የጣና ሞገዶቹ የተጫዋቾቻቸውን ውል ማደስ ቀጥለዋል

ከሳምንት በፊት የተጫዋቾቻቸውን ውል ማደስ የጀመሩት ባህር ዳር ከተማዎች ዛሬ ረፋድም የመስመር ተጫዋቻቸውን ውል ለማደስ ተስማምተዋል።

የአሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝን ውል በማደስ የቀጣይ ዓመት ስራቸውን የጀመሩት ባህር ዳሮች በዚህ ሳምንት የተጨዋቾቻቸውን ውል ማደስ ላይ ተጠምደው ሰንብተዋል። የክለቡ የበላይ አመራሮችም ትላንት ማምሻውን ወደ አዲስ አበባ በመምጣት በመዲናዋ እና አካባቢዋ የሚገኙ ነባር ተጨዋቾቻቸውን ለማቆየት ንግግር ጀምረዋል። ዛሬ ረፋድም የክለቡ አመራሮች ከፈጣኑ የመስመር አጥቂ ወሰኑ ዓሊ ጋር ንግግር በማድረግ የተጫዋቹን ውል ለተጨማሪ 2 ዓመታት ለማደስ ከስምምነት ደርሰዋል።

ከኢትዮጵያ መድን ባህር ዳርን በመቀላቀል የእግር ኳስ ህይወቱን የቀጠለው ወሰኑ ባህርዳሮችን ከከፍተኛ ሊግ ጀምሮ ሲያገለግል መቆየቱ ይታወቃል። በተለይ በአሰልጣኝ ጻውሎስ ጌታቸው ስብስብ ውስጥ ተጫዋቹ ጉልህ ድርሻ ኖሮት ሲጫወት ቆይቷል። ይሁንና መሰረዙ በታወቀው የ2012 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውድድር ላይ ግን ተጫዋቹ ጉዳት በማስተናገዱ ለበርካታ ጊዜያት ከሜዳ ርቆ ቆይቷል።

የጣና ሞገዶቹ ከዚህ በፊት የፍቅረሚካኤል ዓለሙ፣ የዜናው ፈረደ፣ የደረጄ መንግስቱ፣ የኃይለየሱስ ይታየው እና የአቤል ውዱን ውል ለተጨማሪ 2 ዓመታት ማደሳቸው አይዘነጋም።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ