የጉና ንግድ የምንግዜም ምርጥ ተጫዋች ማነው? ከተባለ የብዙዎች መልስ ዳንኤል ፀሐዬ ነው፤ በዚህ ኃሳብ የሚከራከርም በብዛት አይገኝም። በርግጥ አጥቂው በከባድ ጉዳቶች እንደተጠበቀው ባይደምቅም ቢጫውን ማልያ አድርጎ በተጫወተባቸው አስራ አንድ ዓመታት ድፍን የጉና ንግድ ደጋፊ የሚስማማበት የክለቡ ባለታሪክ ነው።
ከእግር ኳስ በፊት በሰርከስ ስፖርት ጥቂት ዓመታት የሰራው ዳንኤል በእግር ኳስ በቆየባቸው ዓመታት ተጫዋቾች የሚያልፍበት ጥበቡ ፣ ከቁመቱ በላይ ዘሎ በግምባር በሚያስቆጥራቸው ጎሎች እና ግብ ካስቆጠረ በኃላ በሚያሳያቸው አክሮባቲክ የደስታ አገላለፆች በልዩ ይታወቃል። በቁመቱ አጭር ቢሆንም ከተከላካዮች በላይ ዘሎ በግንባሩ ግብ ከማስቆጠር አላገደውም። ትውልድ እና እድገቱ በሽረ እንዳሥላሴ ቢሆንም በእግር ኳስ ምክንያት ከትውልድ ከተማው ወደ መቐለ የተዘዋወረው ገና የመጀመርያ ደረጃ ትምህርቱን እንዳጠናቀቀ ነበር።
በ1987 ወደ ጉና ንግድ ከተቀላቀለ በኃላ በዐጼ ዮሐንስ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እየተማረ ጨዋታዎች ማድረግ የጀመረው ይህ ደንዳና አጥቂ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በሦስት የዕድሜ እርከኖች አገልግሏል። ከፕሪምየር ሊጉ ምስረታ ከአንድ ዓመት በፊት በጉና ንግድ ማልያ የትግራይ ምርጥ ተጫዋች እና ኮከብ ግብ አግቢ ሆኖ በማጠናቀቅም በወቅቱ ለእግር ኳሱ ክስተት ሆኖ ነበር። ጉና ንግድ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ለመግባት ባደረገው የመጀመርያው የማጣርያ ጨዋታ የሙገር ሲሚንቶን ተከላካዮች በመረበሽ ለአራት ግቦች መቆጠር ምክንያት በመሆኑ ራሱን ለሀገራዊ እግር ኳስ ያስተዋወቀው ዳንኤል ፀሐዬ በ1999 የቡድን መሪ እና ተጫዋች ሆኖ ጉና ንግድን ባገለገለበት የእግር ኳስ ሕይወቱ የመጨረሻ ዓመት ከቢሾፍቱ ጋር ከተደረገ ጨዋታ በኃላ በይፋ ጫማውን ሰቅሏል።
ከ1987 እስከ 1999 በዘለቀው የእግር ኳስ ሕይወቱ ዙርያ ከዘጠናዎቹ ኮከብ ዳንኤል ፀሐዬ ያደረግነው ቆይታን እንደሚከተለው አቅርበነዋል።
የእግር ኳስ ጅማሬዬ በሽረ ከተማ ነው። እግር ኳስ እንደማንኛውም ህፃን በሰፈር ነው የጀመርኩት። ዕድሜዬ እየጨመረ በሄደ ቁጥርም ለትምህርት ቤት ጨዋታዎችም አድርግያለው። እድገቴም በጣም ፈጣን ነበር፤ የዛኔ ተፈጥሯዊ የኳስ ክህሎቴም ለየት ያለ ነበር። በዛ ምክንያት ከእኩያዎቹ ለየትባለ በዕድሜ ከሚበልጡኝ ጋር ብዙ እንድጫወት እና ገና እያለው የሜዳ ፈተናዎች የመጋፈጥ ልምድ እንዳዳብር ረድቶኛል። ከብቃቴ በተጨማሪ ጥሩ አስተባባሪ እና መሪ ነበርኩ። ልዩ የእግር ኳስ ፍቅር ነበረኝ፤ ተልኬ ስሄድም ኳስ እያንጠባጠብኩ ምናምን ነበር የምሄደው።
በታዳጊ ቡድን ደረጃ የመጀመርያው ክለቤ 04 የተባለ የቀበሌ ቡድን ነበር። በዛን ወቅት የነበረው ውድድር በጣም ሳቢ እና ፉክክር የተሞላበት ነበር። የዛኔ በትልቅ ደረጃ ለመጫወት ብዙ ፈተናዎች ነበሩ እነሱን አልፌ ከተማ ወክዬ መጫወት ከጀመርኩ በኃላ ግን የተሻለ የመታየት ዕድል ገጥሞኛል። በከተማ ደረጃም ኮከብ ተጫዋች ተብዬ ማልያ ተሸልሜያለሁ። በ1986 ደግሞ ሽረ እንዳስላሴ ወክዬ ተጫወትኩ ብዙም ሳልቆይ ደግሞ ዞናችን ወክዬ በአክሱም በተካሄደው ውድድር ተሳተፍኩ። በዛ ውድድር ጥሩ እንቅስቃሴ አድርጌም በትግራይ ደረጃ የውድድሩ ኮከብ ተብያለሁ። ጉና ንግድም ከውድድሩ በኃላ የዝውውር ጥያቄ አቀረበልኝና በአቶ ኃይሉ አማካኝነት ፈረምኩ። ከመፈረሜ በፊት ብዙ ነገሮች ነበሩ። ከቤተሰብ ተለይቼ ወደ መቐለ ለመሄድ ትንሽ ከብዶኝ ነበር። በወቅቱ የዞናችን ኃላፊ አቶ ኪሮስ ቢተው አግባቢነት ነው ለመሄድ የወሰንኩት። ጉና ከፈረምኩ በኃላ ደግሞ ብሄራዊ ቡድን የመጫወት እቅዴ እውነትም እውን ሊሆን ነው እንዴ ብዬ ያሰብኩበት ጊዜ ነበር። ከዛ በፊት የብሄራዊ ቡድን ጨዋታዎች በሬድዬ እየሰማሁ ነው ያደግኩት።
1987 የወንድሜ አባት ፍስሀ ገ/ትንሳኤ መቐለ ይዞኝ ሄዶ ለጉና ንግድ ፈረምኩ። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ለመቀጠልም አፄ ዮሐንስ ሁለተኛ ደረጃ ተመዘገብኩ። ትምህርቴ እስክጨርስ ድረስ እስክርቢቶ እና ደብተር እየገዛ ያስተማረኝ ጉና ነው። የዛኔ እግር ኳሱ ገና ነበር፤ ተጫዋች ልምምድ ሲሰራ ብቻ ነበር የሚመገበው። ለኔ ግን በልዩ ቁርስ፣ ምሳና እራት እዛው ክለብ ውስጥ ነበር። እንደ ተጫዋች እና እንደ ልጃቸው ነበር የሚንከባከቡኝ። በተለይም አብርሀም ተክለኃይማኖት እና አቶ ኃይሉ ትልቅ አስተዋፅዖ ነበራቸው። በ1987 በዕድሜም በተክለ ሰውነትም ገና ልጅ ነበርኩ። ግን በሁለተኛው ዙር ነው ጨዋታ የጀመርኩት። በሚቀጥለው ዓመት ደግሞ ምክር ቤት (ትራንስ ኢትዮጵያ)፣ ጉና ንግድ ፣ ዱቄት ፋብሪካ ፣ ሀዋሳ ጨርቃ ጨርቅ ፣ ባህርዳር ጨርቃ ጨርቅ ፣ አየር መንገድ እና ኮምቦልቻ የተሳተፉበት ውድድር ነበር። በውድድሩ በርካታ ጎሎች እና ጥሩ ብቃት ያሳየሁበት ነበር። ከሁለት ዓመት በኃላ ደግሞ 1989 የትግራይ ኮከብ ግብ አግቢ እና ኮከብ ተጫዋች ሆኜ ተሸልሜያለው። ክለባችንም በክልል ደረጃ የጥሎ ማለፍ እና የዙር ዋንጫ ያነሳበት ዓመት ነበር። በነዚህ ጊዜያት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን እየተማርኩ ነበር የምጫወተው። በ1990 ደግሞ ለወጣት ብሔራዊ ቡድን የተመረጥኩበት ዓመት ነበር። የጉና ቆይታዬ የክለብ እና የተጫዋች ሳይሆን ቤተሰባዊ ግኑኝነት ነው ነበረን። በጉና ያሳለፍኳቸው 11 ዓመታት በጣም ጥሩ ጊዜያት አሳልፍያለው። ጉና ትልቅ ክለብ ነው ከፕሪምየር ሊግ መጀመር በፊት በክልል ሻምፒዮና በተከታታይ ዋንጫ እያገኘ ለኢትዮጵያ ሻምፒዮና የተሳተፈ ቡድን ነው። ቡድኑ በጣም አሪፍ ቡድን ነበር ፤ የጨዋታ ቀን ይቅርና ልምምዳችንም ብዙ ተመልካቾች ይከታተሉት ነበር።
በ1990 ወደ ፕሪምየር ሊግ ለመግባት በድሬዳዋ እና በአዲስ አበባ በሁለት ምድብ ተከፍሎ በተደረገ ውድድር እኛ በሁለተኛው ምድብ አዲስ አበባ ላይ ነው ጨዋታዎቻችን ያደረግነው። የመጀመርያ ሀገራዊ ጨዋታችንም በወቅቱ ዝነኛ የነበረው ሙገር ሲሚንቶ ነበር። በጨዋታውም ሙገር ቀድሞ አገባብን፤ ብዙ ሳንቆይ እኔ ጎል ለማስቆጠር በተቃረብኩበት ጊዜ በሳጥን ውስጥ ተጠልፌ ፍፁም ቅጣት ምት ተሰጠንና አገባን። ከዛ እነሱም በድጋሚ አግብተውብን ሁለት ለአንድ መሩን በድጋሚ ደግሞ በተመሳሳይ መንገድ በሳጥን ጥፋት ተሰርቶብኝ ፍፁም ቅጣት ምት ተሰጠ እና አግብተን አቻ ሆንን። ሜዳው ሰፊ እና በጣም ምቹ ስለነበር ብዙ ጊዜ ኳስ መግፋት አበዛ ነበር። ለዛ ነው ሁለቴ ሳጥን ውስጥ ጠልፈውኝ ፍፁም ቅጣት ምት የተሰጠነው። ከዕረፍት በኃላ ብዙ ነገር አሻሽለን ገባን እንደተጀመረ ብዙ ሳንቆይ ለተስፋይ በርኸ የተባለ ተጫዋቻችን አመቻችቼ አቀብዬው ግብ አስቆጠርን። እኔም ተደስቼ በልዩ መንገድ በአክሮባት ደስታዬን ገለፅኩ። አራተኛው ደግሞ እኔ አስቆጠርኩ ፤ ይቺ ግብ ልዩ የሚያደርጋት ኳሷ ግብ ጠባቅያችን ተመስገን ፍስሀ ነው በቀጥታ ያሻገረልኝ። ጨዋታው አራት ለሁለት ተጠናቀቀ፤ ለክለባችንም ለእኔም ታሪካዊ ጨዋታ ነበር። ለዛ ነው ጠለቅ ብዬ በልዩ ያስታወስኳት። ሳንጠበቅ ለትልቁ ሙገር አሸነፍን እኔም በመጀመርያው ሀገራዊ ጨዋታዬ ጥሩ ብቃት አሳየሁ። ከጨዋታው በኃላ የኛ ሁለተኛ ጨዋታ ስለነበር በትሪቡን ነው የወጣነው ፤ ህዝብ ሞልቶ ነበር ። ልክ ልወጣ ስል ደጋፊዎች ስሜን ሲጠሩኝ እያንዳንዱ እየዞርኩ ሰላም አልኳቸው (ሳቅ)። የዛኔ ገና ተማሪ በመሆኔ ተገርመው ብዙ ሚድያዎች አናግረውኝ ነበር። ቡድናችን አሪፍ ነበር፤ ዮሴፍ ፣ የማነ ፣ እስቲፋኖስ ፣ ሚካኤል አብርሀ ፣ ክንደያ ታመነ የመሳሰሉ ጥሩ ተጫዋቾች የነበሩበት ቡድን ነው። ለእግርኳሱ የሚሞቱ የድርጅት አመራሮች እና ለእግር ኳስ ያለውን የሚሰጥ አሰልጣኝ ነበረን።
ከዛ ውድድር በኃላ ብዙ ቡድኖች የዝውውር ጥያቄ አቅርበውልኝ ነበር። ሆኖም ቅድም እንዳልኩህ ከጉና ጋር የነበረን ግንኙነት ጥብቅ ስለነበር አልተቀበልኩትም። ያሳደገኝ ቡድን ትቼ የመሄድ ሀሳብ አልነበረኝም። በወቅቱ በፕሪምየር ሊግ ጥሩ የሚባል ግዜ ነበረን። በ1993 ጥሎ ማለፍ ሁለተኛ ደረጃ ይዘን አጠናቀንም በአፍሪካ ውድድር ተሳትፈናል። የሚገርምህ ነገር የአፍሪካ ውድድር በተሳተፍንበት ዓመት ነው ከፕሪምየር ሊግ የወረድነው። በዓመቱ እኔ ብዙ ጨዋታ አላደረግኩም፤ ከብሄራዊ ቡድን ጋር ቆይታ ነበረኝ። በሁለተኛው ዙር ደግሞ እጅግ በጣም አስቸጋሪ የጉዳት ጊዜ ነው ያሳለፍኩት። የብሽሽት ጉዳቱ ተደራራቢ ጨዋታ በማድረግ እንደመጣ ነበር ዶክተሮች የነገሩኝ። የዛን ዓመት ወደ ሳዑዲ አረብያ ሄጄ በጅዳ ከተማ ነው የታከምኩት። ጉዳቱን ከባድ ያደረገብኝም ማደንዘዣ እየተወጋሁ ብዙ ጨዋታ ማድረጌ እና ጊዜ ወስጄ አለመታከሜ ነበር። ይሄ ግዜ በእግር ኳስ ሕይወቴ ትልቅ ጠባሳ ጥሎብኝ አልፍዋል። ወደ ሳውዲ ዓረብያ ይሂድ ህክምና ይጀምር ከነ ጉዳቱ አይጫወት ተብሎ አርፌ ነበር፤ ወደ ውጭ ለመሄድ ሂደቶችም ጀምሬ ነበር። ሆኖም ቡድኑ እያሽቆለቆለ ስሄድ ድጋሜ ጨዋታ ማድረግ ጀመርኩ። በአዲስ አበባ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ባደረግነው ጨዋታም ሌላ ትልቅ ጉዳት ደረሰብኝ ፤ የአጥንት መሰንጠቅ ጉዳት ነበር ጉዳቱ። መጀመርያ ላይ ግን አላወቅንም ነበር።
ከዛ በኃላ ግን በቃ ይብቃው የህክምና ጉዳዩን ያድርግ ተባልኩ። ከትንሽ ግዜ በኃላ ደግሞ ቡድኑ ማሽቆልቆሉ ተያያዘው ድጋሜ ወደ ህክምና ከመሄዴ በፊትም እግሬ ትንሽ ለውጥ ስላሳየ መጫወት አለብኝ ብዬ ጨዋታ ጀመርኩ።
በመቐለ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ባደረግነው ጨዋታም ተቀይሬ ገባሁና ክለባችን ቅያሪ ከጨረሰ በኃላ ጠግኖ የነበረው እግሬ ለሦስተኛ ጊዜ ጉዳት ደረሶበት እንደምንም ብዬ ጨዋታውን ጨረስኩ። ከዛ በኃላ ግን በቃ አልቻልኩም በጉዳት ከውድድር ዓመቱ ውጭ ሆንኩ፤ ቡድናችንም ወረደ። ጉና የወረደበት ዓመት በመጀመርያው ዙር ሦስተኛ ደረጃ ይዞ ነበር ያጠናቀቀው። ሁለተኛ ዙር ግን ተንሸራቶ መውረድ ቻለ።
በቀጣዩ ዓመት ወደ ሳውዲ ዓረብያ ሄድኩ፤ በዛ ዓመት ደግሞ ጉና ንግድ በድጋሚ ወደ ፕሪምየር ሊግ አደገ። የዛን ጊዜ እኔ ለህክምና ጅዳ ነበርኩ። ከዛ መልስ በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የተረጋጋ ነገር አልነበረም። በክለቦች እና በፌደሬሽን ክፍተት ተፈጥሮ የተረጋጋ ነገር አልነበረም። በዛ ወቅት በጉና ጫማዬን ለመስቀል እያሰብኩ ነበር፤ ነገር ግን ውበቱ አባተ አዳማ ከተማ እያለ ጥያቄ ሲያቀርብልኝ ለአዳማ ፈረምኩና ለክለቡ አንድ ዓመት ተጫወትኩ። ድጋሚ ከአንድ ዓመት በኃላ ደግሞ ወደ ጉና ንግድ ተመልሼ በተጫዋችነት እና በቡድን መሪነት ቡድኑን አገልግያለው። የመጨረሻ ጨዋታዬም ከቢሾፍቱ ጋር ነበር ያደረግኩት። አሁን የጠቀሱት ጊዜ በእግር ኳስ ሂወቴ መጥፎ ግዜያት የሚባሉ የጉዳት ዓመታት ናቸው። ጥሩ በነበርኩባቸው ዓመታት ግን ከምወደው ክለብ ብዙ ጣፋጭ ጊዜያት አሳልፍያለው። ከዚህ ጊዜ በኋላ ግን ከተጫዋችነት ራሴን አገለልኩ። ለምን እንደዛ አይነት ውሳኔ እንደወሰንኩ አሁን ራሱ ይገርመኛል።
በብሔራዊ ቡድን የነበረኝ ቆይታ ደግሞ በጣም አሪፍ ነበር። ለመጀመርያ ጊዜ ከ17 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድን ነው የተመረጥኩት በአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው እና መኩርያ አሸብር ነበሩ። ውድድሩ በኢትዮጵያ ነበር የተዘጋጀው፤ ኢትዮጵያም ሁለት ቡድን ነበር ያዘጋጀችው። አንዱ ቡድን በአዲስ አበባ ሁለተኛው ደግሞ በድሬዳዋ ነበር። እኔ በድሬዳዋው ብሔራዊ ቡድን ውስጥ ነበርኩ። ከዛ በኃላ ደግሞ ከሀያ ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድን ቆይታ ነበረኝ፤ ከስዊድን ጋር የአቋም መለኪያ ጨዋታ አድርገን በሁለቱም ጨዋታዎች ግብ አስቆጥሬያለው። ከዛ በኃላ ለማጣርያ ከግብፅ ጋር ጨዋታ ነበረን እንደውም በዛ ጨዋታ ከኔ በፊት በልምድ የተሻሉ የነበሩ ተጫዋቾች በዕድሜ ምክንያት ከቡድኑ ሲወጡ እኔ የቡድኑ አምበል ነበርኩ። ከግብፅ ጋር በአዲስ አበባ ባዶ ለባዶ ተለያይተን በካይሮ ሁለት ለአንድ ተሸነፍን። ይቺ ጨዋታ ብናሸንፍ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ማለፍ እንችል ነበር። የሚገርምህ ነገር ከዚች ጨዋታ በኃላ ደግሞ በእድሜው ይጫወት ተብዬ በ1989 ወርጄ ከ17 ዓመት ብሄራዊ ቡድን ተጫውቻለው። ከሞዛምቢክ እና ናይጀርያ ጋርም ጨዋታዎች አድርጌያለው። የዋናው ብሄራዊ ቡድን ማልያ አድርጌም ተጫውቻለው። የዛኔ ነብሱን ይማረው ሥዩም አባተ ዋና፤ ገብረመድህን ኃይሌ ምክትል አሰልጣኝ ነበሩ። ከዛ ግን ከአንድ የዛምቢያ ቡድን ጋር የአቋም መለኪያ ጨዋታ ካደረግኩ በኃላ ተጋጣምያችን ኤርትራ ከውድድሩ ራስዋን አገለለች። እኔም በጉዳት ብዙ ጨዋታ ማድረግ አልቻልኩም። የብሔራዊ ቡድን ቆይታዬ በአጭሩ ይህን ይመስላል።
መድረስ ያለብኝ ቦታ ላይ አልደረስኩም፤ በእግር ኳስ ሕይወቴ ስፖርቱ የሚፈልገው ሥነ-ስርዓትን አሟላ ነበር። እንደ ወጣትም በየመሸታ ቤቱ ሳልታይ ነው ኳስ ያቆምከት። በልምምድም ጠንካራ ሰራተኛ ነበርኩ። ካለ እረፍት ለብዙ ዓመታት መጫወቴና ከነ ጉዳቴ ብዙ ጨዋታዎች ማድረጌም ብዙ ነገር ጎድቶኛል።
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!
© ሶከር ኢትዮጵያ