ባልተለመደ መልኩ ከሌሎች ክለቦች ዘግይተው ወደ ዝውውር እንቅስቃሴ በመግባት ላይ የሚገኙት ምዓም አናብስት የአምስት ተጫዋቾች ውል አራዝመዋል።
አንተነህ ገብረክርስቶስ፣ ሙልጌታ ወልደጊዮርጊስ፣ አሸናፊ ሀፍቱ፣ ሶፎንያስ ሰይፈ እና ክብሮም አፅብሀ ውላቸው ለማራዘም የተስማሙ ተጫዋቾች ናቸው።
በእግር ኳስ ሕይወቱ ለባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ፣ ሐረር ቢራ ፣ አዳማ ከተማ እና ባንክ የተጫወተው የግራ መስመር ተሰላፊው አንተነህ ገ/ክርስቶስ ባለፈው የውድድር ዓመት በቦታው እምብዛም የቋሚ ተሰላፊነት ዕድል ባያገኝም ቻምፒዮን በነበሩበት ዓመት ጥሩ ግልጋሎት ማበርከቱ ይታወሳል።
ሌላው ውሉ ያራዘመው አማካዩ ሙሉጌታ ወልደጊዮርጊስ ነው። ከሁለት ዓመት በፊት በድጋሚ ወደ አሳዳጊ ክለቡ ተመልሶ ማገልገል የጀመረው ይህ አማካይ በመጀመርያው ቆይታው እየተቀየረ ቡድኑ ሲያገለግል ቆይቶ በተቋረጠው የውድድር ዓመት ግን በቋሚነት ሲጫወት ቆይቷል።
ሦስተኛው ውሉን ያራዘመው ተስፈኛው ግብ ጠባቂ ሶፈንያስ ሰይፈ ነው። ቡድኑ ወደ ፕሪምየር ሊግ ሲያድግ የአንበሳ ድርሻ የነበረው ይህ ግብ ጠባቂ ባለፉት ሁለት ዓመታት ቦታው በኢኳቶርያል ጊኒያዊው ፊሊፕ ኦቮኖ ቢያዝም በተሰጡት ጥቂት ዕድሎች የተሻለ እንቅስቃሴ አድርጓል። በዚህ የውድድር ዓመት የበለጠ ዕድል እንደሚያገኝም ይጠበቃል።
በአራተኛነት እና በአምስተኛነት ውላቸውን ለማደስ የተስማሙት ደግሞ የተጠቀሱት ደግሞ ተስፈኚው አሸናፊ ሀፍቱ እና ያለፈውን ስድስት ወር በሶሎዳ ዓድዋ በውሰት የቆየው አጥቂው ክብሮም አፅብሀ ናቸው።
ባለፈው የውድድር ዓመት ጠባብ ስብስብ የነበራቸው እና ከተጠቀሱት አምስት ተጫዋቾች ውጭ ሦስት ውል ያላቸው ተጫዋቸች ብቻ ያላቸው መቐለዎች በቀጣይ ቀናት በርካታ ዝውውሮች እና የውል እድሳቶች ላይ ይጠመዳሉ ተብሎ ይጠበቃል።
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!
© ሶከር ኢትዮጵያአ