ፌዴሬሽኑ ፕሪምየር ሊጉ የሚካሄድበትን መነሻ ሀሳብ ለሚመለከተው አካል አቀረበ

የ2013 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የሚካሄድበት መንገድ አስመልክቶ ፌዴሬሽኑ ለሚመለከታቸው የመንግስት አካላት በላከው ሰነድ ዙርያ ምላሽ እየጠበቀ ነው።

በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት የ2012 ውድድሮች ሙሉ ለሙሉ መሰረዛቸው ይታወቃል። በቀጣይ የ2013 የውድድር ዘመን መቼ ይጀመራል? የሚለው ጉዳይ ምላሽ ሳያገኝ ክለቦች በዝውውሩ ተጠምደው መገኘታቸው የብዙዎች መነጋገርያ ርዕስ ሆኗል። ውድድሩ የሚጀምርበትን ቀን ለመወሰን እና የቀጣይ የውድድር ዓመት የኮሮና ቫይረስን መከላከል በሚቻልበት መልኩ ጨዋታዎች በምን ሁኔታ መካሄድ አለባቸው በሚል የተለያዩ ጥናቶች እና የሌሎች ሀገሮችን ተሞክሮ ሲወስድ የቆየው ፌዴሬሽኑ የፕሪምየር ሊግ ውድድሮችን ለማስጀምር የተለያዩ ቅድመ ሁኔታዎችን የያዘ ሰነድ ለሚመለከታቸው የመንግስት አካላት መላኩን ለማወቅ ችለናል። ምንም እንኳ ከፌዴሬሽኑ የወጣ ግልፅ መግለጫ ባይኖርም ሶከር ኢትዮጵያ ባገኘችው መረጃ መሠረት በሰነዱ ላይ ከቀረቡ ሰፊ ዝርዝር ሀሳቦች ውስጥ በዋናነት የሚጠቀሱትን ሀሳቦች ለማቅረብ ወደድን

* እያንዳንዱ የፕሪምየር ሊግ ቡድን በራሱ ወጪ ጨዋታ ከማድረጉ 72 ሰዓት በፊት የኮሮና ምርመራ ውጤት እንዲያቀርብ

* ውድድሮቹ ክለቦች በራሳቸው ሜዳ ሳይሆን በተመረጡ ሜዳዎች ብቻ እንዲካሄዱ።

* ሁሉም ጨዋታዎች በዝግ ያለ ተመልካች እንዲካሄዱ።

* ጨዋታዎቹ በጠቅላላ በቴሌቪዥን የቀጥታ ስርጭት ሽፋን እንዲያገኙ።

* እያንዳንዱ ቡድን ወደ ተለያዩ የጨዋታ ቦታዎች በመኪና የሚጓዝ ከሆነ ከንክኪ ለመራቅ ሁለት አውቶብስ ማዘጋጀት አለባቸው ።

* የሚጠቀሙበትን የስፖርት ቁሳቁስ መቀላቀል (መነካካት) እንዳይኖር በየስማቸው እንዲለይ ማድረግ ይገባዋል። እና ሌሎች ሀሰሰቦች የተካተቱበት ሰነድ ለሚመለከታቸው አካላት ተበትኖ ውሳኔ ፌዴሬሽኑ እየተጠባበቀ ይገኛል።

ይህ የተዘጋጀው መመርያ ከእኛ ሀገር የእግርኳስ እና የኢኮኖሚ አቅም አኳያ ምን ያህል አዋጪ ነው? ቡድኖች ይህን ሀሳብ ይቀበሉታል ወይ? የሚለው በቀጣይ የሚጠበቅ ሲሆን የተዘጋጀው ሰነድ የከፍተኛ ሊግ፣ የሴቶች ሊግ፣ የአንደኛ ሊግ እና የክልል ፌዴሬሽኖችን የውስጥ ውድድር ያማከለ ነው ወይስ የፕሪምየር ሊግ ውድድሮችን ብቻ የሚለው ጉዳይ ላይ ጥርት ያለ ነገር የለም።

በዚህ ጉዳይ ላይ ተጨማሪ መረጃዎችን እየተከታተልን የምናቀርብ መሆኑን ከወዲሁ እንጠቁማለን።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ