የሸገር ደርቢ ትዕይንት – የአሸናፊ ሲሳይ እና አንዳርጋቸው ሰለሞን ትውስታ

በሸገር ደርቢ ጨዋታዎች ከስፖርት ቤተሰቡ አዕምሮ ከማይጠፉ ክስተቶች አንዱ የሆነው በ1994 ጎል ከተቆጠረ በኃላ በአስቆጣሪዎቹ በኩል የነበረው የደስታ አገላፅ ሁኔታን በትውስታ አምዳችን ተመልክተነዋል።

ሁለቱ የመዲናዋ ክለቦች በ1975 የመጀመርያውን የደርቢ ጨዋታቸውን ካደረጉበት ጨዋታ ማግስት አንስቶ በተገናኙባቸው መድረኮች ሁሉ የማይረሱ የተለያዩ ክስተቶች ተስተናግደዋል። የ1994ቱ በዝናባማው አየር አሸናፊ ሲሳይ እና አንዳርጋቸው ሰለሞን ጎል አስቆጥረው የደስታቸውን የገለፁበት ትዕይንት ደግሞ በብዙዎች ዘንድ አይዘነጋም። በጨዋታው ቀድሞ ጎል ያስቆጠረው ኢትዮጵየ ቡና ሲሆን የጎሉ ባለቤት የመስመር ተከላካዩ አንዳርጋቸው ሰለሞን ነበር። አዳርጋቸው ጎሉን ካስቆጠረ በኃላ ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖንሰር አርማ በመሄድ በእግሩ በመርገጥ ደስታውን ይገልፃል። በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ተቀይሮ የገባው አጥቂው አሸናፊ ሲሳይም የአቻነት ጎል ያስቆጥርና አዳርጋቸው በእግሩ የረገጠውን አርማ በመሳም አፀፋዊ ምላሽ ሰጥቷል። ይህን ብዙም በእግርኳሳችን ያልተለመደውን አፀፋዊ የደስታ አገላለፅ ባለጉዳዮቹን አሸናፊ ሲሳይ እና አዳርጋቸው ሰለሞን ወደ ኋላ አስራ ስምንት ዓመት በትውስታ መለስ አድርገናቸው በወቅቱ የተፈጠረውን ሁኔታ ጠይቀን ተከታዩን ምላሽ ይዘን ቀርበናል።

አዳርጋቸው ሰለሞን ” ጎል ካገባሁ በኃላ ደስታዬን በተለያዩ መንገዶች ገልጫለው። ቅዱስ ጊዮርጊስ ላይ በተለያዩ ጊዜያት ጎል አስቆጥሬ አውቃለው። ይሄን ልዩ የሚያደርገው ጎል ካስቆጠርኩ በኃላ ከጎሉ ጀርባ የጊዮርጊስ ትልቅ ማስታወቂያ (ቢልቦርድ) አለ። በወቅቱ ዝናብ ስለነበር ማስታወቂያው ላይ ወጥቼ ጨፈርኩኝ። በቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎችም ተቃውሞ ደረሰብኝ። ግን አሸናፊ ሲሳይ ተቀይሮ ገብቶ ጎል ሲያስቆጥር እኔ የረገጥኩትን ጠረገና ሳመ። በዚህ የተነሳ የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ተደሰቱ። በጊዜው የተፈጠረው ትዕይንት ይህ ነበር።”

አሸናፊ ሲሳይ “እውነት ለመናገር አንዳርጋቸው ሰለሞን በወቅቱ ያደረገውን አላስታውስም። ጊዜውም ትንሽ ረዘም ያለ ጊዜ ሆኖታል። እኔ ግን ጎሎችን ሳገባ ደስታዬን የምገልፀው ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች እና ወደ ፔፕሲ ማስታወቂያ ጋር ሄጄ ነበር። ይህም የሆነበት ምክንያት ፔፕሲ የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖንሰር ስለሆነ ለዛ ብዬ ነው ይሄን የማደርገው።”

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ