ሙሉዓለም ረጋሳ ጫማውን ሰቀለ

ያለፉትን 23 ዓመታት አይረሴ የእግርኳስ ህይወቱን በክለብ እና በብሔራዊ ቡድን የመራው ድንቁ አማካይ ሙሉዓለም ረጋሳ ጫማውን ሰቀለ።

በ1989 የቅዱስ ጊዮርጊስን ታዳጊ ቡድንን በመቀላቀል በዓመቱ ወደ ዋናው ቡድን በማደግ እስከ 2002 ድረስ ተጫውቷል። ሙሉዓለም ረጋሳ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር የጥሎ ማለፍ እና የአሸናፊ አሸናፊዎች ዋንጫን ሳይጨምር ዘጠኝ የፕሪምየር ሊግ ዋንጫን አንስቷል። በ1994 በግሉ የፕሪምየር ሊጉ ኮከብ ተጫዋችነት ክብር አግኝቷል። ለሰበታ ከተማ፣ ኢትዮጵያ መድን፣ ሀዋሳ ከተማ፣ ለደቡብ ፖሊስ እና እግርኳስን እስካቆመበት ጊዜ ድረስ ለሱሑል ሽረ መጫወት ችሏል። ከ1989 ለታዳጊ ቡድን አንስቶ እስከ 1999 ድረስ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አገልግሏል። በብሔራዊ ቡድን ቆይታውም በ1994 እና በ1998 ኢትዮጵያ የሴካፋ ዋንጫን ስታነሳ የቡድኑ ቁልፍ ተጫዋች ነበር። ለ23 ዓመታት በኢትዮጵያ እግርኳስ ጣፋጭ ጊዜያትን ያሳለፈው ሙሉዓለም ከእግርኳስ ተጫዋችነት ዓለም ራሱን ማግለሉን ለሶከር ኢትዮጵያ ተናግሯል።

” አስደሳች የእግርኳስ ዘመንን በተጫዋችነት ዘመኔ አሳልፌያው። እግርኳስን አሁንም ቢሆን የመጫወት አቅሙ ነበረኝ። ሆኖም አንዳንዴ አሰልጣኞች እኔን የሚረዱበት መንገድ ሌላ ነው። ዕይታችን የተለያየ በመሆኑ እግርኳስን ለማቆም ወስኛለው። ወደ አሰልጣኝነቱ ለመምጣት ወደፊት አላውቅም። ምን አልባት መስመሩ ተመችቶኝ ከሆነ ልመጣ እችላለው። የስልጠናው መስመር ካልተመቸኝ የምመጣ አይመስለኝም። ሁኔታዎችን አይቼ ወደ አሰልጣኝነቱ ልቀላቀል እችላለው። እስከዛ በራሴ በኩል ግን አሰልጣኝ ለመሆን የሚያስፈልጉ ነገሮችን ሁሉ እያደረኩ እጠብቃለው።

“በመጀመርያ ፈጣሪዬን አመሰግናለሁ። በመቀጠል አሰልጣኝ አሥራት ኃይሌ በእግርኳስ ህይወቴ ሁሌም የማመሰግነው ሰው ነው። እግርኳስን አቁሜ ዳግመኛ ወደ እግርኳሱ እንድመለስ በማድረግ አቅሜን እንዳሳይ የረዳኝን አሰልጣኝ ውበቱ አባተንም አመሰግናለው። በመጨረሻም ሲደግፉኝ ሲያበረታቱኝ የነበሩትን ሁሉ ከልብ አመሰግናለው።” ብሏል።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ