አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ለሁለት የውድድር ዘመናት ከቆየበት አርባምንጭ ከተማ ጋር ተለያይቷል።
ለአርባምንጭ ጨርቃ ጨርቅ፣ ኢትዮጵያ ቡና፣ አየር ኃይል እና ጥቁር ዓባይ የተጫወተ ሲሆን በአሰልጣኝነት ህይወቱን አርባምንጭ ዳሽን የጀመረው መሳይ በፕሪምየር ሊጉ ወላይታ ድቻ እና ፋሲል ከነማን አሰልጥኖ ያለፉትን ሁለት ዓመታት በከፍተኛ ሊግ በሚገኘው በአርባምንጭ ከተማ ሲሰራ መቆየቱ ይታወቃል። በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ሊጉ ተሰረዘ እንጂ በዘንድሮ ዓመት አርባምንጭን ዳግም ወደ ፕሪምየር ሊጉ ለመመለስ ተቀራርቦ እንደነበረም ይታወሳል። የኮንትራት ዘመኑ መጠናቀቁን ተከትሎ የክለቡ አመራሮች ለቀጣይ ዓመታት ከቡድኑ ጋር እንዲቆይ ፍላጎት ቢኖራቸውም አሰልጣኝ መሳይ ወደ ፕሪምየር ሊግ ክለብ ለማምራት በማሰብ ውሉን እንደማያራዝም በመግለፁ ከአርባምንጭ ጋር መለያየቱን ተናግሯል። ይህን አስመልክቶ አሰልጣኝ መሳይ ለሶከር ኢትዮጵያ ይህን ተናግሯል።
” አርባምንጭን ወደ ፕሪምየር ሊጉ ለመመለስ የቡድኑ አመራሮች፣ ተጫዋቾች እና ደጋፊዎች በጋራ በሆነን እየሰራን ነበር። የዕድል ጉዳይ ሆኖ በኮሮና ምክንያት ህልማችን ሳይሳካ ቀርቷል። በቡድኑ እንድቆይ አመራሮቹ ፈልገው የነበረ ቢሆንም ራሴን ለሌላ የፕሪምየር ሊግ ክለብ ለማዘጋጀት አስቤለው። በቅርቡ በየትኛው የፕሪሚየር ሊግ ክለብ እንደማሰለጥን ድርድሩ ሲጠናቀቅ አሳውቃለው። አርባምንጭ በነበረኝ ቆይታ ለተጫዋቾቹ ለቡድኑ አባላት እና አመራሮች ልባዊ ምስጋና አቀርባለሀሀ።” ብሏል።
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!
© ሶከር ኢትዮጵያ