“እግርኳስ ያልተጫወተ ሰው ማሰልጠን አይችልም የሚለው የማኅበራችንም፣ የአመራሮቻችንም የግል አቋም አይደለም”

“ማኅበሩ የተጫዋቾችን መብት ለማስከበር እየተንቀሳቀሰ ይገኛል” የተጫዋቾች ማህበር ዋና ፀሐፊ ኤፍሬም ወንድወሰን

ከሰሞኑን በተለያዩ መንገዶች ሁለት ጫፍ ያየዙ ሀሳቦች ተነስተው የብዙዎች የስፖርት ቤተሰቦችን ሀሳብ ከፋፍሏል። በአንድ ወገን እግርኳስ ተጫውተው ያሳለፉ ብቻ ማሰልጠን አለባቸው። በሌላ ወገን እግርኳስን ያልተጫወቱም ቢሆን የማሰልጠን መብት አላቸው የሚሉ ናቸው። በዚህ መነሻነት የኢትዮጵያ ተጫዋቾች ማኀበር አመራሮች በዚህ ጉዳይ ላይ ያላቸውን አቋም እና እግረ መንገድ ደሞዝ ያልተከፈላቸው ተጫዋቾችን መብት ለማስከበር ማኅበሩ ምን እየሰራ እንደሚገኝ የማኀበሩን ዋና ፀኃፊ የቀድሞ ተጫዋች ኤፍሬም ወንደሰን አናግረነዋል።

“ክለቦች ደሞዝ ያልከፈሏቸው ተጫዋቾች ፊርማችሁን በደብዳቤ አስፍራችሁ ውክልና ስጡን ብለን ጠይቀን ነበር። ማኅበሩ ውክልና ካገኘ የህግ ከለላ ለመስጠት አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚያደርግ ከህግ ባለሙያዎቻችን ጋር ተነጋግረናል። በመጀመርያ ክለቦችን በማስጠንቀቂያ እንጠይቃለን። ምላሽ የማይሰጡ ከሆነ ወደ ህግ እንሄዳለን በማለት ለተጫዋቾቹ አስረድተናል። ይህን ለማድረግ አብዛኛዎቹ ተጫዋቾች ፈራ ተባ እያሉ ነው። ሆኖም በግልም፣ እንደ ክለብ ሪፖርት ያደረጉ አሉ። ዛሬ ወይም ነገ በዚህ ጉዳይ ላይ የሚወጡ ደብዳቤዎች አሉ። ለሚዲያው የምናሳውቀው ይሆናል። በአጠቃላይ ማኀበሩ የተጫዋቹን መብት ለማስከበር እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።

“የማኅበሩ አመራሮች በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን እግርኳስን ተጫውተው ያለፉ ብቻ ያሰልጥኑ በማለት የሚናገሩት የማኀበሩ አቋም ነው ወይስ የግል አቋማቸው ነው ብለህ ለጠየቅኸኝ፤ ሀሳቡ የግላቸውም የማኀበሩም አይደለም። ሲጀመር መታወቅ ያለበት ነገሮች በሌላ መንገድ ትርጉም ተሰጥቷቸው ሰዎች ላይ ብዥታ ለመፍጠር እየተወራ ነው እንጂ እግርኳስ ያልተጫወተ ሰው እግርኳስን ማሰልጠን አይችልም የሚል የማኀበራችንም፣ የአመራሮቻችንም የግል አቋም አይደለም። በተቀመጠው መስፈርት መሰረት ሁሉም ሰው ቅድመ ተከተሉን ጠብቆ መምጣት አለበት። ይህ ደግሞ በፌዴሬሽኑ በተቀመጡ የሚመለከታቸው ሰዎች ማስፈፀም አለባቸው። በፍፁም ማኅበሩም ሆነ አመራሮች እግርኳስ ያልተጫወተ አያሰልጥን የሚል ይህ ሀሳብ አላነሱም። እርግጠኛ ሆኜ ነው የምነግርህ ይሄን አቋም የሚያራምድ የለም። የተለያዩ ነገሮችን እየሰማን ነው፤ ግን ደስተኞች አይደለንም። በቀጣይ በዚህ ጉዳይ ላይ መስተካከል ያለባቸው ነገሮችን አስመልክቶ ሰፊ ማብራሪያ እንሰጥበታለን።”

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ