ወልዲያ እግርኳስ ክለብ በአስተዳደራዊ ችግር ምክንያት በሊጉ በተረጋጋ ሁኔታ መጓዝ እየተሳነው ይገኛል።
ወልድያ ከከፍተኛ ሊግ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ካደገበት ያለፈው የውድድር አመት ጀምሮ ከሜዳ ውጪ በተወሰሰቡ ችግሮች ቢከበብም በሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ለተጋጣሚ ቡድን ፈተኝ በመሆን በደረጃ ሰንጠረዡ ወገብ ላይ ማጠናቀቁ የሚታወስ ነው። በዘንድሮ አመት የአሰልጣኝ ለውጥ በማድረግ አሰልጣኝ ዘማርያም ወ/ጊዮርጊስን ዋና አሰልጣኝ አድርጎ የሾመው ክለቡ የነበረበትን ጉድለቶች ለመሙላት በሚል ከፍተኛ ሂሳብ በማውጣት በፕሪምየር ሊጉ ልምድ ያላቸው በርከት ያሉ ተጨዋቾችን በማስፈረም ክለቡን ለማጠናከር ከፍተኛ ስራ ቢሰራም ከሜዳ ውጭ ያልተረጋጋ ጉዞ የጀመሩት ገና በቅድመ ዝግጅት ውድድር ጊዜ ከተጨዋቾች ጋር የተስማሙትን ቅድመ ክፍያ በጊዜው ባለመፈፀማቸው ምክንያት ተጨዋቾች ልምምድ ሲያቋረጡ ነበር።
በወቅቱ የተፈጠረውን አለመግባባት ከተጨዋቾቹ ጋር በመደራደር ችግሩ እልባት አግኝቶ የቀጠለ ቢመስልም ችግሮቹ አሁንም የመፈታት ነገር እያሳዩ አይገኙም።
አሁን የተሰማ ያለው ወቅታዊ መረጃ ደግሞ የቡድኑ ምክትል አሰልጣኝ ኃይማኖት ግርማ በደሞዝ ክፍያ ምክንያት ከቡድኑ የተለያዩ ሲሆን አሰልጣኝ ዘማርያም በ5ኛ ሳምንት በሜዳቸው ከመቐለ ከተማ ጋር በሚያደርጉት ጨዋታ ቡድኑን በብቸኝነት የሚመሩ ይሆናል። ሶከር ኢትዮዽያ ለጉዳዪ ቅርበት ካላቸው ምንጮች እንደተረዳቸው ከሆነ ምን አልባትም የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ዘማርያም ወ/ጊዮርጊስ ክለቡ እሁድ ከመቐለ ከተማ ጋር ከሚያደርገው ጨዋታ በኋላ የረዳት አሰልጣኛቸውን ፈለግ ተከትለው ቡድኑን ጥለው ሊሄዱ ይችላሉ። ይህ የሚሆን ከሆነ ደግሞ የግብ ጠባቂ አሰልጣኙ ይልማ ከበደን ጭምር በድንገተኛ ህመም ያጣው ወልዲያ ያለ አሰልጣኝ ቡድን የመቀጠል ፈተና ተጋርጦበታል።