ዛሬ በጀመርነውና ወደ አሰልጣኝነቱ በቅርቡ ብቅ ያሉ ጀማሪ አሰልጣኞችን በምናቀርብበት አምድ ከፋሲል ከነማ ምክትል አሰልጣኞች መካከል አንዱ ከሆነው ሙሉቀን አቡሃይ (ኢንጅነሩ) ጋር ሰፋ ያለቆይታ አድርገናል።
ከፋሲል ከነማ ታዳጊ ቡድን ጀምሮ ከ18 ዓመት በላይ በተለያዩ የከተማው የውስጥ የእግርኳስ እርከኖችን እንዲሁም በሀገሪቱ የሊግ እርከኖች ብሔራዊ ሊግ ፣ ሱፐር ሊግ እንዲሁም ክለቡ ወደ ፕሪምየር ሊግ ሲያድግም ክለቡን እስከ ለቀቀበት ወቅት በአምበልነት በመምራት ለበርካታ ዓመታት በአፄዎቹ ቤት ያገለገለው ሙሉቀን አቡሃይ በደጋሜ በአሰልጣኝነት ወደ አደገበት ክለብ ተመልሷል። በአሰልጣኝነቱም በተሰረዘው የ2012 የውድድር ዓመት ከዐፄዎቹ ጋር በረዳት አሰልጣኝነት እየሰራ መቆየቱ ይታወሳል። ከሙሉቀን አቡሃይ ጋር ስላሳለፈው የእግር ኳስ ህይወት እንዲሁም ተጫዋቾች እግርኳስን ካቆሙ በኋላ ወደ ጀማሪ አሰልጣኝነት ሲገቡ የሚገጥማቸውን ከልምዱ ለማከፋል ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ቆይታ አድርጓል።
በተጫዋችነት ዘመንህ የት የት ተጫውተሀል ?
በፋሲል ከነማ መልያ ከ’ሲ’ ቡድን ጀምሮ እስከዋናው ከ1986 ክረምት የጀምሮ ለ18 ዓመታት ተጫውቻለው። ክለቡ ቤሔራዊ ሊግ ፣ ሱፐር ሊግ እና ፕሪምየር ሊግምኖ ሲገባ ከክለቡ ጋር አሳልፊያለሁ። ከዛ ውጪ በመሀል እየወጣሁ የተጫወትኩባቸው አጋጣሚዎችም ነበሩ። መድን ለአራት ዓመታት ፣ ሰበታ ለአንድ ዓመት ፣ ከዛ ተመልሼ አማራ ውሃ ስራዎችም ተጫውቻለሁ። በመጨረሻም እግርኳስ ያቆምኩት ኢኮስኮ ለአንድ ዓመት ከተጫወትኩ በኋላ ነበር።
አሰልጣኝ ለመሆን የተነሳሳኸው መቼ እና እንዴት ባለ ሁኔታ ነው? አሰልጣኝነት በውስጥህ ነበር ወይስ ከተጫዋችነት ሲገለሉ አሰልጣኝ የመሆን ልማድ ነው ወደ ሙያው ያመጣህ ?
በተጫዋችነት ዘመኔም በፋሲል ቤት ከታዳጊ ቡድን ጀምሮ በአምበልነት ክለቤን አገለግል ነበር። ለበርካታ ዓመታት አምበል ስሆን ለአሰልጣኞች ቅርብ ነበረኩ እና ያ ነገር በውስጤ የፈጠረብኝ ተፅዕኖ አሰልጣኝ የመሆን ፍላጎት አሳድሮብኛል። የአሰልጣኝነት የመጀመሪያ ደረጃ ኮርስ የወሰድኩት ተጫዋች እያለሁ ነው እና ከበፊትም ፍላጎት ነበረኝ ወደዚህ መስመር የመግባት ዕቅዴ የቆየ ነው።
የአጭር እና የረጅም ጊዜ ዕቅድህ ምንድነው?
ወደ አሰልጣኝነት ህይወት የተቀላቀልኩት ቅርብ ጊዜ ነው ፤ ገና ዓመትም አልሞላኝም። የአጭር ጊዜ ዕቅዴ ኮርሶችን መውሰድ ነው፤ የአሰልጠኝነት ደረጃዬን ከፍ ለማድረግ። በአሰልጣኝነቱ ላይም እየሰራሁበት ስለሆነ አብሬ ከምሰራቸው አጋሮቼ ልምዶችን መውሰድ ነው የአጭር ጊዜ ዕቅዴ። ወደፊት ግን በተጫዋችነት ረዥም ጊዜ ያገለገልኩትን ክለብ ትልቅ ደረጃ ላይ ማድረስ እፈልጋለሁ። ተጫዋች ሆኜ ያላሳካሁት ብሔራዊ ቡድን የመጫዎት ፍላጎቴንም በአሰልጣኝነት ማካካስ እፈልጋለሁ።
ተጨማሪ ሥልጠናዎችን ለማግኘት በግልህ ምን ያህል ትጥራለህ ? ከዘመናዊ እግርኳስ ጋር ራስህን ለማስኬድስ ?
አሰልጣኝነት ከጀመርኩ ቅርብ ጊዜ ነው ብዬሀለው። ከዛ ውስጥ እንኳን ሁለት የማሻሻያ ኮርሶችን አግኝቼ ወስጃለሁ። ከዛ ውጪ ሁሌም ባገኘሁት አጋጣሚ ራሴን ለማሳደግ እጥራለሁ። ያው ከዘመኑ ጋር ለመሄድ ቴክኖሎጂው በጣም ቅርብ ስለሆነ በርካታ ኮርሶችን ኢንተርኔት ላይ እየወሰድኩ እየተማርኩ ነው።
የሥልጠና ዘይቤውን መከተል የምትፈልገው አሰልጣኝ ማነው? ምን ዓይነት ዘይቤስ ትመርጣለህ?
በእግርኳስ ህይወቴ ለብዙ ዓመታት ስጫወት በርካታ አሰልጣኞች ጋር አሳልፊያለሁ ፤ ብዙ ነገርም ተምሬያለሁ። አሁን ኳስ ላቆም ስል የመጨረሻ ዓመት ላይ አብሬው የሰራሁት የኢኮሥኮ አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው ከእሱ ብዙ ነገር ተምሪያለሁ። ለአሰልጣኝነቴ የሚጠቅሙኝን ነገሮች ከሀገር ውጪ ከሆነ ዚነዲን ዚዳን በተጫዋችነት ጊዜውም በአሰልጣኝነት ጊዜውም የሱ ዘይቤ አድናቂ ነኝ። እና የእሱን ዘይቤ መከተል ነው የምፈልገው። ያው የሱን ዘይቤ አምጥተህ እኛ ሀገር እግርኳስ ላይ አትተገብረውም፤ የምታስተካክለው የምታዋህደው ነገር ይኖራል። ደጋፊህን ታያለህ አካባቢህን ታያለህ ያንተም ፍልስፍና ተጨምሮበት ነው ወደ እዚህ የምታመጣው። እንደ ዘይቤ ግን የሁለቱ አሰልጣኞች አሰለጣጠን ይመቸኛል።
ከአሰልጣኝ ሥዩም ከበደ እና ሌሎች አባላት ጋር ያለህ ግንኙነት ምን ይመስላል? ስዩም ረጅም ጊዜ ከማሰልጠኑ አንፃር ምን ዓይነት ትምህርት እየቀሰምክ ነው?
ያው እንደ ተጫዋች ከብዙ አሰልጣኞች ልምድ ወስጃለሁ። አሁን ከስዩም ጋር እንደ አሰልጣኝ ሆኜ መስመር ውስጥ ከገባሁ በኋላ ስለሆነ ብዙ ልምዶችን እያገኘሁ ነው። አሰልጣኝ ሥዩም ከበደ በርካታ ልምድ ያለው አሰልጣኝ ስለሆነ ብዙ ነገር እየተማርኩ ነው። ከሌሎች አሰልጣኞች ስብስብ ጋርም በጣም ጥሩ ነገር እየተማርኩ ነው። ከእነሱ ጋር ጓደኛም ስለሆንን ተጫዋች ሆኜም አብሪያቸው ስለነበርኩ የተሻለ ግንኙነት አለኝ።
ወደ አሰልጣኝነት ከመጣህ በኋላ ያጋጠሙህ ፈተናዎች?
ያው ያጋጠመኝ ፈተና የለም ማለት ይቻላል። ቡድኑን የተቀላቀልኩት ውድድር ከተጀመረ በኋላ ነው። በኋላም ወድድሩ የተጠናቀቀው ሳያልቅ ስለሆነ አጭር ጊዜም በመሆኑ ያጋጠመኝ ከባድ ፈተና የለም።
በተጫዋችነት አላሳካሁትም፤ በአሰልጣኝነት ግን ማሳካት እፈልጋለሁ የምትለው አላማ ምንድነው?
አዎ ቅድም እንደነገርኩህ ነው ከአንድም ሁለት ሦስቴ ብሔራዊ ቡድን የመጠራት ዕድሉን አግኝቼ መልያውን ለብሶ የመጫዎት ዕድሉን አላገኘሁም። በጉዳትም በዕድሜም ከፕሪምየር ሊግም ተጫዋቾች አምጥተው የተመለስኩበት አጋጣሚ አለ። አንዴ ታዳጊ ሁለቴ ደግሞ ወጣት ቡድን ተጠርቼ ነበር። እና ከእግዚያብሔር ጋር ወደፊት ብሔራዊ ቡድን የማሰልጠን ምኞቴን ማሳካት እፈልጋለሁ ።
ወደፊት እግርኳስ አቁመው ወደ አሰልጣኝነት ለሚመጡ ተጫዋቾች ምን የምታካፍላቸው ነገር አለ ?
ወደፊት አሰልጣኝ እሆናለሁ የሚል ፍላጎት ካላቸው ሳቆም እሆናለሁ ብሎ ማሰብ ብቻ በቂ አይደለም። አሰልጣኝ ሆኜ እተገብረዋለሁ የሚሉት ዕቅድ ካላቸው በተጫዋችነት ጊዜያቸው ኮርሶችን ቢወስዱ ሲጨርሱ ነገሮች ይቀሉላቸዋል። ኮርሶችን ቀድመው ቢወስዱ ጥሩ ነው።
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!
© ሶከር ኢትዮጵያ