ቀደም ብለው ወደ እንቅስቃሴ በመግባት የነባር ተጫዋቾች ውል በማራዘም እና አዳዲስ ተጫዋቾች በማስፈረም የሚገኙት ሠራተኞቹ ረመዳን የሱፍ እና ሀብታሙ ሽዋለምን ሲያስፈርሙ የዳግም ንጉሤን ውል አራዝመዋል።
ከንግድ ባንክ ሁለተኛ ቡድን አድጎ ለንስር እና ለስሑል ሽረ የተጫወተው ተስፈኛው ረመዳን የሱፍ ስሙ ከበርካታ የሊጉ ክለቦች እየተያያዘ ቢቆይም በስተመጨረሻ ወደ ሠራተኞቹ አቅንቷል። የግራ መስመር ተከላካይ የሆነውና ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ሁነኛ ምርጫ መሆን የቻለው ረመዳን በቀጣይ በወልቂጤ ከተማ የግራ መስመር ላይ ጥንካሬ ይፈጥራል ተብሎ ይጠበቃል።
ሌላው የቡድን አጋሩን ፈለግ ተከትሎ ወደ ክለቡ ያመራው የቀድሞ ወልዲያ፣ አዳማ ከተማ እና ስሑል ሽረ አማካይ ሀብታሙ ሽዋለም ነው። ባለፈው ዓመት ወሳኝ የፍፁም ቅጣት ምት ግቦችን በማስቆጠር የፍፁም ቅጣት ምት ቀበኛ መሆኑ ያሳየው ይህ አማካይ ከክለቡ ጋር ያለውን ውል በመጠናቀቁ ወደ ወልቂጤ ከተማ ያመራው ሌላኛው ተጫዋች ሆኗል።
በተያያዘ ዜና ክለቡ የዳግም ንጉሤን ውል አራዝሟል። የቀድሞው የሲዳማ ቡና እና ኢኮሥኮ ተከላካይ በተሰረዘው የውድድር ዓመት በወልቂጤ መልካም አቋም ካሳዩ ተጫዋቾች አንዱ ነበር።
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!
© ሶከር ኢትዮጵያ