ይህንን ያውቁ ኖሯል? (፰) | የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ እና አሰልጣኞች

ሶከር ኢትዮጵያ በ”ይህንን ያውቁ ኖሯል?” አምዷ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግን የተመለከቱ እውነታዎችን በተከታታይ ስታቀርብ ቆይታለች። ዛሬም ሊጉ እና አሰልጣኞችን የተመለከቱ እውነታዎችን አጠናክራ ቀርባለች።

– የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በአዲስ መልክ 1990 ከጀመረ በኋላ በተጫዋችነት እና በአሰልጣኝነት ዋንጫ ያነሳ ግለሰብ ፋሲል ተካልኝ ነው። የአሁኑ የባህር ዳር ከተማ አሰልጣኝ በተጫዋችነት ዘመኑ በ1991 እና 1992 እንዲሁም በአሰልጣኝነት (በውድድር ዓመቱ ምክትል አሰልጣኝ ሆኖ እርከ ዓመቱ አጋማሽ ከመራ በኋላ የኔይደር ዶሳንቶስን መልቀቅ ተከትሎ ነበር ዋና አሰልጣኝ የሆነው) በ2007 ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ዋንጫ ማንሳቱን ተከትሎ ነው ብቸኛው ባለታሪክ የሆነው።

– በአንድ የውድድር ዓመት ከአንድ በላይ አሰልጣኞች እየተመሩ ዋንጫ ያነሱ ክለቦች ደደቢት እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ናቸው። ደደቢት በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የሊጉን ዋንጫ ባገኘበት የ2005 የውድድር ዓመት አብርሃም ተክለሃይማኖት እና ንጉሴ ደሥታ ክለቡን ሲመሩ ቅዱስ ጊዮርጊስ ደግሞ በሦስት አጋጣሚዎች ላይ በሁለት አሰልጣኞች እየተመራ ቻምፒዮን ሆኗል። 2006 ላይ ማርት ኑይ እና ሬኒ ፌለር፣ 2007 ላይ ኔይደር ዶሳንቶስ እና ፋሲል ተካልኝ እንዲሁም 2008 ላይ ማርቲን ኩፕማን እና ማርት ኑይን በውድድር ዓመቶቹ ተቀያይረው ዋንጫ አንስተዋል። 2004 ላይ ዱሳን ኮንዲች እና ዳኔሎ ፔርሉዊጂ ቅዱስ ጊዮርጊስን ቢመሩም ኮንዲች ሊጉ ሳይጀመር ከክለቡ ጋር ተለያይተዋል።

– በተከታታይ ዓመታት የሊጉን ዋንጫ በማንሳት ቀዳሚው አሰልጣኝ ሰርዲዮቪን ሚሉቲን ሚቾ ነው። ሚቾ ቅዱስ ጊዮርጊስን ከ2000-02 ዓመት ድረስ ባሰለጠነበት 3 ተከታታይ የውድድር ዓመታት የሊጉን አሸናፊነት ተጎናጽፎ ነበር። ከሚቾ በመቀጠልም ገብረመድህን ኃይሌ በ2010 እና 2011፣ አሥራት ኃይሌ በ1991 እና 1992 እንዲሁም ሥዩም ከበደ በ1994 እና 1995 የሊጉን ዋንጫ በተከታታይ ሁለት ጊዜ አግኝተዋል።

– የሁለተኛውን እና የአንደኛውን የሃገሪቱን የሊግ እርከን ዋንጫ ያገኙ ብቸኛ አሰልጣኝ አሥራት ኃይሌ ናቸው። አሥራት ቅዱስ ጊዮርጊስን እየመሩ በ1990 የ2ኛ ዲቪዚዮን ዋንጫን አንስተው ወደ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ካለፉ በኋላ በ1991 እና 1992 የሊጉን ዋንጫ አሸንፈዋል።

– በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ እያሰለጠኑ ከሚገኙ አሰልጣኞች ውስጥ ከተለያዩ ክለቦች ጋር ዋንጫ ያነሱ አሰልጣኝ ገብረመድህን ኃይሌ ብቻ ናቸው። ገብረመድህን በ2010 ከጅማ አባጅፋር ጋር በ2011 ደግሞ ከመቐለ 70 እንድርታ ጋር ዋንጫ ማንሳታቸው ይታወቃል።

– በሊጉ ለረጅም ጊዜ አንድን ክለብ ያሰለጠኑ የውጪ ዜጋ አሰልጣኝ ሰርዲዮቪን ሚሉቲን ሚቾ ናቸው። ሚቾ ቅዱስ ጊዮርጊስን ለ5 ዓመታት በማሰልጠናቸው ነው በሊጉ ብቸኛው አሰልጣኝ የሆኑት። ከሚቾ በመቀጠል ማርት ኑይ በተመሳሳይ በቅዱስ ጊዮርጊስ ለሁለት ዓመት ከግማሽ በማሰልጠን 2ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

– ባሰለጠኑበት ዓመት ሁሉ ዋንጫ ያነሱ ብቸኛ አሰልጣኝ ሰርዲዮቪች ሚሉቲን ሚቾ ናቸው። አሰልጣኙ ፈረሰኞቹን በመሩበት በ1997፣ 1998፣ 2000፣ 2001 እና 2002 ዋንጫዎችን ለክለቡ አስገኝተዋል።

– የሊጉ ኮከብ አሰልጣኝ በተለምዶ የሚመረጡት ዋንጫ ካነሱ ክለቦች ውስጥ ነው። ቡድኖቹ ዋንጫ ባገኙበት የውድድር ዓመት ለጥቂት ጨዋታዎች ዋና አሰልጣኝ የሆኑ አሰልጣኞች ጭምር ኮከብ አሰልጣኝ ተብለው ተመርጠዋል። ለአብነትም ንጉሤ ደስታ እና ሬኔ ፌለር ቡድኖቻቸውን ከሁለተኛ ዙር በኋላ መርተው ኮከብ ተብለው ተመርጠዋል።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ