተና በቀላሉ የምንወጣው አይሆንም፡፡ የተጫዋቾች ምልመላ ላይ ደካማ ከሆንን፣ በልምምድ ወቅት የምንገለገልባቸው መሳሪያዎች (Equipments) በበቂ ሁኔታ ካላዘጋጀን እና ተገቢ የስልጠና ጊዜ ካላገኘን ድካማችን ከንቱ ይሆናል፡፡
እንዳለመታደል ሆኖ የሃገራችን እግርኳስ ጠንካራ የሆነበት ፈርጅ የለውም፡፡ በደካማ ጎን ከምንፈርጃቸው ጉድለቶቻችን ውስጥ ደግሞ የምልመላ ሥርዓቱ አንዱና ዋነኛው ነው፡፡ በሃገራችን በርካታ የክለብ ኃላፊዎች እና አሰልጣኞች “የተተኪ ተጫዋቾች ችግር አለብን፡፡” ሲሉ ይደመጣል፡፡ በእርግጥም ተተኪ ተጫዋቾች የሉንም? ወይስ ተተኪ ተጫዋቾች ለማፍራት የዘረጋነው ሥርዓት ደካማ ነው? ተስጥዖን በተለያዩ መንገዶች መተርጎሙ እንዳለ ሆኖ በእኔ እምነት በሃገራችን ከአስራ ሶስት ዓመት በታች አያሌ ተስጥኦ ያላቸው ታዳጊዎች አሉ፡፡ ይህንን የምለው በአዲስ አበባ ብቻ ያሉ ታዳጊዎችን አይቼ ሳይሆን ወደ አንዳንድ የሃገራችን ከተሞች ለስራ በሄድኩባቸው አጋጣሚዎች የተመለከትኩት ድምዳሜዬን ስሰሚያሰጋግጥልኝ ነው፡፡ በተለይም አርባምንጭ፣ አዋሳ እና ድሬደዋ ያየዋቸው ታዳጊዎች ክህሎት እንዲሁ ሲመክን ያሳዝናል፡፡ በዘመናዊ <የታዳጊዎች ስልጠና> እና ሁነኛ የ<ምልመላ ሥርዓት> እጦታችን እንድንንገበገብ ያስገድደናል፡፡ ይኸው ችግራችን የእያንዳንዱን ታዳጊ ችሎታና እምቅ አቅም እያየሁ እንድቆጭ ያደርገኛል፡፡ እነዚህን ታዳጊዎች የላቁ ተጫዋቾች ለማድረግ የዘረጋነው አሰራርና ለነገ የሚበጀን የእድገት ዕቅድ የለም፡፡ እግርኳስ ተወዳጅነቱ እየሰፋ፣ ተቀባይነቱ እየናረ፣ እውቅናው እየናኘ፣ ተፎካካሪነቱም እያየለ ይገኛል፡፡ ክለቦች ነገ ምርጥ ሊሆኑ የሚችሉ ተጫዋቾችን ለማግኘት በዓለም ዙሪያ በሰፊው ተሰጥዖ ፍለጋ አህጉራት ተሻግረው ያስሳሉ፡፡ በአገራችን ያልተለመደ ቢሆንም እኛም ጋር መጠነኛ የክህሎት አሰሳ በየክፍለ ሃገራቱ ይደረጋል፤ አንዳንድ አሰልጣኞች ችሎታ ያላቸውን ልጆች ለመመልመል በየክልሎቹ ሲዞሩ ይታያል፡፡ ይሁን እንጂ ደረጃውን የጠበቀ የአመላመል ዘዴ የመከተል ልማድ የለንም፡፡ የአገራችን ክለቦችም በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች ያሉትን የነገ ምርጥ ተጫዋቾች ፈልጎ ለማግኘት የዘረጉት ቀጣይና ውጤታማ የምልመላ ስርዓት የላቸውም፡፡ እንደ’ኔ- እንደ’ኔ ይህን ለማድረግ ፍላጎት ያላቸውም አይመስለኝም፡፡
ተስጥኦን መለየት (Talent Scouting) በስፓርት እድገት ውስጥ ቁልፉ ጉዳይ ነው፡፡ ዓላማውም ውጤታማ ሊሆን የሚችል ተፈጥሯዊ ክህሎትና ብቃት ያለውን ተጫዋች በመመልከት ለወደፊቱ ትልቅ ደረጃ የማድረስ ውጥን ወዳለው ማዕከል መውሰድ ነው፡፡ ይህ ተግባር ተጫዋቾችን ረዘም ላለ ጊዜ ማየት፣ ከውሳኔ በፊት በተደጋጋሚ ትኩረት ሰጥቶ መመልከትን እንደሚጠይቅ ግልፅ ነው፡፡ አንድን ተጫዋች በአንድ ጨዋታ በማየት ብቻ ምን ያህል ርቀት ሊጎዝ እንደሚችል ከወዲሁ መገመት ተስጥኦን የመለየት ከባዱ ስራ ነው፡፡በማይመች ሜዳ እና በቂ ተስጥኦ የመለየት እውቀት በሌለበት የሥልጠና ሒደት ደግሞ ይህንን በአግባቡ መከወን እጅግ አዳጋች ይሆናል፡፡
በሃገራችን እግርኳስ የምልመላ ስርዓቱ ዝብርቅርቅ ያለ ይዘት አለው፡፡ ስለዚህም የተጫዋቾችን ተስጥኦ የመለየት ሥራው እጅግ ደካማ ሆኗል፡፡ የበቁ የምልመላ ባለሙያዎች የሉንም፤ ለምልመላ የሚውሉ ቋሚ የልምምድና የጨዋታ ፕሮግራሞች አይመቻቹም፤ ተጫዋቾች በምልመላ ወቅት ያሻቸውን የሚከውኑበት ምቹ ሜዳዎች አይገኙም፤ ታዳጊዎቹ ያላቸውን ተሰጥኦ ለማውጣት አበረታች ሁኔታዎች አይሟሉም፤….. በአጠቃላይ አሉታዊዎቹ ከባቢያዊ ችግሮች ተስጥዖ የመለየትን ሥራ ዝቅተኛ ደረጃ እንዲያገኝ አድርጎታል፡፡ እነዚህና ሌሎችም ክፍተቶቻችን ጊዜ ወስደን ክህሎት የማሰስ እና ችሎታን የመቃኘት ስራ እናዳንሰራ እንቅፋት ሆነውብናል፤ ልማዳዊው አሰራር ደግሞ ይበልጡን ቀፍድዶ ይዞናል፡፡ የታዳጊ ተጫዋቾችን ተስጦዖ በለጋ እድሜያቸው መለየት በእግርኳስ እጅጉን አስፈላጊ ነገር ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ እንዚህን ባለተስጥኦ ተጫዋቾች ተገቢው የስልጠና እድሜ ሳያልፍ ወደ ትክክለኛውና በአግባቡ ያላቸውን አቅም እንዲጠቀሙ ወደሚያስችላቸው ጎዳና ለማምጣት ነው፡፡ በእግርኳሳችን ይህ ጉዳይ በትልቁ ቦታ ስለማይሰጠው፣ ለዘርፉ ብቁ ባለሙያዎች ስለማይመደቡ፣ ደረጃውን በጠበቀ ሥርዓት ስለማይሰራ፣ ከሰለጠነው የእግርኳስ ዓለም የተሻለ እውቀትና ተመክሮ ለመውሰድ ዝግጁነቱ ስለሌለ፣ ጥቅሙ ውስጣችን ዘልቆ ስላልገባ እና በተለያዩ ምክንያቶች በተለይ በፕሮጀክቶችና በማሰልጣኛ ማዕከላት ለምልመላ ሒደት አስፈላጊውን ትኩረት ስንቸር አንታይም፡፡የታዳጊዎች ፕሮጀክት አሰልጣኞችም በብዙ ችግር ውስጥ ስለሚያልፉ የረጅም ጊዜ ዕቅድ በማቀድ አንድን ባለ ክህሎት ተጫዋች በአግባቡ በማሰልጠን ትልቅ ደረጃ ለማድረስ ይቸገራሉ፤ በተፈለገው የጥራት ደረጃ ለመስራትም ብዙ ማነቆዎች ወጥረው ይይዟቸዋል፡፡ በክለቦችም ቢሆን በታዳጊ ተጫዋቾች ላይ የሚያጠነጥንና የሩቁን ጊዜ የተመለከተ ትልም ስለሌለ ውጤቱ ያው እግርኳሳችንን አንዲት ስንዝር አላራመደውም፡፡ በየወቅቱ ለሚኖሩ ውድድሮች ታስቦ ብቻ ተጫዋቾችን በአሰልጣኞች አማካኝነት መምረጥ የተለመደ እና ለረጅም ጊዜ የሰነበተ አሰራር ሆኖል፡፡ አሁንም በዚያው ባህላዊ መንገድ እየተጓዝን እንገኛለን፡፡ በዚህኛው የምልመላ ዘዴ እንዳላደግን እያወቅንም ልናሻሽለው አልተጋንም፤ አዲስ የምልመላ ሥልትም አላመጣንም፡፡ ተለምዷዊው የመልመላ አካሄድ ተጫዋቾችን ለረጅም ጊዜ በመመልከት ተስጦዖቸውን እንድንለይ ያስቻለን አልነበረም፡፡ ይልቁንም በአጭር ጊዜ ውስጥ በርካታ ተጫዋቾችን በመጥራት አድካሚ እና አሰልቺ ምርጫ ሲካሄድበት ከርሟል፡፡ በዚህ ሒደት በርካታ ተጫዋቾች ለመመረጥ ሲሉ ወደ ሜዳ ስለሚመጡ ለአሰልጣኞቹ በጣም አሰልቺ ሥራ ይሆንባቸዋል፤ በዚህም የተነሳ ቁጥራቸው የበዛ ተጫዋቾች በአግባቡ የመታየት እድል ሳያገኙ ይቀራሉ፡፡ በዚህ ላይ ተጫዋቾቹ በአብዛኛው አንድ እድል ብቻ ስለሚያገኙ በምርጫው ወቅት በተለያየ ምክንያት ሥነ ልቦናዊ ጫናዎችን ለመጋፈጥ ይገደዳሉ፡፡ የድካም፣ የፍርሃት፣ ያለ መመረጥ ሥጋት፣ ጉጉት እና ጉዳት ያላቸውን ክህሎት በነጻ መንፈስ አውጥተው እንዳይጠቀሙ ማነቆ ይሆኑባቸዋል፡፡ በዚያችው አንዷ ዕድል ብቃታቸውን ማሳየት ባይችሉ መልሶ ለመታየት ተጨማሪ እድል አለማግኘታቸው ተስፋ ያስቆርጣቸዋል፡፡ በእንደዚህ ዓይነቱ ተስጥኦን የመለየት አልያም ክህሎትን የመገምገም ሂደት ዘመናት አሳለፍን-ዓመታት አስቆጠርን፤ ግን ይኸው ባለንበት ከመርገጥ ያለፈ አላተረፍንም፡፡ ይህን በመሰለውና በውስን ጊዜ ውስጥ በሚካሄደው ምርጫ ብዙ ተስጥኦ ያላቸው ታዳጊዎች በሰፈር ቀርተዋል፡፡ በየክለቦቹ የምንሰራ አሰልጣኞችም ለደካማው የምልመላ ሥርዓታችን ከተጠያቂነት አንድንም፤ ከጥቂቶቻችን በስተቀር ብዙዎቻችን ጊዜ ኖሮን እንኳ በየመንደሩ የሚገኙ የታዳጊ ማሰልጠኛ ፕሮጀክቶች ልምምዶችና ጨዋታዎችን በተከታታይ የመመልከት ልማድ አላዳበርንም፡፡ ክለቦቻችንም የራሳቸው ማሰልጠኛ ማዕከላት ስለሌላቸው ወይም ከሌሎች በግል ከሚሰሩ የማሰልጠኛ ማዕከላት ጋር ተሳስረው በእቅድ የመስራት ፍላጎት ስለማያሳዩ በምልመላው ዘርፍ ፋይዳ ያለው ነገር ማሳካት ተስኗቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት በደካማ የምልመላ ስርዓትና ስልጠና አልፈው የሚመጡ “የተወላገዱ” ተጫዋቾችን ከመያዝ ውጪ አማራጭ አጥተዋል፡፡
መቼም በታዳጊዎችም ሆነ ወጣቶች ምልመላ የሚዘረዘሩት ችግሮች ቁጥር ሥፍር እንደሌላቸው ሳይታለም የተፈታ ሐቅ ነው፡፡ “ተሰጥዖን በእውቀት መለየት!” አፅንኦት ልንሰጥው የሚገባ ጉዳይ መሆን አለበት፡፡ የአንድን ታዳጊ ተስጥዖ ለመለየት ትኩረት ልናደርግባቸው የሚገቡን ጉዳዮች ምንድን ናቸው? የሚለው ወሳኝ ጥያቄ ነው፡፡ እኔን ጨምሮ በርካታ አሰልጣኞች ታዳጊ ተጫዋቾችን ስንመለምል ትኩረታችን ኳስ እየገፋ ተከላካዮችን የሚያልፍ ተጫዋች ላይ ነው፡፡በተለምዶ “የሚያጣጥፍ” ተጫዋች ላይ ማለቴ እንደሆነ ይታወቅልኝ፡፡ ይህ እይታ ተስጥዖን የመለያ አንደኛው መንገድ ሊሆን ቢችልም በተለይም በክለብ የታዳጊዎች ምልመላ ወቅት ፍጥነት፣ ቅልጥፍና፣ ጥንካሬና የመሳሰሉት የአካል ብቃትን መመዘን የሚያስችሉ መስፈርቶች እንዲሁም ጨዋታን የማንበብ እና የመረዳት ብቃት፣ የታዳጊዎቹ አእምሯዊ አቅም፣ እይታ፣ አጠቃላይ የሥነ-ልቦና ጉዳዮች ልክ እንደ ቴክኒክ፣ ታክቲክና አካል ብቃት ሁሉ አስፈላጊ ናቸው ፡፡
የተስጥዖን ዘላቂነት ለመገመት የፊዚዮሎጂካልና የማህበራዊ ሁኔታዎችንም ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል፡፡ በዘርፉ የተደረጉ ጥናቶች ለእነዚህ ጉዳዮች ትኩረት መስጠቱ ጠቃሚ መሆኑን ያመለክታሉ፡፡ የተጫዋቹን ቁመት መገመት የትኛው ቦታ ላይ ቢጫወት ውጤታማ ሊሆን አንደሚችል ለመወሰን በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ በሃገራችን እግርኳስ ከላይ የተጠቀሱት ጉዳዮች ከፍተኛ ጥናት ተደርጎባቸው ተግባር ላይ ሊውሉ ይገባል ፡፡በተጨማሪም የታዳጊዎችን ተስጥኦ በመለየት ብቁ ለሆኑ ባለሙያዎች የተለያዩ ስልጠናዎችን በመስጠት የነገዎቹን የብሔራዊ ቡድኖቻችን ተጫዋቾች ዛሬ ላይ ለመመልመል መትጋት ይኖርብናል፡፡
ስለ ፀሐፊው
የአስተያየቱ ፀሐፊ አሰልጣኝ ደስታ ታደሰ ነው፡፡ አሰልጣኙ ባለፉት አስር ዓመታት በበጎ ፍቃድ ታዳጊዎችን በማሰልጠንና ለበርካታ ክለቦች በማበርከት እውቅና ባተረፈው የአስኮ እግር ኳስ ፕሮጀክት ሲያሰለጥን ቆይቷል ፡፡ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ በአፍሮ-ፅዮን እግር ኳስ ክለብ ከ17 ዓመት በታች ቡድኑ አሰልጣኝ ሆኖ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!
© ሶከር ኢትዮጵያ