“የዘመናችን ክዋክብት ገፅ” ከረመዳን የሱፍ ጋር…

በስሑል ሽረ እና በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የተሳኩ ጊዜያትን እያሳለፈ የሚገኘው ወጣቱ የግራ መስመር ተከላካይ ረመዳን የሱፍ የዛሬው የዘመናችን ክዋክብት ገፅ እንግዳችን ነው፡፡

ትውልድ እና ዕድገቱ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በርካታ ተጫዋቾችን ለእግርኳሳችን እያበረከተ በሚገኘው ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳ ከተማ ውስጥ በምትገኝ አረብ ሰፈር ተብላ በምትጠራ ሰፈር ውስጥ ነው። ለስታዲየም አቅራቢያ በሆነችው ሰፈሩ ኳስን በማንከባለል የጀመረው የተጫዋችነት ጉዞው ፈጣን እደገት እያሳየ በመምጣት በትውልድ ክልሉ ከ15-17 ዓመቱ ድረስ በፕሮጀክት ስልጠና ሰልጥኖ አሳልፏል፡፡ በተለይ ቤኒሻንጉልን ወክሎ በ2008 ላይ አዳማ ላይ በተደረገ የክረምት ሀገር አቀፍ የፕሮጀክት ውድድር ላይ ሲሳተፍ ነበር በርካታ ክለቦች የያኔውን ታዳጊ በመፈለግ የእናስፈርምህ ጥያቄን ማቅረብ የጀመሩት። ተጫዋቹም የተሻለ ነው ብሎ በወቅቱ ወደሚያስበው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተስፋ ቡድን በማምራት ተቀላቀለ። በወቅቱ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አሰልጣኝ የነበሩት አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም ተጫዋቹ ወደ ዋናው ቡድን ለማሳደግ በመወሰናቸው በ2009 ቢያሳድጉትም ተጫዋቹ ባደገበት ዓመት ግን ክለቡ የመፍረስ አደጋን ሲያስተናግድ ዕጣፈንታው አብሮ በመክሰሙ ወደ ትውልድ ከተማው አሶሳ ሊመለስ ተገደደ። በትልቅ ደረጃ ራሱን ለማሳየት ተቃርቦ መሰናክሎችን ቢያስተናግድም ተስፋ መቁረጥ ያልታየው ረመዳን ወደ ቤተሰቡ ከተመለሰ በኃላ በ2010 ለአንደኛ ሊጉ ንስር ክለብ እየተጫወተ እስከ 2011 ግማሽ ዓመት ድረስ በቡድኑ ቆይታን አድርጓል፡፡

በ2011 ግማሽ ዓመት ላይ ረመዳን ወዳሰበው ትልቅ ደረጃ የመሸጋገር ህልሙ በጓደኛው አሳሪ አልመሀዲ አማካኝነት ዕውን ሆነ፡፡ ዐምና ጥር ወር ላይ የስሑል ሽረ ተጫዋች የነበረው አሳሪ ለክለቡ አሰልጣኝ ሳምሶን አየለ በሙከራ እንዲመለከቱት ጥየመቄ አቅርቦ አስገራሚ አቅሙን በሙከራ ጊዜው በማሳየቱ በይፋ ሊያስፈርሙት ችለዋል፡፡

የግራ መስመር ተከላካዩ ረመዳን ናስር ዐምና ግማሽ ዓመት ላይ ወደ ስሑል ሽረ ካመራ ጊዜ ጀምሮ ዘንድሮ ሊጉ በኮሮና ቫይረስ እስከ ተቋረጠበት ጊዜ ድረስ ምርጥ አቅሙን በማሳየት በበርካታ ተመልካቾች እና ክለቦች ዓይን ውስጥ በአጭር ጊዜ ውስጥ መግባት ችሏል። በአሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ የዋልያዎቹ ስብስብ ውስጥ በተደጋጋሚ መጠራት ችሏል። በተለይ በባህር ዳር ስታዲየም ኢትዮጵያ አይቮሪኮስትን 2ለ1 በረታችበት ወቅት በአሰላለፍ ውስጥ ገብቶ አስገራሚ እንቅስቃሴ ማድረግ የቻለው እና ውሉ በስሑል ሽረ በመጠናቀቁ በበርካታ ክለቦች በጥብቅ እየተፈለገ የሚገኘው ይህ ተስፈኛ ተጫዋች አዝናኝ ጥያቄዎች በሚቀርቡበት የዘመናችን ክዋክብት ገፅ የዛሬው እንግዳችን ነው፡፡

ሊጉ በኮሮና በተቋረጠበት ወቅት እንዴት ረመዳን እንዴት እያሳለፈ ነበር የቆየው ?

በግሌ እየሰራሁ ነበር እስከ አሁን ጊዜ ድረስም አላረፍኩም። አሁን አንተ ስታወራኝ ራሱ ከልምምድ ደክሞኝ መግባቴ ነው፡፡ እያረፍኩ አይደለም በግሌ በደንብ እሰራለሁ። ከጓደኞቼ ጋርም እሰራለሁ። ሊጉ ተቋርጧል ብዬ ቁጭ አላልኩም። አሳሪን ጨምሮ አሶሳ ብዙ ተጫዋቾች ስላሉ ከእነሱ ጋር እየተጫወትኩ ነው እያሳለፍኩ ያለሁት፡፡

በኮሮና ረጅም ጊዜ ከሜዳ ርቀህ ነበር እንደ ሌሎች ስፖርተኞች ሁሉ። አሁን ደግሞ ክረምቱ ገባ እንደ ስፖርተኛ ጊዜው አልከበደህም?

በጣም ከባድ ጊዜን እያሳለፍን ነው። በተለይ ያለ ውድድር ረጅም ጊዜ መቆየት ይከብዳል። ምንም ማድረግ ስለማይቻል እኚህ ሁሉ ችግሮች ቢፈጠሩም የቀጣዩ የ2013 ዓመት ውድድር ይጀመራል በሚል ሀሳብ በደንብ እንድዘጋጅ ረድቶኛል። ፈጣሪ ብሎ ሊጉ ከኖረም ለዛ ብዬ እየተዘጋጀሁ እገኛለሁ፡፡

ረመዳን ኳስ ተጫዋች ባይሆን ኖሮ ምን ላይ ይገኝ ነበር?

እግር ኳስ ተጫዋች ባልሆን ኖሮ ወደ ንግዱ እገባ ነበር። አባት እና እናቴ ወደ ንግዱ ስለሆኑ እኔም እነሱን ተከትዬ ወደዛ አመዝን ነበር፡፡ ነጋዴ መሆኑ ላይ ግን ወደ ፊትም ሀሳብ አለኝ…(እየሳቀ)

በፕሪምየር ሊጉም በብሔራዊ ቡድንም እየተጫወትክ ነው እና በዚህ ወቅት ከነዚህ ተጫዋቾች ጋር አብሬ ተጣምሬ ብጫወት ያስደስተኛል የምትለው ይኖራል?

ለሊጉ አዲስ ነኝ ብዙም አላውቅውም (እየሳቀ) … ብሔራዊ ቡድን ካየዋቸው ውስጥ ግን ብዙ ተጫዋቾች አሉ። ግን እኔ ከሽመልስ በቀለ እና ሱራፌል ዳኛቸው ጋር አብሬ በአንድ ክለብ ብጫወት ያስደስተኛል። እንደነሱ አይነት ድንቅ ተጫዋች ያስደስቱኛል። ኳሊቲያቸው፣ ሜዳ ላይ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ሁሉ ይማርከኛል። በነዚህ ምክንያቶች እመርጣቸዋለሁ፡፡

በስሑል ሽረ ቆይታህ በተቃራኒው ስትገጥመው የሚያስቸግርህ ፈታኝ የሆነብህ ተጫዋች ማነው?

(እየሳቀ) ፈታኝ የሆነብኝ አሁን ጊዮርጊስ የገባው አዲስ ግደይ ነው፡፡ በጣም አስቸጋሪ እና ፈታኝ ተጫዋች ነው፡፡ ብዙ ኳሊቲ አለው፤ ለኔ ሜዳ ላይ እሱን ለመያዝ አስቸጋሪ ነው፤ ያስቸግረኛል፡፡

ሚስጥረኛዬ የምትለው እግር ኳስ ተጫዋች ማነው ?

የልቤ ሚስጥረኛ ነው ብዬ የማስበው ያው አሁን ወልቂጤ የሚጫወተው አሳሪ አልመሀዲ ነው፡፡ ብዙ ነገር ያደረገልኝ እሱ ነው፡፡ አንድ ነገር አስቤ እንኳን ቢሆን ከሱ ጋር ነው የማወራሁ እና የማማክረው፡፡

ትዳር መስርተሀል? ወይንስ ከቤተሰብ ጋር ነው ኑሮህ ?

ኧረ አሁን ከቤተሰብ ጋር ነኝ ያለሁት። ጊዜው ሲደርስ ግን መሆኑ አይቀርም፡፡

ረመዳን በእግር ኳሱ ያዘነበት ወቅት መቼ ነው?

ያዘንኩበት ወቅት ያው 2009 ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተስፋ ቡድን ወደ ዋናው አድጌ ነበር፤ በዛን ወቅት የማደግ ዕድልን አግኝቼ ቡድን የወረደበት ወቅት እጅግ ያዘንኩበት ዓመት ነበር።

የተደሰትክበትስ ወቅትስ?

ደስተኛ የሆንኩበት ዓምና ነው። ክለቤ ሽረ ከባድ ጊዜን ነበር እያሳለፈ የነበረው። በአንደኛ ዙር ላይ የመውረድ አደጋ ነበረበት፤ አስፈሪ ጊዜ ነበር። ያኔ ግን ውጤታማ ሆነን ከመውረድ የተረፍንበት ዓመት ለኔ ሻምፒዮን ከመሆን በላይ ደስተኛ ሆኜ ያሳለፍኩበት ጊዜ ነበር። ሁሉም ሰው ተስፋ ቆርጦ ስለነበር ያልተገመተ ጊዜ ነበር። ተግተን ሰርተን ውጤት ይዘን ስንጨርስ ለኔ የሚገርም ደስታ ነበር የተሰማኝ ፡፡

የምግብ አጠቃቀምህ እንዴት ነው ? ምን አይነት ምግብ ታዘወትራለህ ?

ምግብ እንኳን ብዙም አላማርጥም፤ አብዛኛዎቹን እጠቀማለሁ (እየሳቀ) አብዛኛው ጊዜ የምጠቀመው ፍራፍሬ ነገሮችን ነው። እንደ ሙዝ፣ ሸንኮራ እንዲሁም አትክልት ነገሮችም በጣም ደስ ይሉኛል፡፡ ሥጋ ባላበዛም እጠቀማለሁ፡፡

ሰዎች የማያውቁት የተለየ ባህሪ አለኝ የምትለው ይኖር ይሆን ?

የተለየ ባህሪ የለኝም። ሰው ብዙ ጊዜ ሲያኝ ዝምተኛ አድርጎ ነው የሚያስበኝ። የተለየ ባህሪ ግን የለኝም። በተለይ ወጣ ያሉ ነገሮች የሉኝም። ብዙም ከሰው ጋር የመቀራረብ ነገር ስለሌለኝ ከሚቀርቡኝ ጋር ግን እስቃለሁ እጫወታለሁ፡፡

ቅፅል ስም አለህ ?

ሰፈር ውስጥ “ሮሜ” ብለው ነው የሚጠሩኝ። ጓደኞቼ ረመዳን የሚለውን ለማሳጠር የሚጠቀሙት ስም ይመስለኛል። ሽረ እያለሁ ረመዳን ይሉኛል አሶሳ ስመጣ ግን ሁሉም በዚህ ስም አይጠሩኝም። ሮሜ በሚለው ብቻ ነው የሚጠሩኝ፡፡

ከኳስ ውጪ ምን ያዝናናሀል ?

ውሀ ዋና በጣም ያዝናናኛል። ሌላው ደግሞ ዲኤስቲቪ ቤት ቁጭ ብሎ ኳስ ማየት በጣም ያስደስተኛል፡፡

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ