ወልቂጤ ከተማ የመስመር ተጫዋቹ ጫላ ተሺታን በክለቡ ለማቆየት ከስምምነት ላይ ደርሷል።
ከሰሞኑ የአሰልጣኙን እና የስድስት ተጫዋቾች ውል ለሁለት ተጨማሪ ዓመት ያራዘመው ቡድኑ በዛሬው ዕለት ከሲዳማ ቡና ወደ ወልቂጤ ከተማ በተሰረዘው ዓመት ተዘዋውሮ የቡድኑ ወሳኝ ተጫዋች መሆን የቻለው የመስመር አጥቂ ጫላ ተሺታን ውል ለሁለት ዓመታት ነው ማራዘም የቻለው።
የቀድሞው የሻሸመኔ ከተማ እና ሰበታ ከተማ ተጫዋች ጫላ ተሺታ በኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ካሳየው ድንቅ እንቅስቃሴ በኋላ በኢትዮጵያ እግርኳስ ላይ ያንፀባርቃሉ ተብለው ከሚጠበቁ ተጫዋቾች አንዱ እንደሚሆን ቢጠበቅም በሲዳማ ቡና ቆይታው ነጥሮ ለመውጣት ተቸግሮ ታይቷል። ሆኖም ዘንድሮ ወደ ወልቂጤ ካመራ በኋላ እስከተሰረዘበት ወቅት ድረስ ድንቅ የውድድር ጊዜ ማሳለፍ ችሏል። ይህን ተከትሎ ለቀጣዩ ዓመት ስሙ ከቀድሞ ክለቡ ሲዳማ ቡና ጋር ሲያያዝ ቢቆይም በወልቂጤ ለመቀጠል በዛሬው ዕለት ፊርማውን አኑሯል፡፡
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!
© ሶከር ኢትዮጵያ