ሀዲያ ሆሳዕናዎች ሦስት ተጫዋቾች በማስፈረም ወደ ዝውውሩ ገብተዋል

አዲስ አሰልጣኝ የቀጠሩት ሀዲያ ሆሳዕናዎች ሦስት ተጫዋቾች ለማስፈረም ተስማምተዋል።

ከቀናት በፊት አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለን በዋና አሰልጣኝነት የቀጠሩት ነብሮቹ የአዳማ ከተማ ተጫዋቾች የነበሩት በረከት ደስታ፣ አዲስ ህንፃ እና ቴዎድሮስ በቀለን ነው ወደ ቡድናቸው የቀላቀሉት።

ከአዳማ ሁለተኛ ቡድን ካደገ በኃላ የክለቡ ወሳኝ ተጫዋች ለመሆን ጊዜ ያልወሰደበት በረከት ደስታ ባለፉት ሦስት ዓመታት የአዳማ ወሳኝ ተጫዋች መሆን ችሎ ነበር። ፈጣኑ የመስመር ተጫዋች ሆሳዕናን መቀላቀሉን ተከትሎ ከቀድሞ አሰልጣኙ ጋር በድጋሚ የመስራት ዕድል አግኝቷል።

ሌላው ሆሳዕናን የተቀላቀለው አማካዩ አዲስ ህንፃ ነው። በኢትዮጵያ መድን በአጥቂነት እግርኳስን የጀመረው አዲስ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ደደቢት ራሱን አጎልብቶ የብሔራዊ ቡድኑ ወሳኝ ተጫዋች መሆን ችሎ የነበረ ሲሆን ከአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎ መልስ በሱዳኑ ሒላል ሸንዲ የሦስት ዓመታት ቆይታ አድርጎ በመመለስ ለአዳማ ከተማ ሲጫወት ቆይቷል።

ሌላኛው የቡድኑ አዲስ ፈራሚ ቴዎድሮስ በቀለ ነው። የቀድሞው ሁለገብ የመከላከያ የተከላካይ መስመር ተጫዋቹ ሁለት የውድድር ዓመታትን በአዳማ ከተማ ያሳለፈ ሲሆን በአዲሱ ክለቡ ሆሳዕና ደካማ የነበረው የተከላካይ ክፍልን እንደሚያሻሽል ይጠበቃል።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ