የገብረመድኅን ኃይሌ አይረሴ ትውስታዎች

ያልተጠበቁ ሁለት የመጥፋት ታሪኮች ፣ የእግር ኳስ ፍቅር እና የየመን ቆይታ…

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ስማቸው በግንባር ቀደምትነት ከሚነሱ ግለሰቦች አንዱ ነው። የእግር ኳስ ሕይወቱ በከፍተኛ አንድ ጀምሮ ከፍተኛ ዝና ባገኘበት ባህር ዳር ጨርቃ ጨርቅ እና በርካታ ዋንጫዎች ባነሳበት ቅዱስ ጊዮርጊስ የተጫወተው ገብረመድኅን ኃይሌ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንም በተለያዩ የዕድሜ እርከኖች ተጫውቶ በ1980 የሴካፋን ዋንጫ በአምበልነት አንስቷል። በለጋ ዕድሜው ለከፍተኛ አንድ ተጫውቶ የታዳጊ ቡድኑን እምብዛም ሳያገለግል በታዳጊ ቡድን እያለ በሚያውቁት የጎጃም ክፍለ ሀገር የስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይሉ ገብረመስቀል ወደ ባህር ዳር ጨርቃ ጨርቅ ተዘዋውሮ በክለቡ ጥሩ ዓመታት አሳልፏል።

በክለቡ ወሳኝ ተጫዋች ለመሆን ጊዜ ያልወሰደበት ወጣቱ ገብረመድኅን ከብዙዎች ግምት ውጭ ከክለቡ እስከተለያየበት ጊዜ ድረስ የቡድኑ ወሳኝ ተጫዋች ነበር። በክለቡ ቆይታውም በታዳጊ ብሔራዊ ቡድን የሀገሩን ማልያ ለብሶ ተጫውቷል። ከባህርዳር ጨርቃ ጨርቅ ከተለያየ በኃላም ወደ ፈረሰኞቹ ቤት ቅዱስ ጊዮርጊስ ተዘዋውሮ በተጫወተባቸው አስር ዓመታት በዋንጫ ያሸበረቀ ጊዜ አሳልፈዋል። ከቅዱስ ጊዮርጊስ ምርጥ አስር ዓመታት በኋላ በተደጋጋሚ ጉዳት በቶሎ ከእግር ኳስ ለመገለል የተገደደው ገብረመድኅን በቅርብ ጓደኞቹ ጥያቄ ለእርሻ ሰብል ለጥቂት ግዜ ቢጫወትም ብዙም ሳይቆይ ጫማውን ሰቅሏል።

ከተጫዋችነት ሕወቱ ከተገለለ በኃላ በቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ በሂሳብ ሰራተኛነት ስራ ጀምሮ የነበረው የወቅቱ የእግር ኳስ ኮከብ በተመረቀበት ስራ ብዙም ሳይሰራ ነበር መቐለ ከነማ (ምክር ቤት) ለማሰልጠን ተስማምቶ ወደ መቐለ ያመራው። በመቐለ ሳይጠበቅ ስኬታማ ጊዜያት በማሳለፍ የአሰልጣኝነት ሕወት ጀምሮም በሀገሪቱ ጥሩ ስም ካላቸው አሰልጣኞች ተርታ መሰለፍ ችሏል። ለዛሬም በእግር ኳስ ሕይወቱ ያጋጠሙትን ሦስት አይረሴ ትውስታዎች በራሱ አንደበት እናካፍላችዋለን። በቀጣይም በአሰልጣኞች ገፅ የአሰልጣኙን የሕይወት ጉዞ የምናቀርብላቹ ይሆናል።

* የባህርዳር ጨርቃ ጨርቅ የመጨረሻ ቀን እና የጎጃም ክፍለ ሀገር አይረሴ ትውስታዎች

” ባህር ዳር ጨርቃ ጨርቅ በጣም አሪፍ ጊዜ ነበረኝ። የባህር ዳር የስፖርት ደጋፊ አንዴ ከወደደህ በቃ ልዩ ቦታ ነው የሚሰጥህ። እኔም በነበረኝ ጊዜያት በጣም ደስተኛ ሆኜ ነበር ያሳለፍኩት። እንደውም አንድ ጊዜ ከታዳጊ ብሔራዊ ቡድን ጨዋታ ወደ ባህር ዳር ስገባ ሰርፕራይዝ አድርገውኛል። ባህር ዳር ልትገባ ስትል ባለው የፍተሻ ቦታ ወታደሩ መጥቶ “እዚህ ገብረመድኅን የሚባል አለ?” አለን ድምፁ ከፍ አድርጎ። እኔም ከነበርኩበት ደንግጬ ተነሳሁና አቤት አልኩት። ሰው አንተን እየጠበቀህ ነው ውረድ አለኝና ወረድኩ። ከዛ በኃላ ያየሁት ግን ማመት አልቻልኩም። ደጋፊያችን ፣ የክለብ አመራር የከተማው የእግር ኳስ አፍቃሪ እኔን ለመቀበል መጥቷል፣ እኔም በጣም ደስ አለኝ። አጅበውኝ ወደ ከተማ ሄዱ፤ የመጀመርያዬም ስለነበር ልዩ ደስታ ነበር የፈጠረልኝ። በባህር ዳር ጨርቃ ጨርቅ የነበረኝ ቆይታ በጣም አሪፍ የተሳካ ነበር፤ ሌላው ይቅር የቤት ኪራይ እንኳ ከፍዬ አላውቅም ነበር። በነዚህ ምክንያቶች ባህር ዳር ጨርቃ ጨርቅን ለቅቄ መሄድ ለኔ ከባድ ውሳኔ ነበር፤ በጣም ከባድ ውሳኔ።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ፈለገኝ፤ ንግግርም አደረግን። ከዛ በኃላ ግን ክለቡ ደሞዜ ወደ 403 እንደሚያሳድግልኝና በክለቡ እንድቀጥል ከመስተዳድሩ ደብዳቤ ደረሰኝ። ደሞዙ እና የክለቡ ደጋፊዎች ፍቅር በጣም ብዙ ነበር ለኔ። ግን ጊዮርጊሶች ደግሞ በጣም ፈልገውኝ ትኬት ቆርጠውልኛል። ብነግራቸው ጥያቄዬን አይቀበሉትም፤ ሌላ ደግሞ ከክለቡ ፍቅር የተነሳ እንደዛ ብሎ ጥያቄ ማቅረብም ስለከበደኝ አንድ ሀሳብ መጣልኝ… ጠፍቶ ወደ አዲስ አበባ መሄድ። ከዛ አየር መንገድ የሚሰሩ ሰዎች ስለሚያውቁኝ ወዴት ነህ ምናምን ብለው እንዳይጠይቁኝ እና እንዳያስተጓጉሉስኝ ብዬ ተሸፋፍኜ እየመረረኝም ቢሆን ክለቡን እና ከተማውን ለቅቄ አዲስ ፈተና ለመጋፈጥ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ፈረምኩ። በቅዱስ ጊዮርጊስም በጣም የተሳካ ጊዜ አሳለፍኩ። በርካታ ዋንጫዎችን አነሳሁ፤ በግልም በጣም ጥሩ ብቃት ላይ ነበርኩ። ይህ በእግር ኳስ ሕይወቴ ካጋጠሙኝ ነገሮች ከማልረሳቸው እና ለውሳኔ ከተቸገርኩባቸው አንዱ ነው።

*የየመን የብቸኝነት ጊዜ እና የሰንዓ አየርማረፍያ ያልተሳካ የመጥፋት ሙከራ

ከቡና ጋር አሪፍ ዓመት ካሳለፍኩ በኀላ ከወደ የመን የዝውውር ጥያቄ ቀረበልኝ። መጀመርያ አከባቢ ጥያቄዬ ለመቀበል አልፈለጉም ነበር። ከብዙ ንግግር በኃላ ግን ፈቅደው ውሌን ቀድጄ ወደ የመን ሄድኩ። ቡና አሪፍ እና ከትንሽ ዓመታት በኃላ ለዋንጫ የሚፎካከር ተስፋ የነበረው ቡድን ነበር። እንደውም ከቀጣዩ ዓመት በውበቱ አባተ ስር ዋንጫ አንስተዋል። ወደ የመን ትውስታዬ ስመለስም ኢትዮጵያ ቡናን ለቅቄ ወደ የመን ከፈረምኩ በኃላ ስድስት ወር ብቻ ነው የቆየሁት። ሕይወቱ ከባድ ነበር፤ በመጀመርያ ክለቡ የምፈልገውን ነገር አላሟላልኝም ነበር። ከዛ በኃላ ግን የግድ ማሟላት እንዳለባቸው ነገርኳቸው አሟሉልኝ። አመራሩም ተጫዋቾቹ እንደወደዱኝ እና ይህን አስጠብቄ መሄድ እንዳለብኝ ነገሩኝ ተቀብዬ ስራዬን ቀጠልኩ።

የመጀመርያው ጨዋታዬ የአሸናፊዎች አሸናፊ ነበር፤ በሌላ ሀገር የተዘጋጀ ጨዋታ ነበር። እሱን ዋንጫ አሸንፈን ዓመቱን ጀመርነው። ሁሉም ነገር ግን አልጋ በአልጋ ሊሆንልኝ አልቻለም። በአንድ በኩል የየመን የብቸኝነት ኑሮ ስልችት ብሎኛል፤ በሌላ በኩል ደግሞ በዓመቱ መጀመርያ ላይ ቡድኑን ለመዋሃድ ጊዜ ወስዶበት ነበር። ሁልጊዜ የኔ ቡድን ለመዋሀድ ጊዜ ይወስድበታል። ከዛ በኃላም በጅማም በመቐለም ተመሳሳይ ነገር ገጥሞኛል። አራት አምስት የሚሆን ጨዋታ ቡድኑ መቸገር ጀመረ ደረጃችንም አሽቆለቆለ። ደጋፊውም ” ባራ … ባራ .. ” ማለት ጀመሩ ባራ ማለት አስወጡት ማለት ነው። አመራሩ ግን የቡድኑ እድገት እያዩት ስለነበር ሙሉ በሙሉ ከጎኔ ነበሩ። በአምስተኛው ጨዋታ ከሜዳ ውጭ አሸንፈን ከተመለስን በኃላ ቡድኑ ወደ አሪፍ መንገድ መጣ፤ ተከታታይ ጨዋታዎች ማሸነፍ ጀመርን።

ምንም እንኳ ውጤቱ ወደመስተካከል ቢመጣም እኔ ግን አካባቢውን መልመድ አልቻልኩም፤ ጓደኛ የለኝ የምቀርበው ሰው የለም፤ ጊዜዬን ማሳልፍበት አሪፍ ቦታ የለ፤ ምን አለፋህ በቃ ደንቆሮ ሆንኩ። ኑሮው ከምነግርህ በላይ ከበደኝ፤ የቡድኑ መስተካከል ትንሽ ፋታ ቢሰጠኝም ተረጋግቼ መስራት አልቻልኩም። ከዛ ክለቡን ልቀቁኝ ብዬ ጥያቄ አቀረብኩ። ግን አንቀበልም አሉ። ከባዱን ጊዜ ጠብቀንህ ቡድኑ ጥሩ ከሆነ ደጋፊውም ከጎንህ ከሆነ በኃላ የት ነው የምትሄደው አሉኝ፤ እንደውም ፕሬዝዳንቱ “እኛ እንለመናለን እንጂ አንለምንም ከኦማንም ከግብፅም መጥተው ነው የሚለምኑን አለኝ። ጥያቄህን ሰከን ብለህ አስብበት” ብሎኝ ተለያየን። እኔ ግን ጠፍቼ ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት ወሰንኩና ሁሉም ነገር ጨራርሼ ስልኬን አጥፍቼ ወደ አዲስ አበባ ለመብረር ወሰንኩ። ሁኔታው ግን እንዳሰብኩት ቀላል አልነበረም፤ ያሰብኩት የመጥፋት ሙከራ ከሸፈ። ዓረብኛም ስለማልችል በዚህም በዛም ብለው አስቀሩኝ፤ ከዛ ግን ቀጥታ ወደ ቤት ሄጄ ምንም እንዳልተፈጠረ ወደ ቤቴ ገባሁ። ልክ ቤት ገብቼ ስልኩን ስከፍተው አሰተርጓሚው ተደናግጦ ደወለልኝ ” ምን ሆነህ ነው የቤቱን በር ልንሰብረው ነበር እኮ። በውስጥ አንድ ነገር የሆንክ መስሎን ተደናግጠን ነበር። ” አለኝ እኔ ግን ኧረ ምንም አልሆንኩም እዚው ነበርኩ አልኳቸው። ይህ ነገር ከከሸፈ በኋላም ተረጋግቼ መስራት አቃተኝ፤ ድጋሜ ጥያቄ አቀረብኩ። ቤተሰቤን ወደ የመን እንዳመጣቸው ነገሩኝ። እኔ ደግሞ አይሆንም ቤተሰቤ ወደዚህ አይመጡም፤ ኑሮው ይከብዳቸዋል” አልኩ።

ከስንት ነገር በኃላ ግን ፕሬዝድልንቱ በነገሩ እየተገረመ መሄድ ከፈለግክ ግን ሂድ በቃ አለኝ የመንን ለቅቄ አዲስ አበባ ሄድኩ። የየመን ከባድ የፈተና ጊዜ ይህን ይመስል ነበር፤ በሕይወቴ በብዙ ነገር የተፈተንኩበት ጊዜ ነበር።

* የማልያ መጥፋቱ እንቆቅልሽ

እንዴት እንዳስታወሳችሁት ራሱ በጣም ገርሞኛል (ረዥም ሳቅ) ሁኔታው የሚገርም ነበር። ጊዜው 1980፤ በምስራቅ እና መካከለኛው አፍሪካ ውድድር ነበር። በዛ ውድድር ተደጋጋሚ ጊዜ የማልያ መጥፋት አጋጥሞኝ ነበር። አስር ቁጥር ነበር የማደርገው፤ የመጀመርያው ጨዋታ ከማድረጌ በፊት ግን አስር ቁጥሩ ማልያ ጠፋ። ማን እንደወሰዳት እስካሁን ድረስ አላውቅም። ከዛ በኃላ 15 ቁጥር አድርጌ ወደ ጨዋታው ገባሁ። ከቀናት በኃላ በሁለተኛው ጨዋታ ከመጀመሩ በፊት ደግሞ በድጋሚ አስራ አምስት ቁጥሩ ማልያ ጠፋ። ሁኔታው ግራ ነው የሚያጋባው፤ ማን እንደሚወስደው አይታወቅም። ያውን በጨዋታው መቃረብያ ሰዓት ላይ ሁለቱም ማልያዎች በአስገራሚ ሁኔታ ከጨዋታ በፊት ከጠፉብኝ በኃላ በፍፃሜው ጨዋታ 17 ቁጥር ለብሼ ነው የገባሁት።

በአጠቃላይ ሁኔታው እንቆቅልሽ ነበር፤ ስለ ሁኔታው ከትጥቅ ጋር በተያያዘ ስራ ለሚሰሩት ሰዎች ብጠይቅም አሳማኝ መልስ አላገኘሁም። አሁን ሆኜ ሳስበው ግን ሆን ብሎ አድብቶ የሚወስዳት ሰው ነበር ማለት ነው።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ