” ትልቁ እቅዴ ከምወደው ክለቤ ጋር የፕሪምየር ሊግ ዋንጫ ማንሳት ነው” ስምዖን ማሩ

ትውልድ እና እድገቱ በዓዲግራት ከተማ ነው። ባለፈው የውድድር ዓመት አጋማሽ ወደ ዋናው ቡድን ካደገ በኋላ በተለያዩ ቦታዎች ተሰልፎ ባሳየው ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ በቢጫ ለባሾቹ ቤት ተስፋ ከሚጣልባቸው ወጣቶች ተርታ እንዲመደብ አድርጎታል።

በመስመር ተከላካይነት እና በመስመር ተጫዋችነት መሰለፍ የሚችለው ስምዖን ማሩ በተለይም በወልዋሎ ሁለተኛ ቡድን የተሳካ ጊዜ አሳልፏል። ባለፈው የውድድር ዓመት በአሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ አማካኝነት ወደ ዋናው ቡድን አድጎ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ የሚገኘው ይህ ተስፈኛ ከአሳዳጊው ክለብ ጋር የሊጉን ዋንጫ መሳም ዋነኛ እቅዱ እንደሆነ ይገልፃል። በ”ተስፈኞች” አምድ ከተጫዋቹ ጋር ያደረግነው ቆይታንም እንዲህ አቅርበነዋል።

“እግርኳስን በሰፈር ነው የጀመርኩት፤ እናት የሚባል የታዳጊ ቡድን ነበር። በዛ ነው የጀመርኩት በቡድኑም አሪፍ ቆይታ ነበረኝ። ከዛ በኃላ በ2010 ሁለተኛው ዙር ወደ ወልዋሎ ሁለተኛ ቡድን ተቀላቀልኩ። በግል ጥሩ ቆይታ ነበረኝ ፤ እንደ ቡድንም በጣም ጥሩ ቡድን ነበርን፤ እስከ ሀገራዊ የማጠቃለያ ውድድር የተሳተፍንበት ጊዜ ነበር። በግሌም በርካታ ግቦች ያስቆጠርኩበት ነበር። በተለይም በአክሱም በተዘጋጀው የትግራይ ክልል የማጠቃለያ ውድድር ወሳኝ ግቦች ያስቆጠርኩበት እና ራሴን ከእግር ኳስ ቤተሰብ በደንብ ያስተዋወቅኩበት ጊዜ ነበር። ከዛ በኃላ በ2011 አጋማሽ ወደ ወልዋሎ ዋናው ቡድን ማደግ ቻልኩ። ልክ ወደ ዋናው ቡድን እንዳደግኩ አሰልጣኝ ዮሐንስ ሳህሌ የመጫወት እድል ሰጥቶኛል። ልምድ ያላቸው ተጫዋቾችም ብዙ እገዛ አድርገውልኛል፤ በዚ አጋጣሚ ማመስገን እፈልጋለሁ። በመጀመርያው ስድስት ወር የተሰጠኝ ዕድል ተጠቅሜ ጥሩ ነበርኩ ለጎል የሆነ ኳስም አመቻችቻለው፤ በዘንድሮ የውድድር ዓመት ደግሞ የተሻለ ዕድል ተሰጥቶኝ በተለያዩ ቦታዎች ተጫውቻለው። በልምድ ደረጃ ብዙ ልምድ አግኝቻለው በዛ ረገድ እንደውም እድለኛ ነኝ ፤ በብሐራዊ ቡድን ለብዙ ዓመታት ያገለገሉ እንደነ ዓይናለም ኃይሉ፣ ብርሀኑ ቦጋለ፣ አሥራት መገርሳ እና ሌሎች ብዙ ልምድ ወስጃለው።

” ብዙ ቦታዎች መጫወት እችላለው። ዘንድሮ የመስመር ተከላካይ እና የመስመር ተጫዋች ሆኜ አገልግያለሁ። በቀጣይም ይህን አጠናክሬ እቀጥልበታለው። ከመደበኛ ልምምድ ውጭ ተጨማሪ ነገሮች መስራት እወዳለው። እሱ እሱ ብዙ ነገር ጠቅሞኛል። አባቴ ማሩ ገብረፃዲቅም ብዙ አግዞኛል። ሁሉም ነገር ያማላልኝ ነበር፤ ለኔ ብቻ ሳይሆን ለብዙዎች ጥሩ አስተዋጽኦ አድርጓል። በቀጣይ የመጀመርያው እቅዴ ከምወደው ክለቤ ወልዋሎ ጋር የሊጉን ዋንጫ አንስቶ በአፍሪካ መድረክ መሳተፍ ነው። ከዛ ቀጥሎ ደግሞ በብሔራዊ ቡድን ደረጃ መጫወት እና ውጭ ወጥቶ መጫወትም ትልቁ ዓላማዬ ነው። ከሀገር ውስጥ ጌታነህ ከበደን እያደነቅኩ ነው ያደግኩት፤ ከውጭ ደግሞ የሊዮኔል ሜሲ አድናቂ ነኝ።

በእግር ኳስ ሕወቴ ትልቅ አስተዋፅኦ ላላቸው ቤተሰቦቼ ፣ ያሰለጠኑኝ ሁሉንም አሰልጣኞች አንድነት ፀጋዬ፣ ኮማንደር ኪዳነ፣ አታክልቲ በርኸ (ወዲ ራያ)፣ ተስፋዓለም፣ ተመስገን እና ዮሐንስ ሳህሌን ማመስገን እፈልጋለሁ።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ