ሜዳ ውስጥ የሰው ህይወት የዳነበት አጋጣሚ – የበኃይሉ አሰፋ ትውስታ

“ፈጣሪ እሱን ለማዳን እኔን መረጠ እንጂ ያን ያህል እውቀት የለኝም”

“በኃይሉን ሕይወቴን ስላዳነልኝ በጣም ላመሰግነው እፈለጋለሁ”

በ2003 የውድድር ዓመት ከተከሰቱ በርካታ አነጋጋሪ ጉዳዮች አንዱ ሙገር ሲሚንቶ እና ደደቢት ባገናኘው ጨዋታ የተከሰተው አስደንጋጭ አጋጣሚ አንዱ ነው። ዳንኤል መኮንን የተባለ የሙገር ሲሚንቶ ተጫዋች ኳስ ለማግኘት በሚያደርገው ጥረት ከጋናዊው ጋብርኤል አሕመድ ጋር ተጋጭቶ የምላስ መንሸራተት በማጋጠሙ (በተለምዶ ምላስ በመዋጡ) በወቅቱ የደደቢት የመስመር አማካይ በኃይሉ አሰፋ (ቱሳ) ጥረት በህይወት ለመትረፍ ችሏል።

በወቅቱ የተጫዋቹን ህይወት አድኖ በፌደሬሽኑ የልዩ ተሸላሚ የነበረው የቀድሞ የሀዋሳ ከተማ ፣ ደደቢት ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አማካይ ሁኔታውን እንደሚከተለው ያስታውሰዋል።

” ጉዳቱ አስደንጋጭ ነበር ተጫዋቹ ዳንኤል መኮንን ይባላል። ከሻይቡ ጋር ተጋጭቶ ነው ከበድ ያለ ሁኔታ ውስጥ የገባው፤ ሁኔታውም የምላስ መዋጥ ነበር። እኔ በቅርብ ርቀት ነበርኩ፤ ሌሎች ተጫዋቾቹ እየሸሹት አይቼ ስጠጋው ነው ምላሱን መዋጡን ያስተዋልኩት። ከዚህ በፊት ተመሳሳይ ሁኔታ አጋጥሞ በቅርብ ርቀት ሆኜ ተከታትያለው። ሀዋሳ ከተማ እያለው ፍቃዱ የሚባል ግብ ጠባቂ በተመሳሳይ ምላሱን ውጦ የቡድናችን ሀኪም ሲረዱት በቅርበት ስላየሁ የዳንኤልንም ሁኔታ ካስተዋልኩ በኃላ ተጠግቼ ነፍሱን ለማትረፍ ጥረት አደረኩ። በሰዓቱ የተጫዋቹ ሁኔታ በጣም ያሳዝን ነበር ልጁ ህይወቱ በሜዳ ብያልፍ ሀዘኑ ከባድ ይሆን ነበር።

” እግዚአብሔር እሱን ለማዳን እኔን መረጠ እንጂ ያን ያህል እውቀት የለኝም። መጀመርያ ምላሱ የመተንፈሻ አካሉን ሙሉ ለሙሉ እንዳይዘጋው ነበር ያደረግኩት። ከዛ በኃላ ደግሞ መንጋጋውን ፈቀቅ ማድረግ ትንሽ ከባድ ነበር። እጄ ላይም ትንሽ ተነክሼ ነበር፤ ከዛ ጥረት በኃላ ግን ህይወቱን ስላዳንኩ በጣም ነው ደስ ያለኝ። ተጫዋቾቹም ደስ ብሏዋቸዋል፤ ጨዋታውን ለማየት ሜዳ ውስጥ የነበረ አንድ ዶክተርም እኔን በማበረታታት ብዙ ጥረት አድርጓል፤ ከሁኔታው ትንሽ ዘግየት ብሎ ነበር የመጣው።

” ከተጫዋቹ በስልክም ምናምን እንገናኛለን። ምላሹ በጣም ነው የሚገርመው፤ በጣም ነው የሚያመሰግነኝ። እኔም የምችለውን አድርጌ የሰው ህይወት ስላዳንኩ በጣም ደስተኛ ነኝ። ”

በሰዓቱ ሜዳ ውስጥ ጉዳት ያጋጠመው እና ከዚህ ቀደም በጥቁር ዓባይ፣ ወሎ ኮምቦልቻ እና ናሽናል ሴሜንት ተጫውቶ በዚህ ወቅት በፌደራል ፖሊስ ክለብ የሚገኘው ዳንኤል መኮንንም ሀሳቡን ገልጾልናል።
“ጨዋታው ላይ ዝናብ ነበር፤ ጨዋታው ሊያልቅ ወደ ሦስት ደቂቃ ሲቀረው ነው ይህ ነገር ያጋጠመው። ልክ ጋብርኤል ኳሳን ሊመታት ሲል እኔ ዝናቡ አንሸራቶኝ ከጉልበቱ ጋር ተጋጨሁ፤ የጉዳቱ መነሻ ይህ ነው። ከዛ በኃላ መተንፈስ ነው እንጂ ሜዳ ውስጥ የማስታውሰው ነገር አልነበረም። ግን ጨዋታው ላይ ጥሩ እንደነበርኩ እና ከዛ በኃላ የነበረውን ሁኔታ ጓደኞቼ ነግረውኛል። ከበኃይሉ ጋር ከዛ በኃላ ጥሩ ጓደኝነት ነው ያለን። ምንም እንኳ በአካል ብዙም ባንገናኝም እንደዋወላለን። በኃይሉ በጣም ጥሩ ሰው ነው፤ በዚህ አጋጣሚ ሕይወቴን ስላዳነልኝ በጣም ላመሰግነው እፈለጋለሁ።”

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ