ስለ ዮርዳኖስ ዓባይ ሊያውቋቸው የሚገቡ እውነታዎች

ያገኘውን የጎል አጋጣሚ የመጨረስ አቅሙ የተዋጣለት ነው። እርሱ ሜዳ ውስጥ ካለ ጎል አለ ብለው ብዙዎች በእርግጠኝነት ይናገሩለታል። በኢትዮጵያ እግርኳስ አንቱታ ካተረፉ አጥቂዎች መካከል አንዱ የነበረው ጎል አነፍናፊው ዮርዳኖስ ዓባይ (ቡሎ) የዛሬው የዘጠናዎቹ ኮከብ እንግዳችን ነው።

የብዙዎች ድንቅ ተጫዋቾች መፍለቂያ ከሆነችው ማህፀነ ለምለሟ ድሬደዋ ከተማ ልዩ ስሙ ደቻቱ በተባለ አካባቢ ነው ዮርዳኖስ ዓባይ የተወለደው። “ፊጂክ” የሚባል የሱማሌዎች አማተር ቡድን በታዳጊነት እድሜው መጫወት ጀምሮ በመቀጠል በድሬደዋ ጨርቃጨርቅ ቢ ቡድን ውስጥ ለአምስት ወራት ያህል ብቻ ቆይታ ካደረገ በኋላ በፍጥነት ወደ ዋናው ቡድን በ1991 ማደግ ችሏል። በሁለት ዓመት የጨርቃጨርቅ ቆይታው ያሳየውን ድንቅ እንቅስቃሴ የተመለከቱት መብራት ኃይሎች በ1993 ዮርዳኖስን ዓባይን የግላቸው አደረጉት።

ዮርዳኖስ አማካይ ተጫዋቾች ወደ ፊት እንዲመጡ አጫውቶ የሚሄድበት መንገድ እና የጎል አጋጣሚን ካገኘ የማይስት መሆኑ ለሁሉም የስፖርት ቤተሰብ በኤልፓ በነበረው የሁለት ዓመት ቆይታው ማሳየት ችሏል። በጣም በአስገራሚ ሁኔታ መብራት ኃይል በመጣበት ዓመት የሦስትእፀዮሽ ዋንጫ ከማንሳቱም ባሻገር በ26 ጨዋታዎች 24 ጎል በማስቆጠር የሊጉ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ በመሆን አጠናቋል። ይህ የጎል ብዛት በጌታነህ ከበደ በ26 ጎል እስከ ተሰበረበት 2009 ድረስ ለአስራ ስድስት ዓመት ሳይደፈር ባለ ሪከርድ ሆኖ መቆየት ችሏል። ይህም ብቻ አይደለም ለተከታታይ ሦስት ዓመት ከ1993–95 ለተከታታይ ሦስት ዓመት ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ሆኖ በማጠናቀቅ የተዋጣለት አጥቂ መሆኑን ማስመስከር ችሏል።

በብሔራዊ ቡድን አብሮት የተጫወተው ድንቁ አማካይ አሸናፊ ግርማ ስለ ዮርዳኖስ ዓባይ ይህን ምስክርነት ይሰጣል። “ዮርዳኖስ ብልጥ እና ጎበዝ አጥቂ ነው። ኳስ ይችላል፤ አንድ ለአንድ ሲገናኝ አብዶ ሰርቶ አልፎ ጎል ያስቆጥራል፤ ለጎል የሚሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ ያቀብላል፤ ሲሸፍን ጎበዝ ነው፤ የምትሰጠውን ኳስ በአግባቡ የሚጨርስ የተዋጣለት ጨራሽ አጥቂ ነው” ይለዋል።

በኢትዮጵያ እግርኳስ ዝናቸው ከናኙ አጥቂዎች መካከል አንዱ የሆነው ዮርዳኖስ ለሁለት ዓመት ከነገሰበት ከሁሉም የስፖርት ቤተሰብ ጋር ከተዋወቀበት መብራት ኃይል ጋር ተለያይቶ በ1995 በአሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ ወደሚሰለጥነው ኢትዮጵያ ቡናን መቀላቀል ችሏል። ለአንድ ዓመት ብቻ ቆይታ በነበረው ቡና ቤት የጥሎ ማለፍ ዋንጫን አንስቶ ከአህመድ ጁንዲ ጋር በጣምራ የከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነት ክብርን አግኝቷል። በቡና ማልያ ረጅም ዓመት ሳይቆይ ግን ብዙ የቆየ እስኪመስል ድረስ እንደተወደደ፣ ሳይጠገብ ለቀጣይ አስር ዓመታት በቆየበት የየመኑ አልሳቅር ክለብ አምርቷል።

ዝምተኛው አጥቂ በየመን በቆየባቸው ዓመታቶች በሀገሩ ያሳካውን ለተከታታይ ሦስት ዓመት ከፍተኛ ጎል የማስቆጠር ልማድ በየመንም በመድገም ለተከታታይ ሦስት ዓመት የመን ሊግ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ በመሆን አጠናቋል። አመለ ሸጋው ዮርዳኖስ በየመን ሊግ በአንድ የውድድር ዘመን አንድም ቢጫ ሳይመለከት ውድድሩን በማጠናቀቁ የፀባይ ዋንጫን ተሸልሟል። በየመን የተሳኩ አስር ዓመታትን አሳልፎ ወደ ሀገሩ በመመለስ ለቀድሞ ክለቡ መብራት ኃይል፣ ድሬዳዋ ከተማ፣ ድሬዳዋ ፖሊስ እና ናሽናል ስሚንት በተጫዋችነት እና በም/ አሰልጣኝነት አግልግሏል። በወጣት እና በዋናው ብሄራዊ ቡድን ሀገሩን ያገለገለው ዮርዳኖስ በአርጀንቲና በተዘጋጀው የዓለም ወጣቶች ዋንጫ ከተሳተፈው ቡድን ውስጥ የተካተተ ሲሆን በ1994 ከሀገር ውጭ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የሴካፋ ዋንጫ ሲያነሳ የነበረው አስተዋፅኦ የጎላ ነበር። በአጠቃላይ ጣፋጭ የሆኑ የማይዘነጉ አስራ አምስት ዓመታትን ካሳለፈ በኋላ በ2010 ከጨዋታ ዓለም መግለሉ ይታወቃል።

በአንድ ወቅት የሀዋሳ ከነማ አሰልጣኝ የነበሩት ጋሽ ከማል ዮርዳኖስ በተከላካዮች ቁጥጥር ስር ለማድረግ ከመቸገራቸው የተነሳ ለተከላካዮቻቸው እንዲህ ብለው መከሩ “መቼም እናተ አትይዙትም ገብርኤል ይያዘው እንጂ” በማለት ተናግረውለታል። በዛሬው የሶከር ኢትዮጵያ የዘጠናዎቹ ኮከብ ተጫዋች አምዳችንም የዚህን ድንቅ አጥቂ የእግርኳስ ዘመን አስመልክቶ ከእርሱ ጋር ያደረግነው ቆይታ እነሆ…

“በመጀመርያ አመሰግናለሁ። በእግርኳስ ህይወቴ ያገኘሁት ቀዳሚው ስኬት ሰው ነው። በእግርኳሱ በነበረኝ ቆይታ ብዙ መልካም ሰዎችን አትርፌበታለሁ። በሁለተኛ ደረጃ እኔን እንደ አርዓያ አይተው ወደ እግርኳሱ የገቡ ተጫዋቾችን ስመለከት ደሞ እደሰታለሁ። በመብራት ኃይል፣ በቡና፣ በየመን በዋንጫ የታጀበ ድሎችን እንዲሁም የከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነትን ክብርን አግኝቻለው። ስለዚህ እነዚህ ዋነኛ ነገሮች ስኬታማ አድርገውኛል ብዬ አስባለሁ። በግሌ ስኬታማ የሆንኩባቸው ዓመታት ላይ አጋጣሚ ሆኖ የነበርኩበት የቡድን ስብስብ ጥሩ ነበር። ለምሳሌ ድሬዳዋ ጨርቃጨርቅ ሆነ መብራት ኃይል፣ ቡና እያለሁ የነበረው የቡድን ስብስብ በጣም አሪፍ ነበር። ለዚህም ነው ስኬታማ የሆነ ጊዜ የነበረኝ።

“አንዳንድ ጊዜ ከጨዋታ በፊት የማስባቸውን ነገሮች ሜዳ ላይ አለማድረጌ ያስቆጨኛል። ይህንን ማድረግ አለብኝ! ብዬ ወደ ሜዳ ገብቼ ሳላደርጋቸው ስቀር ማለቴ ነው። በስኬት ደረጃ ደግሞ በ1995 የነበረው የኢትዮጵያ ቡና ስብስብ ዋንጫ አለማንሳቱ ያንገበግበኛል። በጣም ምርጥ ቡድን ነበር። እንደውም በጊዜው ኮከብ ተብዬ ልሸለም ደረጃ ስወጣ ዋንጫ ባለማንሳታችን ተናድጄ እያለቀስኩ ነበር። ከዚህ በተጨማሪ ኢትዮጵያ መድን እያለው አሰልጣኝ ዓባይነህ የሰራው ቡድን ጥሩ ነበር። በዚህም ቡድኑን ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ እናሳድገዋለን ብለን ነበር። ግን ሳይሆን ቀረ። እቅዳችን ባለመሳካቱ ደግሞ በጣም ተቆጭቻለሁ።

“በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያ ጎሌን ያስቆጠርኩት ድሬዳዋ ጨርቃጨርቅ እያለሁ ነው። ግን አሁን ላይ ግቡን ማን ላይ እንዳስቆጠርኩ አላስታውሰውም። በክለብ ደረጃ እያለሁ የመጨረሻ ጎሌን ያስቆጠርኩት ደግሞ ድሬዳዋ ሲሚንት እያለሁ ነው።

“እናት እና አባቴ በነገሩኝ መሰረት ቡሎ ማለት ጎበዝ ነጭ ፈረስ ጋላቢ ማለት ነው። ይህንንም ስም ያወጡልኝ አንድ እናት (እማሆይ) ናቸው። እኚህ እናት ሁልጊዜ ከቁልቢ ሲመጡ እኛ ግቢ እየመጡ ሰው ይጠይቃሉ። ሲመጡ ደሞ እኔን ያገኙኝ ነበር። የሚገርመው እኔ ስወለድ ከ5 ኪሎ እበልጥ ነበር። በጣም ትልቅ ነበርኩ። እና እኚህ እናት ሲያጫውቱኝ “ቡሎ፤ አባ ቡሎ” እያሉ ነበር። እንዲህ እያሉ ሲያጫውቱኝ ደግሞ ወላጅ አባቴ ይሰማቸውና ለምን ቡሎ እንደሚሉኝ ጠየቃቸው። እኚህ እናትም ወፍራም ልጅ መሆኔን አይተው ቡሎ እንዳሉኝ ቡሎ ማለትም በኦሮሞ ባህል ትልቅ እና ነጭ ፈረስ ጋላቢ ማለት እንደሆነ ነገሩዋቸው። የሚገርመው እኚህ እናት አያይዘውም ትልቅ ደረጃ ይደርሳል ብለው ቡሎ እንዳሉኝ ለአባቴ ገልፀው ነበር።

“ጎል የመጨረስ አቅሜን ችሎታዬን ያዳበርኩት ቅድም እንዳልኩህ ጨርቃ ጨርቅ ስገባ በጣም ሲኒየር የሆኑ ተጫዋቾችን ነው ያገኘሁት። እነሱ የሚሉኝን ነበር የምሰማው። አባቴም ስምዖንም እዛ ስለተጫወቱ የተሻለ እንድሆን ይመክሩኝ ነበር ፤ እኔም እሰማለሁ። ልምምዴን በአግባቡ እሰራ ነበር። ለስራዬም (ተገዢ) ዲሲፕሊንድ ነበርኩ። ያገኘኋቸውን ተጫዋቾች ምክር ሰምቻለው። የእነሱን ልምድ ወስጃለሁ። መብራት ኃይልም በጥሩ የአማካይ ተጫዋቾች ታጅቤ መጫወቴም ያለኝን ችሎታ በይበልጥ አውጥቼ እንድጫወት እንዳደረገኝ ነው የማስበው።

“በእግርኳስ ገጠመኜ አጠፋህም አላጠፋህም እግርኳስ ተጫዋች ሆነህ ከደጋፊዎች የሚሰነዘሩብህ አንዳድ ነገሮች አሉ። በእህትህ፣ ባለቤትህ ወይም በአጠቃላይ ቤተሰብህ ላይ የሚሰነዘር ነገር (ስድብ) ሊኖር ይችላል። አንድ ጊዜ ጋዜጣ ላይ አዜብ ስለምትባል እንስት ሃሳብ ሰጥቼ ነበር። አዜብ ሁልጊዜ ለእኔ ደብዳቤ የምትፅፍልኝ ልጅ ነበረች። የምትፅፍልኝም ደብዳቤ በየጨዋታዎቹ ስላደረኳቸው ነገሮች ነው። ደግሞም የምታነሳቸው ነጥቦች በጣም ድንቅ ነበሩ። አሰልጣኝ ካልሆነ ሰው የምጠብቀው አልነበረም። እና ጋዜጣው ላይ አዜብን ላመሰግን እወዳለሁ ብዬ ሃሳብ ሰጠሁ። ከዛ ጋዜጣው በወጣ በሁለተኛው ቀን ከባንክ ጋር ጨዋታ ልናደርግ ወደ ሜዳ ገባን። ባልጠበኩት ሁኔታ ምንም ሳላደርግ “አዜብ! አዜብ! አዜብ!…” እየተባለ ይጮህ ጀመረ። በዚህም በጣም ነው የደነገጥኩት። እኔ ልጅቷን አደነኳት እንጂ ምንም አላልኩም ነበር። ግን በጊዜው ጉዳዩ ወደ ሌላ ነገር ተወስዶ ሲዜምብኝ ነበር። እኔ ግን ቀደም ብዬ ሌሎች ተጫዋቾች በሚስቶቻቸው ሲሰደቡ ስላየው ጠንከር ብዬ ጊዜውን አለፍኩት።

“የአርጀንቲናው ቡድን በጣም ጥሩ ቡድን ነበር። እንደውም በጣም የሚያስቆጨኝ ቡድን ነበር ፤ አንድ ደረጃ መሻገር እንችል ነበር። 15 ቀን ቀድመን ነበር የገባነው ግን ከጨዋታ በፊት ሰማንያ ፐርሰንት የሚሆነው ተጫዋች ውስጥ ለመጥፋት ስሜት ነበር። ይሄ ስሜት እያለ ደግሞ ወደ ቀጣይ ዙር ማለፍ ከባድ ነው። እንጂ ያ ሀሳብ ባይኖር እና አንድ ብንሆን ኖሮ ቡድኑ የማለፍ አቅም ነበረው። ጨዋታው ካለቀ በኋላም ቢሆን የመጥፋት ሀሰሰቡን እኮ ማሰብ ይቻል ነበር። አልተሳካም በአጠቃላይ አርጀንቲና የነበረኝ ቆይታ በጣም አሪፍ ነበረ።

“የመንም ከ1996 መጫወት ከጀመርኩ ጊዜ አንስቶ ጥሩ ጊዜ ነበረኝ። እንደውም ለሦስት ተከታታይ ዓመትት የውድድሩ ኮከብ ግብ አስቆጣሪ ተብዬ ተመርጫለሁ። አንድ ዓመት ላይ ደግሞ ኮከብ ግብ አግቢነትንም ሆነ የፀባይ ዋንጫን በጣምራ በማሸነፍ ዋንጫ ወስጃለሁ። የፀባይ ዋንጫው የተሰጠኝ ዓመቱን ምንም የቢጫ ካርድ ሳልመለከት በማጠናቀቄ ነው። የመን ብዙ ትውስታ ነበረኝ አሪፍ ጊዜም አሳልፌ ወደ ሀገሬ ተመልሻለው።

“ድሬዳዋን አሁን ላይ ሆኜ ያለውን የእግርኳስ ደረጃ ስመለከት እውነት ለመናገር ዝም ማለት ነው እንጂ የሚሻለው ከተወራ ብዙ ነገር ማለት ይቻላል። አንተ እዚህ ድሬዳዋ በእግር ኳሱ ያጣችውን ስም ለመመለስ ስትጥር በአንድ ጎን ደግሞ ከአንተ መቶ በመቶ ተቃራኒ የሆነ ሀሳብ ያለው ሰው ይገጥምሀል። እና ምንም ማድረግ አትችልም ፤ የሰማይና የምድር ያህል የተራራቀ ሀሳብ ነው ያለን። ለመናገርም የሚከብድ ነገር ነው። በእኛ ጊዜ እንኳን ወጣት ተጫዋቾች እንደዚህ አልበዙም። እኛ በነበርን ጊዜ የተወሰንን ነበርን። ሁላችንም ቦታ ቦታ ያዝን እና ጥሩ ቦታ ደረስን። አሁን እኮ ወላ አዲስ ከተማ ፣ ለገሀሬ ወላ ሳቢያን ትላለህ የትም ቦታ ሄደህ ብታይ ከበጣም በጣም የሚያሳዝኑ ልጆች ነው ያሉት። በዚህ ሰዓት እኮ የ 20 ዓመት ልጆች የጤና ቡድን ሰርተው ታያለህ። ድሬዳዋ አሁን ባሉት ልጆች ሁለት ቡድን መስራት ትችላለች። ግን የሚሰራው ስራ ትንሽ ጠጋ ስትል እንድትሸሽ የሚያደርግህ ነው። ለምሳሌ ዮሃንስ ሳህሌ በቴክኒክ አማካሪነት ትሰራለህ ብሎኝ መጥቼ ነበር እኮ። ‘እናንተን የመሰላችሁ ተጫዋቾች እያላችሁ ለምንድነው የምትሸሹት ? ‘ በማለት። በአንድ ፊርማ ስራዬን መስራት እችል ነበር። ከዛ ግን እሱ ሳይስማማ ቀርቶ ሲሄድ ያንን ነገር ተዉት። የሚገርመው ስምዖን ከምክትልነት ወደ ዋና አሰልጣኝነት ሲመጣ አብዛኛው ሰው እኔም ስራ እንደጀመርኩ ነበር የሚያውቀው። መጨረሻ ላይ ግን ስጠይቃቸው በዓለም ላይ የሌለ ‘ከአንድ ቤት እንዴት ሁለት ሰው? የሚል ነገር ነው የሰማሁት። ይሄን ሚዲያ ላይም ሆነ ለማንም ሰው አላወራሁትም። ምክንያቱም ወንድሜ በወቅቱ ስራ እየሰራ ነበር። እኔ ብጋፈጣቸው የእሱን ስራ ነው የሚያበላሹት። ስለዚህ ዝም አልኩኝ። ሁሉን ነገር ጊዜ የሚፈታው ይሆናል።

“ድሬደዋ ወደ ቀደመ ስሟ እንድትመለስ ወጣቶች ላይ ለመስራት ብዙ ዕቅድ ነበረኝ። ግን እኔ ነኝ ስራ ልስራ ብዬ መምጣት ያለብኝ ? አንዳንዴ የሚባል ነገር አለ ፤ እኔ ለሀገሬ ምን ሰራሁላት ? ማለት ይቀድማል ይባላል። ለሀገሬ የሰራሁላትንማ ህዝብ አይቷል እኮ። አሁን ደግሞ ባለህ ልምድ ባሳለፍከው ነገር ደግሞ ና ስራ ፤ ይሄን ልምድህን ለወጣቶች አካፍል ተብለህ ልትጠራ ይገባል። አብረሀቸው ቡና ብትጠጣ ወይ ስጋ ብትቆርጥ እኮ የሆነ ቦታ ስራ ይሰጡሀል። ይሄንን ካደረኩ ደግሞ እኔም ከእነሱ አልተለየሁም። ከምንም ነገር በላይ ሰው ይበልጣል ፤ በሰራው ነገርን መከበር አለበት። እንጂ ድሬዳዋ ላይ እንደ አሸን የፈሉ ልጆች አሉ። ብቻ በጣም ነው የሚያሳዝነው።

“አሁን ያለውን የኢትዮጵያ እግር ኳስን ለማነፃፀር ሁሉም በጊዜው ጥሩ ነገር አለው። ግን የተሻለ ዕድገት መምጣት ነበረበት። በዚህ ሰዓትም የማይታመን በጣም ጥሩ ስራ የሚሰሩ ልጄችም አሉ። ግን ምስቀልቀሉ ወጣ። ለመግለፅ በጣም ይከብድል። እንጂ በእኛ ጊዜ በጣም ይሻል ነበር ምናምን ልል አልችልም። በእኛም ጊዜ ጥሩ ያልሆኑ ነገሮች ነበሩ። ጥሩ ያልሆኑትን ነገሮች ትቶ መልካሞቹን ለማሻገር መሞከር ነው ያለበት እንጂ በእኛ ጊዜ በእኛ ጊዜ ማለቱ ሁሉንም እርስ በእርስ ከማባላት ውጪ ጥቅም አይኖረውም። ሁሉም ጊዜ ላይ የራሱ ጥሩ ነገር ነበር። አሁን ደግሞ የተሻለ ለመስራት መሞከር አለበት። ወደ ኋላ ተመልሰን በክርክር ፣ በመጣላት እና በአሽሙር ማሳለፉ አይጠቅምም። ለምሳሌ አሁን ሙስና ይባላል። በእኛ ጊዜ ይሄ ሁሉ ብር ቢከፈል ሙስና አይኖርም ነበር ? እውነት ነው አሁን የገንዘብ ነገር ብዙ ምስቅልቅል አምጥቷል። ደጋፊ ለክለብ ተጫዋች እስከማምጣት የደረሰበ ጊዜ ሆኗል። ብቻ እንደኔ ሁሉም በጊዜው የራሱ ጥሩ ነገር አለው ብዬ ነው የማምነው።

“በአሰልጣኝነቱ የ’ሲ’ ላይሰንስ ኮርስ ወስጃለሁ። ከዛ በተጨማሪ ደግሞ በራሴ በጎ ፍቃደኝነት እዚህ ወጣቶች ላይ ከሚሰሩ ልጆች ጋር ልምድ በማካፈል አብሮ ልምምድ በመስራት ልጆቹን በማበረታታት እንቀሳቀሰላሁ። ቀስ እያልኩ ደግሞ ተጨማሪ ኮርሶችን እወስዳለሁ። ጥሩ ነገር እስካየሁ ድረስ በአሰልጣኝነቱ መስራት እፈልጋለሁ። ነገር ግን ብዙ አሰልጣኞች ለእግር ኳሱ ያላቸውን ነገር ሰጥተው እኮ መጨረሻ ላይ ሳይረዱ የሞቱ አሉ። እኔ እነሱን እያየሁ መስዕዋት መሆን አልፈልግም።

እኔ በተጫዋችነት ዘመኔ በ93 ላይ ኤልፓ ሆኜ ጊዮርጊስ ላይ ያገባሁዋቸውን ጎሎች አልረሳቸውም። ምክንያቱም ጊዮርጊስ ትልቅ ክለብ ነው፤ ትልቅ ክለብ ላይ ማግባት ደግሞ ያስደስታል። ሁለተኛ ደግሞ አሁን ስመለስ ኤልፓ ከገባሁ በኋላ ዳሽን ላይ ያገባኋት ግብ።”

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ