የአደይ አበባ ብሔራዊ ስታዲየም ቀጣይ ምዕራፍ ግንባታ በይፋ ተጀመረ

የአደይ አበባ ስታዲየም የጣራ እና የማጠቃለያ ግንባታ ዛሬ በይፋ የተለያዩ የመንግሥት አካላት በተገኙበት በይፋ ተጀምሯል ፡፡

*ሙሉ መረጃው መረጃው የኢፌድሪ ስፖርት ኮሚሽን ነው።

ለአዲስ አበባ ተጨማሪ ውበት እና ኩራት ይሆናል ተብሎ የታሰበው በአዲስ አበባ ቦሌ ክፍለ ከተማ ገርጂ አካባቢ በቻይና ስቴት ኮንስትራክሽን ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን ስራ ተቋራጭነት በMH ኢንጅነሪንግ አማካሪነት እየተገነባ የሚገኘው ብሔራዊ ስታዲየም በሁለት ምዕራፍ ተከፍሎ እየተገነባ ይገኛል። የስታዲየሙን የጣራ እና የማጠቃለያ ግንባታ የተለያዩ እንግዶች በተገኙበት ዛሬ በይፋ ተጀምሯል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የኢፊዲሪ ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ኤሊያስ ሽኩር “በሀገራችን የነበረው ብቸኛው ስታዲየም የአዲስ አበባ ስታዲየም እንደነበር ጠቁመው በአሁኑ ሰዓት በሁሉም የሀገራችን ክልሎች ከ12 በላይ ስታዲየሞች በመገንባት ላይ መሆናቸውን ገልፀዋል። እነዚህ ስታዲየሞች ተጠናቀው ለአገልግሎት እንዲበቁ አስፈላጊው ክትትል እየተደረገ ይገኛል። ከዚህ በተጨማሪም መንግስት ለስፖርት ሴክተር በሰጠው ከፍተኛ ትኩረት በከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ በአዲስ አበባ በመገንባት ላይ የሚገኘው የአደይ አበባ ስታዲም ግንባታም በተያዘለት ጊዜ እና በፍጥነት እንዲሁም በተቀመጠው የግንባታ ጥራት መሠረት እንዲጠናቀቅ መንግስት ከፍተኛ ፍላጎት አለው።” ሲሉ ገልፀዋል፡፡

የቻይና ስቴት ኮንስትራክሽን ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን ማኔጅንግ ዳይሬክተር ሚስተር ሚንግ ቾ በበኩላቸው ኩባንያቸው ግዙፍ ፕሮጀክቶችን በመስራት ከፍተኛ ልምድ ያለው መሆኑን ጠቅሰው የዓለም አቀፍ ስጋት የሆነውን የኮሮና ቫይረስ በመቋቋም ስታዲየሙን በተያዘለት ጊዜ ለማጠናቀቅ እንደሚሰሩ ተናግረዋል። የግንባታ ተቆጣጣሪ አማካሪ ድርጅት ባለቤት ዶ/ር ኢንጅነር መሠለ ህይሌ “ስታዲየሙ በአሁኑ ሰዓት ዓለም የደረሰበትን ቴክኖሎጂ ያሟላ መሆኑን እና የኦሊምፒክ እና የዓለም ዋንጫን ማስተናገድ በሚችል መልኩ ሆኖ በመገንባት ላይ መሆኑን፤ የመቀመጫ ወንበሩም እስከ 80 ሺ ሊደርስ እንደሚችል ገልፀዋል፡፡

በፕሮግራሙ ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሪዚዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ ግንባታውን በማስመልከት በሰጡት አስተያየት “ሀገራችን በአሁኑ ስዓት የካፍ እና የፊፋን መስፈርት ያሟላ ኢንተናሽናል ጨዋታዎችን ማስተናገድ የሚያስችን ስታዲየም እንደሌለ ጠቁመው ፤ የአደይ አበባ ስታዲም የዓለም ዋንጫ ፍፃሜን ማስተናገድ የሚያስችን ስታዲየም እየተገነባ መሆኑ ትልቅ ደስታን ፈጥሮልኛል።” ብለዋል ፡፡

ብሔራዊ ስታዲየሙ ከ62 ሺ በላይ ተመልካች የመያዝ አቅም ያለው ሲሆን በሁለተኛው ምዕራፍ ግንባታ የመጫወቻ ሜዳውን ሳር ማልበስ፣ የመሮጫ ትራክ ማንጠፍ፣ የስታዲየሙን ጣሪያ ማልበስና ወንበር መግጠም፣ ሰው ሰውራሽ ሀይቅ፣ የሄሊፕተር ማረፊያ፣ ዘመናዊ የደህንነት ካሜራ ፣ ሳውንድ ሲስተም፣ የፓርኪንግ አገልግሎት መስጫ ቦታዎች፣ የመለማመጃ ሜዳዎች እና ሌሎች የማጠቃለያ ስራዎች የሚያካትት ይሆናል፡፡

የ2ኛው ምዕራፍ ግንባታ ለማካሄድ እና አጠቃላይ ሥራውን ለመሥራት 900 ቀናት ይፈጃል ተብሎ ሲገመት ግንባታውን ለማከናወን ከ5.57 ቢሊዮን ብር በላይ ይፈጃል ተብሎ ይታሰባል፡፡ ለመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታ 2.47 ቢሊዮን ብር ወጪ ተደርጎበታል። በመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታ ከተካተቱት ውስጥም ከ30 በላይ የሚዲያ ክፍሎች፣ ጋዜጣዊ መግለጫ አዳራሾች፣ የክብር እንግዶች ማረፊያዎች፣ አሳንሰሮች፣ የተለያዩ ደረጃቸውን የጠበቁ ካፌዎች እና ሬስቶራንቶች ፣ ከ1000 በላይ መፀደጃ ክፍሎች፣ የፍሳሽ ማስወገጃ ፣ ኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ ተጠናቀዋል። ስታዲየሙን ሙሉ ለሙሉ ለማጠናቀቅ መንግስት ከ 8 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ይሆናል። አጠቃላይ ፕሮጀክቱም 48.8 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ ሲሆን ስታዲየሙ ብቻውን 95,000 ካሬ ሜትር ይሸፍናል ።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ