የውጭ ሀገር ግብጠባቂዎች በሊጋችን እና ከውጭ በሚመጡ አሰልጣኞች ዙርያ ከኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ ጋር አጭር ቆይታ አድርገናል።
የውጭ ሀገር ዜግነት ያላቸው ግብጠባቂዎች በሀገራችን ሊግ እንዳይኖሩ በማሰብ ፌዴሬሽኑ የዝውውር መመርያን አውጥቶ ክለቦች እስከ ነሐሴ ሰባት ቀን ድረስ ምላሽ እንዲሰጡበት ቀጠሮ መያዙ ይታወቃል። ይህ ሀሳብ ለሀገራችን ግብጠባቂዎች ያለውን ፋይዳ፣ ያሳደረውን ተፅዕኖ አስመልክቶ እና የውጭ ሀገር አሰልጣኞች ለሊጋችን ያስፈልጋሉ ወይስ አያስፈልጉም በሚሉ ጉዳኞች ዙርያ ሙያዊ አስተያየት እንዲሰጡን የካፍ ኤሊት ኢንስትራክተር ከሆኑት አብርሀም መብራቱ ጋር አጠር ያለ ቆይታ አድርገናል እንዲህ አቅርበነዋል።
“በግብጠባቂዎች በኩል ያለኝ ሀሳብ እኔ ብሔራዊ ቡድን ላይ የሚፈጥረውን ተፅእኖ ስላለ ቢቻል ለሀገር ውስጥ ግብጠባቂዎች ብቻ ዕድሉ ቢሰጥ መልካም ነው፤ ከብሔራዊ ቡደን ግንባታ አንፃር። አንደኛ የሀገር ውስጥ ግብጠባቂዎች የተሻለ ደረጃ ደርሰው ጥሩ ግብጠባቂዎች እንዲሆኑ እና በሀጉራዊ ውድድር ተፎካካሪ እንዲሆኑ ሥራዎች መሰራት አለባቸው። በተለይ ወደ እዚህ ሀገር ከመጣው በኃላ የታዘብኩት የግብጠባቂ አሰልጣኞች ስልጠና ደረጃውን ጠብቆ እየተሰጠ አይገኝም። ብዙ ጊዜ ተለምዷዊ የሆነ አሰራር አለ። ተጫውቶ ያለፈ ግብጠባቂ ልምድ አለው በሚል ብቻ በእውቀት በትምህርት ሳይደገፍ አሰልጣኝ የሚሆኑበት ሁኔታ አለ። ይህ መስተካከል አለበት። የግብጠባቂዎች አሰልጣኝን መሠረት ያደረገ ስልጠናዎች በስፋት በቀጣይ መሰጠት አለበት። በተደጋጋሚ ይህን ለማድረግ ያደረግነው ጥረትም ለጊዜው አልተሳካም። አሁን ፌዴሬሽኑ የሀገር ውስጥ ግብጠባቂዎች ብቻ በሊጋችን እንዲሆኑ ያዘጋጀው መመርያ መልካም ሆኖ ሳለ ለክለቦቻችን የእፎይታ ጊዜ ሊሰጣቸው ይገባል። ይህ ማለት የሚቀጥለው ዓመት የውጭ ግብጠባቂ አትጠቀሙ ከማለት ክለቦች የተወሰነ ጊዜ ተሰጥቷቸው የውጭ ሀገር ግብጠባቂዎች ኮንትራት ካለባቸው እንዲጨርሱ፣ የሀገር ውስጥ ግብጠባቂዎችን በስነ ልቦና በአካል ብቃትም አዘጋጅተው እንዲሁም ፌዴሬሽኑ ተረባርቦ ከውጭ ሀገር በሚመጡ አሰልጣኞች ብቁ የሆኑ በትምህርት የታገዘ የግብጠባቂዎች አሰልጣኞችን ማዘጋጀት ቢቻል። ሌላው አስገዳጅ ህግ ወጥቶ ዋና እና ም/አሰልጣኝ ክለቦች እንደሚኖሯቸው ሁሉ ሁሉም ክለቦች በጀት መድበው የግብጠባቂ አሰልጣኞች ሊኖራቸው ይገባል። የቀጠሯቸውን የግብጠባቂዎች አሰልጣኝን ደግሞ በእውቀት ማስተማር፣ በስልጠና የማብቃት ስራ መስራት አለባቸው። የአንድ ቡድን ውጤት 50% ግብጠባቂ ነው። ግብጠባቂዎች አንድ ሆነው ውጤት ሲቀይሩ አይተናል። ስለዚህ ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል። የውጭ ሀገር ግብጠባቂዎች ባይኖሩ ጥሩ ነው ብዬ ሙያዊ ሀሳቤን አካፍላለው።
“በሊጋችን የውጭ ሀገር አሰልጣኞች መኖር ላይ ብዙ ችግር የለኝም። የሚመጡት አሰልጣኞች የተሻለ እውቀት እና አቅም ካላቸው ተጫዋቾች ከፍተኛ ልምድ ያገኛሉ። እኛም አሰልጣኞች የእውቀት ሽግግር እናደርጋለን። በሌሎች ሀገሮች እንደሚሰራበት አንድ የውጭ አሰልጣኝ በክለብም ሆነ በብሔራዊ ቡድን ሲመጣ የተለያዩ አውደ ጥናቶች ይዘጋጁና የእውቀት ግብይቶች፣ የልምድ ልውውጦች ይካሄዳሉ። እኛ ሀገር ስትመጣ ይህ አይደረግም። የውጭ ሀገር አሰልጣኞች ይመጣሉ ምንም የተለየ ነገር ሳይሰሩ ወደ ሀገራቸው ይመለሳሉ። እንኳንስ አውደ ጥናት ተዘጋጅቶ ይቅርና! ያላቸውን እውቀት ለመካፈል አንዳንድ አሰልጣኞች በግል ቀርበው እንኳን አይጠይቋቸውም። ምንም እንኳን ለአንድ ክለብ አሰልጣኝነት ቢመጡም እንደ ሀገር የምንጠቀምበት እድል መመቻቸት አለበት። አለበለዚያ የሁለት ሰዓት ልምምድ ሰዎች ብቻ፣ የዘጠና ደቂቃ ጨዋታ ሰዎች ብቻ ከሆኑ ምን ያደርጋል። የሃያ አራት ሰዓት የእግርኳስ ልማት ሰዎች እንዲሆኑ ማድረግ ያስፈልጋል።”
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!
© ሶከር ኢትዮጵያ