ድሬዳዋ ከተማ አማካይ ሲያስፈርም የሁለት ተጫዋቾችን ውል አራዝሟል

በትናንትናው ዕለት ወደ ገበያው የገባው ድሬዳዋ ከተማ ዛሬም እንቅስቃሴውን ቀጥሎ የወሳኝ ተከላካዩ በረከት ሳሙኤል እና የግብ ጠባቂው ፍሬው ጌታሁን ውልን ለተጨማሪ ዓመት ሲያራዝም ሱራፌል ጌታቸውን ወደ ክለቡ መልሷል።

ወደ ክለቡ ለመቀላቀል የተስማማው ተጫዋች ያለፉትን ሁለት የውድድር ዓመታት ከሀድያ ሆሳዕና ጋር ያሳለፈው ሱራፌል ጌታቸው ነው። ከሙገር ሲሚንቶ የተገኘው ሱራፌል ከሙገር መፍረስ በኋላ በአዲስ አበባ ከተማ፣ ጅማ አባ ቡና እና አዳማ ከተማ አጫጭር ጊዜያትን ያሳለፈ ሲሆን ሀዲያ ሆሳዕና ወደ ፕሪምየር ሊግ በድጋሚ ሲያድግም ወሳኝ ሚና ተጫውቷል። በአንድ ዓመት ውል ክለቡን የተቀላቀለው አማካይ ሥፍራ ተጫዋቹ ከአስጨናቂ ሉቃስ በመቀጠል ሁለተኛ ፈራሚም ሆኗል።

ከክለቡ ጋር ውል ያራዘሙት ተጫዋቾች ከሙገር ሲሚንቶ በ2008 ክለቡን ተቀላቅሎ ላለፉት አራት ዓመታት ቡድኑን በቋሚነት ያገለገለው ግዙፉ ተከላካይ በረከት ሳሙኤል እና ከሁለት ዓመት በፊት ከአርሲ ነጌሌ ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ አምርቶ በመቀጠል ደግሞ በ2011 ወደ ድሬዳዋ ተቀላቅሎ በተለይ ባለፈው የውድድር ዓመት በበርካታ ጨዋታዎች ላይ ቡድኑን ያገለገለው ግብ ጠባቂው ፍሬው ጌታሁን ነው።


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ