ፋሲል ከነማ የሦስት ተጫዋቾችን ውል አድሷል

ለ2013 የውድድር ዘመን አዳዲስ ተጫዋቾች ከማስፈረም ባለፈ ውል በማራዘሙ የተጠመዱት ዐፄዎቹ የአምሳሉ ጥላሁን ቴዎድሮስ ጌትነት እና መጣባቸው ሙሉን ውል አራዝሟል፡፡

በ2009 ቡድኑን ከተቀላቀለ ወዲህ በወጥነት ጠንካራ ብቃቱን እያሳየ የሚገኘው የግራ መስመር ተከላካዩ አምሳሉ ጥላሁን ውሉን ለተጨማሪ አመት ያራዘመ ተጫዋች ሆኗል፡፡ የቀድሞው የዳሽን ቢራ ተጫዋች ውሉን ማራዘሙን ተከትሎ ባለፉት ሁለት ዓመታት የነበረው የፋሲል የተከላካይ ክፍል አሁንም ለውጥ ሳይደረግበት በጥንካሬ እንደሚዘልቅ ይጠበቃል።

ሌላኛው ውሉን ያራዘመው ቁመተ ረጅሙ ግብ ጠባቂ ቴዎድሮስ ጌትነት ነው፡፡ በማሊያዊው ሳማኪ ሚኬል ተጠባባቂነት ረጅም ገዜ ያሳለፈው ቴዎድሮስ በተሰረዘው የውድድር ዓመት ራሱን እያሻሻለ በመምጣት በተለይ በመጨረሻው የአንደኛው ዙር እና ሁለተኛ ዙር አጋማሽ ጅማሮ ላይ ያገኘውን እድል በመጠቀም ድንቅ አቋም ማሳየቱ አይዘነጋም።

የተከላካይ አማካዩ መጣባቸው ሙሉም ውሉን ያራዘመ ሦስተኛው የክለቡ ተጫዋች ነው፡፡ ተጫዋቹ በመጀመርያ አሰላለፍ ክለቡን በበርካታ ጨዋታዎች ላይ መሰለፍ ባይችልም ተቀይሮ በመግባት ቡድኑን አገልግሏል። ለአንድ ተጨማሪ ዓመት ለመቆየትም ተስማምቷል፡፡

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ