በአዕምሯቸው ከሚጫወቱ አጥቂዎች አንዱ ነው። ሜዳ ውስጥ ያለውን ሳይሰስት አቅሙን ሁሉ በመስጠት የሚታወቀውና የእግርኳስ ዘመኑን በአጥቂነት ጀምሮ በተከላካይነት የጨረሰው የዘጠናዎቹ ታታሪ አጥቂ ያሬድ አበጀ ማነው?
ታሪኩ መንጀታ፣ አየለ መንጀታ፣ ዓለማየሁ መኩርያ ሌሎችም የቀድሞ ድንቅ ተጫዋቾች ከፈሩባት ሻሸመኔ ከተማ 04 ቀበሌ ከሚገኘው ካቶሊክ ሚሽን ይህ ድንቅ አጥቂ ተገኝቷል። አሰልጣኝ ጋሽ ከማል ለወዳጅነት ጨዋታ ሻሸመኔ በአጋጣሚ ተገኝተው የዚህን ታዳጊ ተጫዋች ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ እና የሚያስቆጥራቸውን ጎሎች ተመልክተው ለሀዋሳ ከነማ እንዲጫወት ለማድረግ የሙከራ ዕድል አመቻቹለት። ይህን ዕድል በአግባቡ የተጠቀው ያሬድ በ1989 መጨረሻ አካባቢ የሀዋሳ ከነማ ተጫዋች ሆነ። በጣም ፈጣን፣ ታጋይ እና ባልሸነፍ ባይነቱ የሚታወቀው ያሬድ የክልል ቡድኖች እምብዛም የአዲስ አበባ ቡድኖችን ብዙም ለማሸነፍ በሚቸገሩበት ወቅት ብቅ ያለው ሀዋሳ ከተማ ለአዲስ አበባ ቡድኖችን በመፈተን ጥሩ ተፎካካሪ ቡድን በሆነበት ጊዜ ውስጥ ከነበሩ ጠንካራ ተጫዋቾች መካከል ያሬድ አበጀ አንዱ ነው። ሀዋሳ በታሪኩ ለመጀመርያ ጊዜ የአፍሪካ ኮፌዴሬሽን ዋንጫ እንዲሳተፍ ካስቻሉ ቁልፍ ተጫዋቾች መካከልም ይመደባል።
ከሀዋሳ የስድስት ዓመታት ቆይታ በኋላ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክን እየተመላለሰ ሁለት ጊዜ ከአራት ዓመት በላይ ያገለገለው ያሬድ መከላከያ፣ መተሐራ ስኳር፣ ድሬደዋ ከተማ እና በየመን ሊግ ለአንድ ዓመት ተጫውቷል። ንግድ ባንክ በነበረው ቆይታም በ1996 የኢትዮጵያ ጥሎ ማለፍ እና የአሸናፊ አሸናፊዎች ዋንጫን ማንሳት ችሏል።
ሌላው የሻሸመኔ ልጅ መስፍን አህመድ (ጢቃሶ) ስለ ያሬድ ሲናገር ” በጣም የሚገርም ትልቅ አቅም የነበረው ተጫዋች ነው። ያሬድ እንዳውም እንደነበረው ችሎታ እና አቅም በዚህ ደረጃ ብቻ የሚጫወት አልነበረም። ከዚህ በላይ መጫወት የሚችል ትልቅ አቅም ያለው። አሰልጣኞች በሰጡት የተለያዩ ቦታዎች የሚጫወት ፣ ታታሪ እና ሁለገብ ተጫዋች ነው”። ይለዋል።
በየተጫወተባቸው ክለቦች ጎል በማስቆጠር የከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነትን ይፎካከር የነበረው ያሬድ በተለያዩ ቦታዎች በመጫወት ሲታወቅ አጥቂ በመሆን መጫወት የጀመረው የእግርኳስ ህይወቱ ወደ ኋላ በመመለስ በተከላካይነት የእግርኳስ ተጫዋችነት ዘመኑን አጠናቋል።
በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከታዳጊ እስከ ዋናው ቡድን ድረስ መጫወት የቻለው ያሬድ በተለይ በ1995 ወደ አፍሪካ ዏንጫ ለማለፍ ጫፍ ደርሶ የአንድ ደርሶ መልስ ጨዋታ ብቻ እየቀረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የቲኪ ካማራው ጊኒ ጋር የመጀመርያ ጨዋታውን በአዲስ አበባ ስታዲየም አንድ ለምንም ስታሸንፍ ብቸኛውን ጎል ያስቆጠረው ያሬድ አበጀ ነበር። በ2006 መጨረሻ ላይ የ17 ዓመት የእግርኳስ ዘመኑን አጠናቆ ጫማውን ከሰቀለ በኃላ በከፍተኛ ሊግ ተሳታፊ ለነበሩት ሻሸመኔ ከተማ እና ሀምበሪቾ ዱራሜ በዋና አሰልጣኝነት ካገለገለ በኋላ በአሁኑ ወቅት በግል የንግድ ስራ ውስጥ ይገኛል። ከዛሬው የዘጠናዎቹ ድንቅ ተጫዋች ያሬድ አበጀ ጋር ያደረግነው ቆይታ እንደሚከተለው ይቀርባል።
“የብዙ ተጫዋቾች ህልም በክለብ እና የሀገሩን መለያ ለብሶ መጫወት ነው። እኔ በዚህ ረገድ ሀገሬን ወክዬ መጫወቴ ለኔ በጣም ደስ የሚለኝ ስኬቴ ነው። ተጫዋች ሆነህ ድልን ዋንጫን ማንሳትን ትመኛለህ ሀዋሳ የጥሎ ማለፍ ዋንጫን፣ ንግድ ባንክ ደግሞ የአሸናፊ አሸናፊዎች ዋንጫ እና የጥሎ ማለፍ ዋንጫን በማንሳቴ ለኔ ስኬቴ የምላቸው እነዚህ ናቸው። በአጠቃላይ በተጫዋችነት ዘመኔ ጥሩ የሆነ ጊዜ አሳልፌአለው። በተለይ ባንክ እያለው ምርጥ አጥቂ መሆኔን አሳይቻለው።
“ይሄን አላደረኩትም ብዬ ብዙ የሚቆጨኝ ነገር የለም። ግን እግርኳስ ብዙ ጊዜ ተጫዋች ስትሆን ማሳካት የምትፈልጋቸው ነገሮች ይኖራሉ። የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫ ባነሳ ደስ ይለኝ ነበር። ይህ አለመሆኑ ያስቆጨኛል። ሌላው የሀገሬ ብሔራዊ ቡድን ለአፍረካ ዋንጫ አልፋ ተሳታፊ ባደርገት በጣም ደስ ይለኝ ነበር። ይሄም ባይሆን በተጫዋችነት ዘመኔ ብዙም የሚቆጨኝ ነገር የለም።
“ሁለት ዓይነት የአሰልጣኞች መንገድ አለ። አንደኛው የአንተን አቅም አውቆ (ተረድቶ) የሚጠቀም አለ። ሁለተኛ ደግሞ የሌለህን ነገር እየሰጠህ፣ እያበቃህ የሚጠቀምብህ አሰልጣኝ አለ። ለኔ ነፍሱን ይማረው እና በአሰልጣኝ ሥዩም አባተ ስር ማለፌ በጣም ደስተኛ ነኝ። ለእርሱ ትልቅ ክብር አለኝ። በብዙ አሰልጣኞች ስር አልፌያለው። የእርሱ ግን ለየት የሚለው እያበቃ፣ እየሰጠህ የሚያዘጋጅህ አሰልጣኝ ነው።
“ከተጫወትኩባቸው ክለቦች ሁሉ ለኔ ትልቅ ትውስታ ያለኝ በሀዋሳ ከነማ ነው። የነበረን ህብረት እና አንድነት የሚገርም ነበር። ፕሪምየር ሊጉ ሲጀመር ይከፈለን የነበረን ደሞዝ ሁለት መቶ ሰማንያ ብር ነበር። ግን በዛ ሰዓት የነበረው የመጫወት ፍላጎታችን የተለየ ነበር። በዛን ወቅት ከነበረን ጥንካሬ አንፃር ማንም ቡድን ሀዋሳ ላይ መጥቶ አሸንፎን አያቅም። በአጠቃላይ ያን ቡድን መቼም የማረሳው ነው። ወደ አሰልጣኝነቱ ከመጣው በኋላ ብዙ ተጫዋቾች የሚቸገሩት ይሄ ነው ለምን እንደሚጫወቱ እና ለሙያው ትኩረት ያለመስጠት ሁኔታዎችን እታዘባለው። እኛ እንጫወት የነበረው ለገንዘብ ብቻ አልነበረም። ትልቅ ደረጃ ለመድረስ፣ ብሔራዊ ቡድን ለመጫወት እናስብ ነበር።
“በብሔራዊ ቡድን ቆይታዬ ተከታታይነት ያለው ጥሪ ቢደረግልኝም ብዙም የመጫወት ዕድሉን አላገኘሁም። ሆኖም ግን በተመረጥኩባቸው ግዜያት ሁሉ ሀገሬን አገለግያለው። ያው የመጠራት መልሶ የመቀነስ ሁኔታዎች የነበሩ በመሆኑ የምፈልገውን ያህል ለብሔራዊ ቡድን ተጫውቻለው አልልም።
“በተለያዩ ቦታዎች ተጫውቻለው ከግብጠባቂነት በቀር። ከአጥቂ ጀርባ፣ አማካይ፣ የመሐል ተከላካይ፣ የመስመር ተከላካይ እንዲሁም የመጨረሻ አጥቂ ሆኜ ተጫውቻለው። አሰልጣኞች የሚሰጡኝን አጨዋወት አክብሬ እሰራ ነበር። በዚህም ብዙ አሰልጣኞች በኔ ደስተኛ ነበሩ። ወደ እግርኳስ ማቆምያዬ አካባቢ ወደ ተከላካይነቱ አድልቼ መጫወት ችያለው። ይሄም ቢሆን በተለይ ባንክ እያለው የመጨረሻ አጥቂ በመሆን በርከት ያሉ ጎሎችን አስቆጥሬአለው።
“መሸነፍን አልወድም በዚህ ምክንያት ሜዳ ውስጥ አብረውኝ ከሚጫወቱት ጋር ጭቅጭቅ ውስጥ እገባለው። ይሄ ላለመሸነፍ ከነበረኝ ባህሪ የመጣ ነው። በተረፈ ለተቃታኒ ቡድን፣ ለዳኞች ትልቅ አቅብሮት አለኝ። በአስራ ስድስት ዓመት የተጫዋችነት ቆይታዬ አንድም ቀን ቀይ ካርድ ተመልክቼ አላቅም። በተለይ ባንክ እያለው ሲኒየር ተጫዋች እንደ መሆኔ መጠን እነ ዳዊት እስጢፋኖስ ፣ መልዐከ መስፍን እና በረከት አዲሱን እየመከርን ልምዳችንን እያካፈልን አሳድገናል። ሜዳ ላይ የመቆጣት ነገር የማሳየው ላለመሸነፍ ካለኝ እሳቤ እንጂ ባህሪዬ መልካም ነው።
“እግርኳስን ካቆምኩ በኃላ ወደ ንግድ ዓለም ገብቼ የግሌን ስራ እየሰራው ባለበት ወቅት የሻሸመኔ እግርኳስ ክለብ አመራሮች መጥተው በጠየቁኝ መሰረት በምክትል አሰልጣኝነት ሻሸመኔ መስራት ጀመርኩ። በኋላ ወደ ዋና አሰልጣኝነት በመምጣት ወደ አራት ዓመት ሠርቻለው። ከዚህ በኃላ ውጤት እየጠፋ ሲመጣ ወደ ሀንበሪቾ ክለብ በመሄድ አሰልጥያለው። ያለፉትን አንድ ዓመታት ከአሰልጣኝነቱ በመውጣት በንግድ ስራ ላይ እገኛለው። ወደ ፊት ሁኔታዎች ከተመቻቹ ያለኝን ልምድ፣ እውቀት ተጠቅሜ ወደ ስራ ለመቀየር አሰልጣኝ ሆኜ ተመልሼ ብሰራ ደስ ይለኛል። ሞክሬ አለው በጣም ጥሩ ነገር እንዳለኝ አውቃለው። ወደ አሰልጣኝነቱ ተመልሼ ብሰራ በርግጠኝነት ጥሩ ነገር እንደማደርግ እገምታለው።
“ሀዋሳ ከነማ እያለው ለኮፌዴሬሽን ካፕ ጨዋታ ናይጄርያ ሄደን ነበር። እቃ ልንገዛ ሁላችንም በሞተር ተበታትነን ሄድን እቃውን ገዝተን ስንመለስ የመጣንበት መንገድ ጠፍቶን ወደ ሆቴል መመለስ አቃተን። ጠዋት የወጣን እስከ ማታ ስንከራተት ውለን ማንም ሊረዳን ሊነግረን አልቻልንም። በመጨረሻም ፖሊሶች መጥተው የወሰዱን ጊዜን መቼም የማረሳው ገጠመኝ ነው።
“በትልቅ ውድድር ማለት በፕሪምየር ሊግ ውድድር የመጀመርያ ጎሌን ያስቆጠርኩት በሀዋሳ ሜዳ ጉና ላይ ነው። የመጨረሻ ጎሌ ድሬደዋ እያለው የቀድሞ ክለቤ ንግድ ባንክ ላይ ነው። መቼም ካገባዋቸው ጎሎች ሁሉ የማረሳው ኢትዮጵያ ቡና ላይ የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ ከማዕዘን ምት ተሻግሮ ተደርቦ ሲመለስ አክርሬ በመምታት ያስቆጠርኩት ጎል ለኔ ልዩ ስፍራ አላት።
“አሁን ያለው የኢትዮጵያ እግርኳስ ካለው ወቅታዊ ሁኔታ አንፃር ጠንካራ ነው ብሎ መናገር ይከብደኛል። ብዙ የተቀዛቀዘ እና ብዙ አስደሳች ነገር የማትመለከትበት ነው። በፊት የነበረው የመጫወት ፍላጎቱ ፣ የጨዋታው ፍሰት አሁን ካለው ጋር ምንም የሚገናኝ አይደለም። ለምን እየወረደ እንደመጣ አላቅም ። በፊት ከነበረው ጋር ባላንስ ለማድረግ ይከብደኛል። እኔ በግሌ ቀንሷል ባይ ነኝ።
“የቤተሰብ ህይወቴ ባለ ትዳር እና የሦስት ልጆች አባት ነኝ። ሁለት ወንድ አንዷ ሴት ናት ። ሁለቱ ወንድ ልጆች የአስር እና የዘጠኝ ዓመት ልጆች ናቸው። እግርኳስ ተጫዋች የመሆን ፍላጎት አላይባቸውም የበለጠ ትምህርታቸው ላይ እንዲያተኩሩ ነው ፍላጎቴ። ወደ ፊት የሚሆነውን ባላቅም እስካሁን ስመለከታቸው ኳስ ተጫዋች የመሆን ፍላጎት አላይባቸውም።
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!
© ሶከር ኢትዮጵያ