ሁለት ተጨማሪ ተጫዋቾች ሀዲያ ሆሳዕናን ለመቀላቀል ተስማሙ

ግብ ጠባቂው መሳይ አያኖ እና አማካዩ ብሩክ ቃልቦሬ ወደ ሀድያ ሆሳዕና ለማምራት ከስምነት ደርሰዋል፡፡

የቀድሞው አርባምንጭ ከተማ እና ደቡብ ፖሊስ ግብ ጠባቂ መሳይ አያኖ በአንድ ዓመት ውል ሆሳዕናን ለመቀላቀል ተስማምቷል፡፡ ደቡብ ፖሊስን ከለቀቀ በኃላ ከ2010 የኢትዮጵያ የውድድር ዓመት ጀምሮ ለሲዳማ ቡና በመጫወት ላይ የሚገኘው ተጫዋቹ ዘንድሮ ውሉ በሲዳማ ቤት መጠናቀቁን ተከትሎ ከሰሞኑ በክለቡ ሲዳማ ለመቀጠል የቃል ስምምነት ላይ ደርሶ የነበረ ቢሆንም ማረፊያው ሀዲያ ሆሳዕና መሆኑ ተረጋግጧል፡፡ መሳይ አያኖ ዛሬ ረፋድ ቡድኑን ከተቀላቀለው ሌላኛው ግብ ጠባቂ ደረጀ ዓለሙ ጋር ለቋሚነት የሚፎካከርም ይሆናል፡፡

ሌላኛው ለሀዲያ ሆሳዕና ፊርማውን ያኖረው የተከላካይ አማካዩ ብሩክ ቃልቦሬ ነው፡፡ የቀድሞው ወላይታ ድቻ እና ወልድያ ተጫዋች ባለፉት ሁለት ዓመታት ወደ አዳማ ከተማ ተመልሶ ቆይታን አድርጓል፡፡ ውሉ በአዳማ ከተማ መጠናቀቁን ተከትሎ የቀድሞው አሰልጣኙ አሸናፊ በቀለን እግር በመከተል አዳማን የለቀቀ ሌላኛው ተጫዋች መሆኑ ማምሻውን ተረጋግጧል፡፡ በቀጣዩ ዓመት ከተስፋዬ አለባቸው እና አዲስ ህንፃ ጋር ብርቱ ፉክክርን የሚያደርግም ይሆናል

ነብሮቹ እስከ አሁን ለማስፈረም ከስምምነት የደረሷቸው ተጫዋቾችን ቁጥር አስራ ሁለት አድርሰዋል፡፡

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ