ፌዴሬሽኑ ከነገ ጀምሮ ከክለቦች ጋር ውይይት ያደርጋል

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በ2013 በሚደረጉ ሁሉም የሊግ ውድድሮች ዙሪያ ከነገ ጀምሮ ከክለቦች ጋር ንግግር ይጀምራል፡፡

የ2012 በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ስር የሚካሄዱ ውድድሮች ከመጋቢት ወር ወር አጋማሽ ጀምሮ መቋረጣቸው ይታወሳል፡፡ የመቋረጡ መንስኤ ደግሞ በዓለማችን ብሎም በሀገራችን የተንሰራፋው የኮቪድ 19 ቫይረስ እንደሆነ ይታወሳል፡፡ በሽታውም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋ በመምጣቱ ሊጉን ለማካሄድ አዳጋች በመሆኑ ሁሉም የእግር ኳስ ውድድሮች ሙሉ በሙሉ እንዳልተካሄዱ ተቆጥረው እንዲሰረዙ በቅርቡ ውሳኔ መተላለፉ ይታወቃል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ በቀጣዩ ዓመት ውድድሮችን ዳግም ለማስጀመር ፌዴሬሽኑ ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት የመነሻ ሀሳብ በሰነድ መልክ ያቀረበ ሲሆን በቀረቡ ሀሳቦች ዙሪያ የክለቦችን ሀሳብ ለመስማት እና ጥልቅ ውይይት ለማድረግ ከነገ 3፡00 ጀምሮ በካፍ አካዳሚ የስብሰባ አዳራሽ ከፕሪምየር ሊግ፣ ከፍተኛ ሊግ እንዲሁም ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የክለብ ቦርድ አመራሮች እና ተወካዮች ጋር ቀጠሮ የያዘ ሲሆን ቅዳሜ ደግሞ የአንደኛ ሊግ ክለቦችን በማካተት ውይይት እንደሚደረግ ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ይጠቁማል፡፡

ነገ በሚጀመረው በዚህ ስብሰባ ላይ በዋናነት በ2013 የውድድር ዘመን አጀማመር ላይ እንዲሁም ፌዴሬሽኑ ለመንግስት ባቀረበው ሰነድ ዙሪያ ጥልቅ ውይይት ይደረጋል ተብሏል። ከዚህም በተጨማሪ ውድድሩን ለማስጀመር ክለቦች ማሟላት ያለባቸው ጉዳዮች ላይ በስፋት ይነጋገራል ተብሏል፡፡

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ