ባህር ዳር ከተማ የወሳኝ ተጫዋቹን ውል ለማደስ ተስማማ

ከሳምንታት በፊት ለፋሲል ከነማ ለመጫወት ተስማምቶ የነበረው ፈጣኑ የመስመር አጥቂ ውሉን በጣና ሞገዶቹ ቤት ማደሱ ታውቋል።

ቡድናቸውን ማጠናከር ላይ ተጠምደው የሚገኙት ባህር ዳር ከተማዎች ከዚህ በፊት የ13 ነባር ተጫዋቾችን ውል ማደሳቸው ይታወቃል። ከነባሮቹ በተጨማሪ 4 አዳዲስ ተጫዋቾችን ወደ ስብስባቸው ለመቀላቀል መስማማታቸው ይታወሳል። ከደቂቃዎች በፊት ደግሞ የመስመር ተጫዋቹ ግርማ ዲሳሳን ውል ለሁለት ዓመታት አድሰዋል።

ይህ ፈጣን የመስመር አጥቂ ከሳምንታት በፊት ለፋሲል ከነማ ለመጫወት ተስማምቶ የነበረ ቢሆንም ዛሬ ከባህር ዳሮች ጋር ባደረገው ስምምነት ውሉን እንዲያድስ ሆኗል። ተጫዋቹ በተለይ ፍጥነቱን ተጠቅሞ በሚያደርጋቸው ጥሩ እንቅስቃሴዎች ለባህርዳሮች መልካም ግልጋሎትን በመስጠት ይቀጥላል ተብሎ ይጠበቃል።

ባህር ዳር ከተማዎች ከዚህ በፊት የዜናው ፈረደ፣ የፍቅረሚካኤል ዓለሙ፣ የደረጄ መንግስቱ፣ የኃይለየሱስ ይታየው፣ የሚኪያስ ግርማ፣ የወሰኑ ዓሊ፣ የሳላምላክ ተገኝ፣ የሳምሶን ጥላሁን፣ የአቤል ውዱ፣ የፅዮን መርዕድ፣ የሳሙኤል ተስፋዬ፣ ፍፁም ዓለሙ እና የሰለሞን ወዴሳን ውል ለ2 ዓመታት ማደሳቸው ይታወቃል።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ