ስለ ተክሌ ብርሀኔ (ገመዳ) ሊያውቋቸው የሚገቡ እውነታዎች

“ሜዳ ውስጥ አራት ነገሮችን ማድረግ የሚችል ብቸኛ ተጫዋች ነው፤ አብዶኛ፣ ነጣቂ፣ የጎል እድል ፈጣሪ እና ጎል አስቆጣሪ” በማለት ብዙዎች የሚመሰክሩለት በዘመኑ ከተዋጣላቸው አማካይ መካከል አንዱ የነበረው ባለ ብዙ ተስዕጦው የዘጠናዎቹ ድንቅ አማካይ ተክሌ ብርሀኔ (ገመዳ) ማነው?

በአዲሱ ሚሌኒየም ወቅት ኢትዮጵያ የአፍሪካ የአትሌቲክስ ውድድርን ባዘጋጀችበት ወቅት ለልምምድ እና ለተለያዩ ዝግጅቶች እንዲውል በሚል አዲስ አበባ ስታድየም አጠገብ የሚገኘው “ሲ ሜዳ” ታጥሮ መቅረቱ ይታወቃል። ይህ ሜዳ ለአትሌቲክስ ውድድር ተብሎ ከመዘጋቱ አስቀድሞ ለኢትዮጵያ እግርኳስ ዕድገት አስተዋፆኦ ያደረጉ በርካታ እግርኳሰኛ ትውልድን ያፈራ ሜዳ ነበር። የዛሬው የዘጠናዎቹ ኮከብ እንግዳችን የሆነው ድንቁ አማካይ ተክሌ ብርሀኔም ምንም እንኳን ትውልዱ ትግራይ ክልል ቢሆንም እድገቱ አዲስ አበባ ፍል-ውሀ አካባቢ ነው። ለፍል-ውሀ በቅርብ ርቀት በሚገኘው ደግሞ “ሲ ሜዳ” ነበር። ጋሽ ታዴ እያሰለጠኑት እግርኳስ ተጫዋች የመሆን ህልሙን መኖር የጀመረው ተክሌ በክለብ ደረጃ ለመጀመርያ ጊዜ በ “ሲ” ታዳጊ ቡድን መጫወት የጀመረው ለጭማድ (ጭነት ማመላለሻ) ቡድን በመጫወት ነበር።

በመቀጠል በ1982 መድን ቢ በመግባት ብዙም ሳይቆይ ወደ ዋናው ቡድን በማደግ ለአስር ዓመት መድንን አገልግሏል። በቆይታውም በኢትዮጵያ እግርኳስ ታሪክ ከፍተኛ ስኬት የሆነው በካፍ ካፕ መድን ለግማሽ ፍፃሜ በደረሰበት ወቅት የተክሌ አበርክቶ ቀላል የሚባል አልነበረም። የናሚቢያውን ቡድን አዲስ አበባ ስታዲየም ሰባት ለዜሮ ሲያሸንፉ በጨዋታው ላይ ሐት-ትሪክ በመስራት አቅሙን አሳይቷል። በጣም የሚገርመው ይህ በአፍሪካ መድረክ አስገራሚ ግስጋሴን አሳይቶን የነበረው መድን በዓመቱ ላለመውረድ እና በሊጉ ለመቆየት ወሳኝ ጨዋታ ከኪራይ ቤት ጋር ተጫውቶ 2-1 ሲያሸንፍ ወሳኙን የመጨረሻ ጎል አስቆጥሮ መድንን ከመውረድ ያተረፈው ተክሌ ብርሀኔ ነበር።

በ1993 በማስተር ቴክኒሻን ጋሽ ሀጎስ ደስታ ጥሪ አማካኝነት ኤልፓን ተቀላቅሎ በዚሁ ዓመት ኤልፓ የሦስትዮሽ ዋንጫ እንዲያነሳ ከማስቻሉ በተጓዳኝ ዮርዳኖስ ዓባይ 24 ጎል አስቆጥሮ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ በመሆን ሪከርዱን ሲሰብር አብዛኛውን ለጎሎች የሚሆነውን ኳሶችን አመቻችቶ ያቀበለው ተክሌ ብርሀኔ እንደነበረ ብዙዎች ይናገራሉ።

ምርጡ አጥቂ ዮርዳኖስ አባይ ስለ ተክሌ ብርሀኔ ሲመሰክር እንዲህ ይላል። ” ኳስ የማይበላሽበት፣ ከአጥቂዎች ጋር በደብል ፓስ ወደ ፊት የሚጫወት፣ ለአጥቂዎች የመጨረሻ ለጎል የሚሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ የሚሰጥ፣ በተለይ ከኔ ጋር የነበረው ጥምረት መቼም የማልዘነጋው ነው። ከአስራ አንድ ምርጥ ተጫዋቾች መካከል በአማካይ ስፍራ የኔ ቀዳሚ ምርጫዬ የሆነ በጣም የማከብረው ድንቅ ተጫዋች ነው ተክሌ ብርሃኔ” በማለት ይናገራል።

ከመብራት ኃይል ጋር ከተለያየ በኃላ ወደ ጉና አምርቶ ለአንድ ዓመት ተጫውቷል። በተለይ ወደ በብሔራዊ ሊግ ወርዶ የነበረው ጉና ዳግም ወደ ሊጉ ለመመለስ አሰልጣኝ አብርሀም ተ/ሀይማኖት የተክሌ እገዛ አስፈልጓቸው ነበር። ጉናዎች ያሰቡት እቅዳቸው ተሳክቶ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ለመመለስ ሲችሉ የተክሌ ሚና የጎላ የነበረ ሲሆን በወቅቱም የብሔራዊ ሊጉ ኮከብ ተጫዋች ተሸላሚ መሆን ችሏል።

አልሸነፍ ባዩ እና ባለተሰጥዖው ተጫዋች ለአስር ጨዋታ ብቻ የነበረበትን ክፍተት ለመሙላት ከጉና በውሰት ቅዱስ ጊዮርጊስ ወስዶት የ1995 ዋንጫን እንዲያነሳ ማድረግ ችሏል። በአዳማ ከተማ ለዓመታት ከተጫወተ በኋላም በመጨረሻ በአሮጌው ሚሌንየም መባቻ የእግርኳስ ህይወቱን አጠናቆ ጫማውን በመስቀል አሁን ወደሚኖርበት ሲውዘርላንድ አቅንቷል።

በተክሌ ብቻ ያልቆመው ተጫዋችነት ወደ ቤተሰቡ አምርቶ ታናሽ ወንድሙ ሀብቶም ብርሀኔ ከመድን ሲ ቡድን ጅማሮውን አድርጎ በዋናው ቡድን ተጫውቶ በመቀጠል በመብራት ኃይል፣ ትራንስ ኢትዮጵያ ፣ አዳማ ከተማ እና ሀዋሳ ከተማ መጫወቱ ይታወቃል።

ብዙ ያልተወራለት ይህ ድንቅ አማካይ እንደነበረው ልዩ ችሎታ በወቅቱ የነበሩት የብሔራዊ ቡድን አሰልጣኞች በተደጋጋሚ ጥሪ ቢያቀርቡለትም የመጫወት ዕድል በመንፈጋቸው ሀገሩን በሚገባ አለማገልገሉ አስገራሚ ነው። በጉና አብሮት የተጫወተው ዳንኤል ፀሐዬ ስለ ተክሌ ብርሀኔ ሲናገር ” በእኔ እምነት በሀገሪቷ ውስጥ ከነበሩ ከማምንባቸው ድንቅ አማካዮች መካከል አንዱ ነው። የነበረው አቅም በጣም የሚገርም ነው። ኳስ ይዞ ቀድሞ የሚመለከተው አጥቂዎችን ብቻ የነበረ የጎንዮሽ ኳስ የማያበዛ ፊት ለፊት ለሚገኙ አጥቂዎች የመጨረሻ ኳስ አመቻችቶ የማቀበል አቅሙ ከፍተኛ የነበረ ነው። ዕይታው፣ ቡድን እና ጨዋታ የማንበብ አቅሙ የሚገርም ነበር። በችግር ሰዓት ኳስ አምጣ ብሎ በድፍረት በመቀበል ተጨናንቆ የነበረውን የሜዳ ክፍል በተን አድርጎ ቡድንህን ባላንስ የሚያደርግ፣ የዛኑ ያህል ጎል አግቢ የነበረ ድንቅ ተጫዋች ነው” ይለዋል።

ከሀገር ከወጣ አስራ ሁለት ዓመት የሆነው ተክሌ በዘጠናዎቹ ኮከብ አምዳችን ካለበት ሲውዘርላንድ ሀገር ፈልገን አግኝተነው በወቅቱ ስለነበረው የእግርኳስ ህይወቱ ይሄን አጋርቶናል። መልካም ቆይታ።

“በመጀመርያ አክብራቹ ስላናገራቹሁኝ በጣም አመሰግናለው። በእግርኳስ ተጫዋችነት ዘመኔ ብዙ ያሳካኋቸው ስኬቶች ነበሩኝ። መድን ቤት እያለው ፕሪምየር ሊግ ዋንጫ አላንሳ እንጂ የተለያዩ የማጠናከርያ ዋንጫ ከተዘጋጀ መድን ሁሌ ያሸንፍ ነበር። በተለይ ለካፍ ካፕ (ኮፌዴሬሽን ዋንጫ) ግማሽ ፍፃሜ የበቃንበት ጊዜ ለኔ ትልቁ ስኬት ነው። መብራት ኃይል እያለሁ የ1993 የሦስትዮሽ ዋንጫ በማንሳት የማይረሳ ጥሩ ጊዜ አሳልፌያሁ። ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ለስድስት ወር በነበረኝ የውሰት ቆይታም የፕሪምየር ሊግ ዋንጫ አንስቻለው።

“በእግርኳስ ተጫዋችነት ህይወቴ ይሄን አላደረኩም ብዬ የምቆጭበት ነገር የለም። ፈጣሪ ይነስገን የህዝብን ፍቅር አግኝቼበታለሁ። ሜዳ ላይ በነፃነት የምፈልገውን እንቅስቃሴ አሳይቻለሁ። በዚህም በጣም ደስተኛ ነኝ።

“በመብራት ሀይል የዛን የማይረሳ ውብ ጊዜ አሳልፌያለው። በመብራት ኃይል ቆይታዬ በእግርኳስ ህይወቴ ከውጤት አንፃር በጣም የተደሰትኩበት በጣም ውብ የሆነ ጊዜ ነው። ጋሽ ሀጎስ የሰሩት ቡድን የሚገርም ስብስብ ነበር። የነበረው የቡድን ህብረት ምን ብዬ ልንገርህ ልዩ ቦታ የምሰጠው ክለቤ ነው።

“ዮርዳኖስ ዓባይ ላስቆጠራቸው ጎሎች አመቻችቶ በማቀበል የኔ ሚናን በተመለከተ ያው ተመልካች ነው የሚፈርደው። ዮርዳኖስ ልዩ ችሎታ የነበረው ተጫዋች ነው። ለእርሱ ለጎል የሚሆኑ ኳሶች እንድታቀበልው የሚያስገድዱት ተጫዋች በመሆኑ እግሬ ኳስ ሲገባ ቀድሜ የማየው እርሱን ነው። እንዲሁም በግሌ እኔ ከማገባ ይልቅ የማቀብላቸውም ኳሶች ውጤት ላይ ሲያርፉ ሳይ የምደሰት ተጫዋች በመሆኔ ይመስለኛል ይሄን የማደርገው። ዮርዳኖስም ይሄን ነገር ብዙ ጊዜ ይናገረዋል መሰለኝ። እኔ በዚህ መልኩ ነው የማየው።

“ከመብራት ኃይል በኃላ በ1995 ወደ ጉና ነው ያመራሁት። አጋጣሚ ሆኖ ጉና ብሔራዊ ሊግ የወረደበት ስለሆነ የማነህ፣ ሚካኤል አብርሃ፣ ዳንኤል ፀሐዬ፣ ዮሴፍ ኪዳኔ ይሆኑና ከአብርሐም ተክለሃይማኖት ጋር በመሆን አነጋገሩኝ። እኔም ደስተኛ ሆኜ ወደ ጉና ሄድኩ። እጅግ የሚገርም አሪፍ ቤተሰባዊ የሆነ ጥሩ ጊዜ ነበር ያሳለፍኩት። በመጨረሻም ጉናን ወደ ፕሪምየር ሊግ አስገባንና እኔ በግሌ የብሔራዊ ሊጉ ኮከብ ተጫዋች ሆኜ ተሸለምኩ። ኮከብ ተጫዋች በመሆኔ ምክንያት እኔን በውሰት ለመውሰድ ያልጠየቀኝ ክለብ የለም። ሀዋሳ ፣ ባንኮች እና የመሳሰሉ ክለቦች ጠይቀውኝ በመጨረሻም አስታውሳለው ቴዎድሮስ በቀለ (ቦካንዴ) ከቅዱስ ጊዮርጊስ ለቆ ስለነበር የእርሱን ቦታ ለመተካት እኔ ታስቤ በውሰት ጠየቁኝ። ከወንድሜ ጋር ተመካክሬ ለአስር ጨዋታ በ1995 ግማሽ ላይ ጊዮርጊስን ተቀላቅዬ የፕሪምየር ሊግ ዋንጫን አንስቻለው።

“ኳስ የመንጠቅ፣ የማቀበል እና አብዶ (ሰው ቀንሶ የማለፍ) ክህሎቱን ያዳበርኩት ከልጅነቴ ጀምሮ ነው። ሠፈር ውስጥ ስንጫወት የሚገርምህ ህፃናትን ሰብስቤ በጨርቅ ኳስ ስንጫወት ቀሙኝ እያልኳቸው በጣም ነበር የምላፋው፤ እንዳይነጥቁኝ ለማድረግ። አንዱን ልጅ ሳልፍ ሌላም ነገር ሳደርግ ይህ ነገር በጭንቅላቴ ውስጥ ቀርቶ በዛ ይመስለኛል ማለት እችላለው ችሎታውን ያገኘሁት። ኳስ መንጠቅ ላይ የአልሸነፍ ባይነት እልህ የነበረኝ መሆኑና አንድ ተጫዋች (አማካይ) ኳስ የመንጠቅ፣ የማለፍ እና የማቀበል ሁለገብ ተጫዋች መሆን አለበት ብዬ ስለማስብ ሁሌም ሜዳ ውስጥ ነጥቄ፣ አልፌ እና አቀብዬ መጫወት ያስደስተኝ ነበር።

“ገመዳ የሚለውን ቅፅል ስም ያወጣልኝ ገነነ መኩርያ (ሊብሮ) ነው። በጊዜው አብዶ ስሰራ ይከታተለኛል መሰለኝ፤ ደግሞም ተጫዋች ሳልፍ አጋጣሚ ሆኖ ኳስ አልነጠቅም። ሌላው ጠቅልዬ የማልፋት አስተላለፍ አለችኝ። ያንን በማየት ይመስለኛል ገመዳ የሚል ስም ያወጣልኝ።

“በብሔራዊ ቡድን በ1986 ነፍሱን ይማረው እና ጋሽ ሥዩም አባተ ለወጣት ቡድን ለመጀመርያ ጊዜ እንድጫወት የጠራኝ እርሱ ነው። ከዚህ በኃላ በዋናው ቡድን ብዙውን ጊዜ የመመረጡን ዕድሉን አግኝቻለው። ሆኖም የቡድኑ አባል እሆናለው እንጂ የመሰለፉን እድል አላገኘሁም። በጣም የሚገርምህ ሜዳ ውስጥ ገብተህ በምታደርገው ጥሩ እንቅስቃሴ እንኳን አይተው ደግመው የማያስገቡበት ሁኔታ ነበር። ለምን ይህ እንደሆነ አላውቅም። ሌሎች ስለዚህ ጉዳይ ቢናገሩ ይሻላል። እኔ እንዲህ ነበርኩ ብሎ መናገሩን አልፈልግም። በወቅቱ የነበረውን ተመልካች ይፈርደዋል። ብቻ ብዙ የመሰለፍ የመጫወት ዕድሉን አላገኘውም።

“አማካይ ሆኜ ብዙ ጎል ለማስቆጠሬ ምክንያት ከአጥቂ ጀርባ ስለሆንኩ እና ትንፋሹ ስለነበረኝ ይመስለኛል ብዙ ጊዜ ከጎል አልጠፋም ነበር። በወቅቱም አብረውኝ የተጫወቱት አጥቂዎች አቀብለሀቸው መድገም የሚችሉ በመሆናቸው ጎል እንዳስቆጥር ምክንያት ሆነዋል። ኳስቆጠርኳቸው በርካታ ጎሎች የማረሳው ኢትዮጵያ መድን ካሸነፈ ከመውረድ የሚተርፍበትን ጨዋታ ከኪራይ ቤት ጋር አድርገን 2-1 ስናሸነፍ ወሳኛን ሁለተኛ ጎል ያስቆጠርኩበት እና ናሚቢያ ሄደን 2-1 ተሸንፈን የመልሱ ጨዋታ በአዲስ አበባ ስታዲየም ሰባት ለዜሮ ስናሸንፍ ሦስት ጎል አስቆጥሬ ሐት-ትሪክ የሰራሁበት አጋጣሚ መቼም የማረሳቸው ናቸው።

“አሁን ላይ ያለውን እግርኳሳችንን በአገኘሁት አጋጣሚ እከታተላለው። በተለይ ተጫዋቾች ጥሩ ተከፋይ በመሆናቸው በጣም ደስተኛ ነኝ። በእኛ ዘመን እድሉን አግኝተን ወደ ውጭ ወጥተን የተሻለ ኑሮ ኖርን እንጂ በሀገር ቤት በምን አይነት አስቸጋሪ ኑሮ እየኖሩ እንደሆነ ሁላችንም እናውቃለን። ስለዚህ የዚህ ዘመን ተጫዋቾች ራሳቸውን ከብዙ ነገር ቆጥበው ቤተሰቦቻቸውን በስነ ሥርዓት ማስተዳደር አለባቸው። በኃላ ወድቀው የሰው እጅ እንዳያዩ ከአሁኑ ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው።

“መድን እና መብራት ኃይል አሁን እዚህ ደረጃ ደርሰው እንዲህ ሆነው በማየቴ እውነት ነው የምልህ በጣም ነው የማዝነው። ምክንያቱም መድንም፣ ኤልፓም ለኔ ልዩ ቦታ አላቸው። ያው እግርኳስ ነውና ወደፊት ወደ ቀድሞ ክብራቸው ይመለሳሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለው።

“እስካሁን የአሰልጣኝነት ኮርስ አልወሰድኩም ። ያው ሀገር ቤት እያለው አሰልጣኝ የመሆን ፍላጎት አልነበረኝም። እዚህ ሀገር ከመጣው በኋላ ሌላ ሥራ ነው እየሰራው የምገኘው። እንደ ፈጣሪ ፍቃድ ኮርሶችን ወስጄ ሀገር ቤት መጥቼ የማሰልጠን ዕድል አገኛለሁ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።

“ከሀገሬ ከወጣው 12 ዓመት ሆኖኛል። የምኖረው ሲዊዘርላንድ ነው። በዚሁ ሀገረ ኢትዮ ስዊዝ ለሚባል ቡድን አሁንም ድረስ ከወንድሜ ሀብቶም ጋር በአንድ ማልያ እየተጫወትኩ ነው። በትዳር ህይወቴ ከቀድሞ ባለቤቴ የ20 ዓመት ወንድ ልጅ አባት ነኝ። ስሙ ናታን ተክሌ ይባላል። በመቐለ ዩኒቨርስቲ የመጀመርያ ዓመት ተማሪ ነው። በትምህርቱ በጣም ጎበዝ ተማሪ ነው። እንደኔ አይነት የእግርኳስ ፍቅር ብዙም የለውም።”

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ