የኢትዮጵያ ቡና የዝውውር እንቅስቃሴ…

“5ኛው የቡና የቤተሰብ ሩጫ”ን አስመልክቶ በተጠራው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የክለቡ የዝውውር እንቅስቃሴዎችን በተመለከተ መጠነኛ ገለፃ ተደርጓል።

የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሸን የክረምቱን የዝውውር መስኮት መስከረም 2 እከፍታለሁ ቢልም አንዳንድ ክለቦች በውስጥ ውል የተለያዩ ተጫዋቾችን እያስፈረሙ ይገኛሉ። ይህንን የሌሎች ክለቦች እንቅስቃሴን ተከትሎ የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች “እኛስ?” የሚሉ ጥያቄዎችን ከየአቅጣጫው እየሰነዘሩ ይገኛሉ። በተለይ ክለቡ ይፋዊ ባልሆነ መንገድ (በፌደሬሽኑ ስላልፀደቀ) ወሳኝ ተጫዋቾቹን እያጣ በመሆኑ ክለቡ ላይ የተለያዩ ጥያቄዎች ተነስተዋል። ይህንን ተከትሎ ዛሬ ከሰዓት በተሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይም የክለቡ አመራሮች ከጋዜጠኞች ለተነሳላቸው ዝውውር ነክ ጥያቄዎች ማብራሪያ ሰጥተዋል።

“በቅድሚያ ቀጣይ ዓመት የሃገራችን እግርኳስ መኖሩ እና አለመኖሩ አልተረጋገጠም። እርግጥ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌደሬሽን ለጤና ሚኒስቴር፣ ለህብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት፣ ለሰላም ሚኒስቴር እና ለሚመለከታቸው አካላት ጥያቄ እንዳቀረበ ሰምተናል። ግን ምላሹ እስካሁን አልታወቅ። ይህ እንዳለ ሆኖ የዝውውር መስኮቱ ገና በ2013 ነው የሚከፈተው። ይህንን ተከትሎ ክለባችን እስካሁን ምንም እንቅስቃሴ አላደረገም። ምክንያቱም በፌደሬሽኑ ፊት ያልቀረበ ስምምነት ህጋዊ ስላልሆነ። ይህ ቢሆንም ግን ከነባር ተጫዋቾቻችን ጋር እየተወያየን ነው። በዜናም ጭምር ወደ ሌሎች ክለቦች ተዘዋውረዋል ከተባሉትም ጋር። ግን በቲቪ ማሊያ ለብሰህ ስለታየህ ተዘዋውረሃል ማለት አይደለም። ግዴታ ውሉ ህጋዊ እንዲሆን በፌደሬሽን ፊት ውሉን ማፅደቅ አለብህ።” ሲሉ አቶ ገዛኸኝ ወልዴ ገልፀዋል።

ከብዙሃን መገናኛዎች ከመጡ ጋዜጠኞች የዝውውር ሁኔታውን በተመለከተ ጥያቄ የበዛባቸው መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ በተከታይነት ከአቶ ገዛኸኝ በመቀጠል የክለቡን አሁናዊ የዝውውር ሂደት እና ቁመና በተጨማሪነት አስረድተዋል።

“ኢትዮጵያ ቡና እስካሁን ዝውውር አልጀመረም። በተለያዩ ቦታዎች የሚወሩት ወሬዎች ሃሰተኛ ናቸው። በተለይ ‘ቡና አዳዲስ ተጫዋቾችን ሲያስፈርም ደሞዝ እያስቀነሰ ነው’ የሚለው ውሸት ነው። ሲጀምር 60/40 የሚለውን የደሞዝ አከፋፈል ያደረግነው ከነባር ተጫዋቾቻችን ጋር በመነጋገር ነው። አዲስ ተጫዋቾቸ ይህ አይመለከታቸውም። ነባሮቹንም ደሞዝ በስምምነት እንዲቀንሱ ያደረግነው ክለቡ አደጋ ላይ ስለነበር እና ተጫዋቾቹ በክለቡ ህልውና ላይ አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ስለተስማማን ነው።” ብለዋል።

መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞ የምክትል አሰልጣኞችን በተመለከተ ለተነሳላቸው ጥያቄም ተከታዩን ማብራሪያ ሰጥተዋል።

“ኢትዮጵያ ቡና ክለብ ውስጥ ያለ ማንኛውም ግለሰብ ብቃቱ በየጊዜው ይገመገማል። ማንኛውም ሰው ያለው ክህሎት እና አበርክቶ በተለያዩ ጊዜያት ይታያል። ይህንን ተከትሎ አሰልጣኞቻችን ላይም ተመሳሳይ ነገር ይከናወናል። ብቃት ያላቸው ከእኛ ጋር ይቀጥላሉ፣ ብቃት የሌላቸው ግን ክለቡን እንዲለቁ ይደረጋል። ስለዚህ አሁን ካሉት ምክትሎች የሚለቁ ሊኖሩ ይችላሉ። አዲስም ሊመጣ ይችላል።” በማለት ሃሳባቸውን አገባደዋል።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ