ከሰሞኑ አዲስ ሥራ አስኪያጅ በይፋ የሾመው ወላይታ ድቻ አዳዲስ ተጫዋቾችን ለቀጣዩ የውድድር አመት ከማምጣት አስቀድሞ በክለቡ ያሉ ነባር ልጆችን ውል ለማራዘም ድርድር ማድረግ የጀመረ ሲሆን ከሦስት ተጫዋቾት ጋር ቅድመ ስምምነትን መፈፀሙ ታውቋል፡፡
በክለቡ ውሉን ለማራዘም ከተስማሙት መካከል ፈጣኑ አጥቂ ባዬ ገዛኸኝ አንዱ ነው፡፡ የቀድሞው የስልጤ ወራቤ፣ ሲዳማ ቡና እና መከላከያ አጥቂ ከ2011 የውድድር ዘመን ጀምሮ ወደ ቀደም ክለቡ ወላይታ ድቻ በመመለስ መልካም የውድድር ዓመታትን ያሳለፈ ሲሆን በበርካታ የፕሪምየር ሊጉ ክለቦች ቢፈለግም ውሉን በክለቡ ለማራዘም ቅድመ ስምምነት ላይ ደርሷል፡፡
ሌላው በክለቡ ለመቆየት የተስማማው ተከላካዩ አንተነህ ጉግሳ ነው፡፡ ባለፈው የውድድር ዓመት አጋማሽ ላይ የከፍተኛ ሊጉ ክለብ ሶዶ ከተማን በመልቀቅ ወላይታ ድቻን በአንድ ዓመት ከግማሽ ውል ተቀላቅሎ የነበረው ይህ የመስመር እና የመለል ተከላካይ በክለቡ ለተጨማሪ ዓመት ቆይታን ለማድረግ ተስማምቷል፡፡
ሦስተኛው እና በክለቡ ውሉ የተጠናቀቀው በመስመር ተጫዋችነት ተሰልፎ ሲጫወት የነበረው ሁለገቡ ያሬድ ዳዊት ነው፡፡ ከወላይታ ድቻ ወጣት ቡድን ካደገ በኋላ ባለፉት አራት ዓመታት ለዋናው ቡድን ጥሩ ግልጋሎት ሲሰጥ የነበረው ተጫዋቹ ለቀጣዮቹ ዓመታት በክለቡ መለያ ዳግም ለመታየት ተስማምቷል፡፡
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!
© ሶከር ኢትዮጵያ