የሴቶች ገጽ | ያልተኖረው የብዙዓየሁ ህልም

ብዙ ህልሞች የነበሯትን እና ከ11 ዓመቷ ጀምሮ ብቻዋን ለመኖር የተገደደችው ብዙዓየሁ ጀምበሩን የእግርኳስ ህይወት በዛሬው የሴቶች ገፅ አምዳችን እናቀርብላችኋለን።
በድሬዳዋ ከተማ ውልደቷን እና እድገቷን ያደረገችው ብዙዓየሁ ጀምበሩ ኳስን ከ6 ዓመቷ ጀምሮ ስትጫወት ነበር። በተለይ በተወለደችበት ድሬዳዋ አካባቢ የእንስት ቡድኖች ስላልነበሩ ኳስን በፆታ ከማይመሳሰሏት ወንዶች ጋር መጫወት ያዘች። እስከ 11 ዓመቷ ድረስም ቤታቸው አካባቢ በሚገኘው አሸዋ ሜዳ በግሏ ወንዶችን እየተለማመጠች እና እየለመነች ከተጫወተች በኋላ 11 ዓመቷ ላይ ወደ ወንዶች ፕሮጀክት ገባች።
“መኖሪያ ቤታችን ትላልቅ ተጫዋቾችን ያፈራው አሸዋ ሜዳ አካባቢ ነበር። ከጎል ጀርባ እየተቀመጥኩ የተጨዋቾቹን አጨዋወት ገና በልጅነቴ አጠና ነበር። እነሱንም ለማስመሰል እሞክር ነበር። በተለይ ዮርዳኖስ አባይ ልዩ ተምሳሌቴ ነው። ሜዳ ላይ የሚያደርጋቸውን እያንዳንዱን ነገሮች ለመኮረጅ እጥር ነበር። እግርጥ ዮርዳኖስ ለእኔ ብቻ ሳይሆን ለብዙ የድሬዳዋ ወጣቶች አርዓያ ነበር። በእግርኳስ ችሎታው ብቻ ሳይሆን በስብዕናውም ዮርዳኖስ ብዙዎቻችንን ገዝቶናል። የሆነው ሆኖ እግርኳስ ተጫዋች እግርኳስን መጫወት መጀመር ባለበት እድሜ ነው መጫወት የጀመርኩት። ከስድስት ዓመቴ ጀምሮ ማለቴ ነው። እውነት ለመናገር ኳስ በጣም እችል ነበር። ቄንጠኛ ተጫዋችም ነበርኩ። ይህንን ደሞ የሚያውቁኝን ሰዎች ጠይቀክ መረዳት ትችላለክ። እስከ 11 ዓመቴ ድረስ በግሌ እየተጫወትኩ ከቆየሁ በኋላ አመሃ መኩሪያ እና ኃይሉ ገብረፃዲቅ የሚባሉ አሰልጣኞች ጋር ሄድኩ። እነሱ የሚያሰሩት ወንዶችን ነው ግን አማራጭ ስላልነበረኝ እነሱ ጋር መሰልጠን ቀጠልኩ። ‘ከወንዶች ጋር መጫወት አትችይም’ እንዳልባል ልምምድ በጣም ነበር የምሰራው። በተለይ የአካል ብቃት ስራዎችን በግሌ እሰራ ነበር። ከዛን ከ13 እስከ 17 ዓመት በታች ቡድኖች ውስጥ በፕሮጀክት ደረጃ ሰለጠንኩ።”

ራሷን ከወንዶች ጋር እያፎካከረች ሀፍካት የተባለ የሴቶች ቡድን ውስጥ ጎን ለጎን መስራት የጀመረችው ተጫዋቿ ህይወቷን ወደ ሌላ ጎዳና የሚወስድ መጥፎ አጋጣሚ ገና በአፍላ እድሜዋ አጋጥሟት እንደነበረ ታወሳለች።

“ቤት ውስጥ ብቸኛ ልጅ ስለነበርኩ የምፈልገውን ነገር አልከለከልም ነበር። እንደፈለኩ ኳስ እጫወት ነበር። ግን ገና በጊዜ ህልሜን የሚያሰናክሉ ነገሮች አጋጠሙኝ። ወላጅ አባቴ የከባድ መኪና ሹፌር ነበር። እናቴ እና እኔ ጋር ከስንት አንድ ጊዜ ነበር የሚመጣው። 8 ዓመቴ ላይ እያለሁ ግን እቤት መቶ ከእናቴ ጋር ከባድ ፀብ ውስጥ ገባ። በዛ ፀብ የተነሳ ከቤት እንደወጣ አልተመለሰም። አሁንም ድረስ ወላጅ አባቴ በህይወት ይኑር አይኑር የማቀው ነገር የለም። ከ3 ዓመታት በኋላ ደግሞ ወላጅ እናቴን በሞት አጣሁኝ። እነዚህ ነገሮች ተደራርበውብኝ የህልም መስመሬን ሊያስቱኝ ነበር። በተለይ አካባቢዬ ማንም ሰው አለመኖሩን ተከትሎ ተስፋ ብቆርጥ ኖሮ አሁን የድሬዳዋም ሆነ የኢትዮጵያ ህዝብ አያቀኝም ነበር። ግን እኔ ኑሮዬን ብቻዬን አድርጌ ኳስ እና ትምህርቴን አልተውኩም።”

በቀለም ትምህርቷም ገፍታ የቀጠለችው ይህቺ ህልመኛ ታዳጊ በኢትዮጵያ ሻምፒዮና የመመረጡን እድል በማግኘት የብዙዎችን ቀልብ መግዛት ጀመረች። በተለይ በውድድሩ ላይ ኮከብ ግብ አግቢ በመባል በመመረጥ የኢትዮጵያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን ውስጥ የመካተቱን እድል አገኘች። ከኮከብ ግብ አስቆጣሪነት በተጨማሪ ኮከብ ተጫዋች በመባል ሽልማቶችን መውሰድ ቻለች።

“ኢትዮጵያ ሻምፒዮና ስጫወት እድሜዬ ከ16 አይዘልም ነበር። ቶሎ ወደ እግርኳሱ ስለገባው ገና በለጋነቴ ነው ኮከብነትን ያገኘሁት። በዚህም መነቻነት ብዙዎች ተስፋ ጥለውብኝ ነበር። ኢትዮጵያ ሻምፒዮና ላይ ከመጫወቴ በፊት ደሞ በትምህርት ቤት ውድድሮች ላይ ከ4ኛ ክፍል ጀምሮ እስከ 9ኛ ክፍል ድረስ ተጫውቻለሁ። በየውድድሮቹም ኮከብ ግብ አግቢ እና ኮከብ ተጫዋች በመባል ተመርጫለሁ። በተለይ ሽልማቱ የመማሪያ ደብተር እና እስክርቢቶ ስለነበረ እሱን ለማግኘት እጥር ነበር። ምክንያቱም በጊዜው የሚገዛልኝ ሰው ስላልነበረ ሽልማቱን እንደ ‘ባሎን’ዶር’ በመቁጠር እዘጋጅ ነበር። ግን ገና 20 ዓመት ሳይሞላኝ ለጉዳት እጄን ሰጥቼ የምወደውን ኳስ ተሰናበትኩ።”

ባጋጠማት ጉዳት ኳስን የተሰናበተችው ይህቺ ተጫዋች በጊዜው ያጋጠማትን ጉዳት መለስ ብላ ታጫውተናለች።

“እንዳልኩት ጉዳት የገጠመኝ ገና 20 ዓመት ሳይሞላኝ ነው። በትምህርትም 10ኛ ክፍል ማትሪክ ልወስድ አካባቢ ነው የተጎዳሁት። ቀድሜ እንደገለፅኩት ወንድምም ሆነ እህት የለኝም። እናቴንም ገና በ11 ዓመቴ ስላጣሁ የሚያስታምመኝ እንኳን አልነበረም። በነገራችን ላይ ያጋጠመኝ ጉዳት በቀላሉ የሚታከም ነበር። ግን የሚረዳኝ ስላልነበረ እራሴው በውስጤ እያስታመምኩት ቆየሁ። የመጀመሪያው የቁርጭምጭሚት ጉዳቱ የደረሰብኝ የትምህር ቤት ውድድር ላይ ስጫወት ነው። በጉዳቱም ምክንያት በየአመቱ የምሳተፍበት ውድድር ላይ ልቀር ሆነ። ከምንም በላይ ደሞ የለመድኩትን ደብተር እና እስክርቢቶ ማጣቴን ሳስብ ተብሰከሰኩ። በጊዜው የመማሪያ መሳሪያ ብቻ ሳይሆን የምለብሰውም የትምህርት መለያ(ዩኒፎርም) መቀየር ስለነበረበት ሁሉ ነገር በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆነብኝ። ይህ ነገር ለሌላው ሰው ትንሽ ቢሆንም ለእኔ ግን ትምህርቴት ለማቋረጥ ከበቂ በላይ ነበር። እንደአጋጣሚ ሆኖ ግን አንድ ከጅቡቲ የመጣ አድናቂዬ ስለእኔ ጠይቆ እና አጠያይቆ በውድድሩ ብሰለፍ ኖሮ የምሸለመውን የትምህርት መሳሪያ እና ዩኒፎርም ገዝቶ በስጦታነት አበረከተልኝ። ከዛም ትምህርቴን ቀጥዬ 10ኛ ክፍል ደረስኩ። ቀድሜ እንደገለፅኩት በዚህ ሰዓት በኢትዮጵያ ሻምፒዮና እና በብሄራዊ ቡድን የመመረጡን እድል አግኝቼ ነበር። ማትሪክንም 2.8 አግኝቼ ወደ ቀጣይ ክፍል የማለፉን እድል አገኘሁ። ግን በቀላሉ መታከም የሚችለው ጉዳት ዳግም በብሄራዊ ቡድን ልምምድ ስሰራ ተባብሶ ለ6 ወራት ከቤት እንዳልወጣ አደረገኝ። ጉዳቱ በጣም ከባድ ነበር። የሚረዳኝ እና የሚያስታምመኝም ስላልነበረ ብቻዬን ከብዶኝ ነበር። እንደውም የድሬዳዋ ህዝብ መካከል ጥሩ የመረዳዳት ባህል ስለነበረ ደግፎኝ ነው እንጂ ከዚህም በላይ ጊዜው አስከፊ ነበር። ግን ቢሆንም በቅርቡ አይዞሽ የሚለኝ ስላልነበረ በጣም ነበር ስሜቴ የተጎዳው። ከ1-10 እየወጣሁ የቀጠልኩት የቀለም ትምህርቴንም ወደ 11ኛ ክፍል በመግባት ማስቀጠል ተሳነኝ።”

በቀላሉ ሊታከም የሚችለው ጉዳት እየተባባሰ ሄዶ እቤት ያስቀመጣት ይህቺ የ20 ዓመት ኮከብ እንደምንም መደገፊያ (ክራንች) እየያዘች የቀለም ትምህርቷን ማስቀጠሏን ትናገራለች።

“ጉዳቱ ከተባባሰብኝ በኋላ እንደልቤ መንቀሳቀስ ባለመቻሌ ለ3 ዓመታት በመደገፊያ እንጨት(ክራንች) ነበር የምሄደው። ኢያሱ መርሃፅድቅ እና ወገኔ ዋልተንጉስ የሚባሉ ሰዎች ያለኝን ነገር ያውቁ ስለነበር በግላቸው ኮተቤ የስፖርት ሳይንስ ያስተምሩኝ ነበር። እዛም ህመሜን በውስጤ ችዬ ለ1 ዓመት ከ3 ወር ተማርኩ። ግን የማያቀኝ እና የማላቀው ከተማ ላይ መማር ከበደኝ እና ወደ ድሬዳዋ ተመለስኩ። ድሬም መጥቼ እየወደኩ እና እየተነሳው ፋርማሲ በዲፕሎም ደረጃ ተምሬ ጨረስኩ። የተመረኩትም ከነክራንቼ ነበር።ግን እኔ ህይወቴን ሳስቀጥል ጉዳቱ ውስጥ ውስጡን እየተባባሰ ሄዶ እጅ እንድሰጥ አደረገኝ። ከዛም ብዙ ሰዎች ተረባርበው እንድታከም ሆነ።”

ገና በታዳጊ እድሜዋ የነበራትን ብቃት እና ቅልጥፍና ተከትሎ ብዙዓየሁ በ2 የተለያዩ ጊዜያት ለብሔራዊ ቡድን ምርጫ ተደርጎላታል። ነገርግን በእግሯ ላይ ባጋጠማት ጉዳት ምክንያት ተጫዋቿ ግልጋሎት ሳትሰጥ ቀርታለች። እንደውም ብዙዓየሁ ኢትዮጵያ ከእሷ ማግኘት የነበረባትን ነገር እንዳላገኘች በቁጭት ታወሳለች።

“ኢትዮጵያ ከእኔ ማግኘት የሚገባትን ነገር አላገኘችም። እኔም ለሃገሬ ማድረግ የሚገባኝን ሳላደርግ ቀርቻለሁ። ይህንን ስል እየተመፃደቁ አደለም። የማስበውን እና ብዙዎች የሚሉኝን ነው የምነግርክ። ግን ተጎዳው። የሚገርምህ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ የነበሩት አቶ አዳነ(ከአሸናፊ በቀለ ጋር በጋራ በመሆን) ከእኔ በላይ በደረሰብኝ ጉዳት አዝነዋል። በየአመቱ ድሬዳዋ ይመጡ ስለነበር ብቃቴን ይከታተሉ ነበር። ጉዳት ደርሶብኝ እራሱ ‘ትንሽ ደቂቃ ልጠቀምብሽ’ ብለውኝ ሊወስዱኝ ሁሉ ነበር። ግን ሙሉ ጤነኛ ስላልነበርኩ አልሆነም። ለ2 ጊዜያት ምርጫ ቢደረግልኝም በጉዳቴ ምክንያት መጫወት ሳልችል ቀረሁ።”

ውጣ ውረዶችን ገና በታዳጊ እድሜዋ ያሳለፈችው ብዙዓየሁ ህልሟን መኖር ቢሳናትም አሁን ላይ ወደ አሰልጣኝነት ህይወት በመግባት የትውልድ ከተማዋብ(ድሬዳዋ) የሴቶች ቡድን በዋና አሰልጣኝነት እየመራች ትገኛለች። በሃገሪቱ የሴቶች ከፍተኛ የሊግ እርከን ውስጥ የሚገኘውን ድሬዳዋ ከተማን 2011 ላይ ማሰልጠን ከጀመረችበት ጊዜ በፊት ያሳላፈችውን የአሰልጣኝነት ቆይታም እንዲህ አጫውታናለች።

“ታክሜ ከመጣሁ በኋላ የሲ(C) ላይሰንስ ለማውጣት አመት አልፈጀብኝም። ወዲያው ነው ያወጣሁት። ልክ ሰርጀሪው ከተሰራልኝ ከ9 ወር በኋላ በግሌ የ11 እና 12 ዓመት ሴት ታዳጊዎችን ሰብስቤ ማሰራት ጀመርኩ። ከታች መጀመር የፈለኩትም ትክክለኛ ባለሙያ ስለሆንኩ ነው። ተመልካቹም ሆነ ባለሙያው በታዳጊዎች ላይ ‘ተቺ’ ስለሆነ እኔ ወርጄ መጀመር እንዳለብኝ በማመን ስራ ጀመርኩ። እንድታከም ድጋፍ ካደረጉልኝ ውጪ ከሚገኙ የቀድሞ ተጫዋቾቸ ጋር በመተባበር 30 የሚጠጉ ታዳጊዎችን ይዤ የሴቶች ፕሮጀክት አቋቋምኩ። በዚህም ለ4 ዓመታት በበጎ ፍቃደኝነት 2 ዓመታት ደሞ በትንሽ ክፍያ በአጠቃላይ ለ6 ዓመታት በፕሮጀክቱ ታዳጊዎችን ለማብቃት ሞከርኩ። ከዛ በኋላ ድሬዳዋ ከተማ የሴቶች ቡድን ውስጥ ልፋቴን እና አመጣጤን አይተው ደውለው ጠርተው አነጋገሩኝ። ከዛም ተስማምተን ከ2011 ጀምሮ እስካሁን በድሬዳዋ ከተማ የሴቶች ቡድን ውስጥ እያሰለጠንኩ እገኛለሁ።”

የፍቅር ጓደኛ እንዳላት የተናገረችውና በሚቀጥለው ዓመት ለመሞሸር ሽር ጉድ እያለች የምትገኘው ብዙዓየሁ በተጫዋችነት ዘመኗ እንዳለመችው ክብሮችን ማግኘት ባትችልም ወደፊት በአሰልጣኝነት ሙያዋ ሃገሯን ማገልገል እንደምትሻ ትናገራለች። ከሃገር ወጥታም በትልቅ ደረጃ ክለብ ይዛ ማሰልጠን ፍላጎቷ እንደሆነ ሳትሸሽግ ነግራናለች።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ