እግርኳስን ከመጫወቻ ሜዳ ውጪ ሆኖ ከመደገፉ እና ስለኳስ ከመዘመሩ በፊት የሚደግፈውን ክለብ ማሊያ ለብሶ ተጫውቷል። ለሚደግፈው ክለቡ የአቅሙን ግልጋሎት በተጫዋችነት ከሰጠ በኋላ ደግሞ በሚወደው የሙዚቃ ሙያ ለክለቡ አዚሟል። ከ2008 ጀምሮ በአፄ ቴዎድሮስ እና በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም ዋነኛ አስጨፋሪ ሆኖ ከክለቡ ጎን በቋሚነት ቆሟል። ከ7 ወራት በፊት ደግሞ የክለቡ የደጋፊዎች ማኅበር ፕሬዝዳንት ሆኖ እያገለገለ ይገኛል። ክለቡ ባህር ዳር ከተማ ጨዋታ ሲያደርግ ውሃ ሰማያዊውን ማሊያ ለብሶ ብቻ የማይቀመጠው የዛሬው እንግዳችን እስባለው ልይህ ከእርሱ፣ ከደጋፊ ማኅበሩ እና ከክለቡ ባህር ዳር ከተማ ጋር የተያያዙ ጥያቄዎችን ሰንዝረንለት ጥሩ ቆይታ አድርገናል።
በባህር ዳር ከተማ ተወልደክ እንዳደክ አቃለሁ። መቼ እና በምን አጋጣሚ ነው የትውልድ ከተማህን መደገፍ ጀመርክ?
እንዳልከው ተወልጄ ያደኩት ባህር ዳር ነው። ከልጅነቴ ጀምሮም የክለቡን ጨዋታዎች ስመለከት ነበር። ወደ ክለቡ በደጋፊነት በደንብ መቅረብ ከመጀመሬ በፊት የክለቡ ተጫዋች ነበርኩ። ገና በአፍላ እድሜዬ በታዳጊ ፕሮጀክት ደረጃ ውሃ ሰማያዊውን ማለያ ለብሼ ተጫውቻለሁ። አሁን በወልቂጤ ከተማ እያሰለጠነ የሚገኘው ደጋረገ ይግዛው አሰልጥኖኛል። ብቻ ገና አስራዎቹን እድሜ እየጀርኩ ነው ወደ እግርኳሱ መቅረብ የመረጥኩት። ተጫዋችነቱም ሳይሳካልኝ ሲቀር ወደ ሌላ ሙያ ፊቴን አዞርኩ። ነገር ግን ሌላ ሙያ ውስጥ ብሆንም እግርኳስ በደሜ ውስጥ ነበር። ስታዲየም እየገባሁ ጨዋታዎችን እመለከት ነበር። የሚገርምህ የውጪ ጨዋታዎችን አላይም ነበር። አፄ ቴዎድሮስ ስታዲየም ጨዋታ ካለ ውሎዬን እዛ አደርጋለሁ። ከዛም እያደኩ ስመጣ በይበልጥ የባህር ዳር ፍቅር ተጠናውቶኝ የክለቡ ቀንደኛ ደጋፊ ሆንኩ። ከምንም በላይ ደግሞ ከተማችን ብዙ እግርኳስ ወዳድ ኖሮባት ለፕሪምየር ሊግ አለመብቃቷ ያሳስበኝ ነበር። ከ2006 በኋላ ደግሞ ዋርካውን ጨምሮ የከተማው ጀግና ልጆች ተሰባስበው ክለቡን ለፕሪሚየር ሊግ ለማብቃት ስራዎችን በተደራጀ ሁኔታ መስራት ጀመሩ። ከዛም የደጋፊ ማኅበር ተቋቁሞ ስራዎች መሰራት ቀጠሉ። ግን እኔ በግሌ በደንብ ወደ ስታዲየም በአስጨፋሪነት የገባሁት ከ2008 በኋላ ነው። እርግጥ ከዛም በፊት የሚሻ ሚሾ እና የሆያ ሆዬ ጭፈራዎችን ከሜዳ ውጪ እየጨፈርር ገንዘብ ለክለባችን ለማስገኘት እንጥር ነበር።
ተጫዋች እንደነበርክ በመሃል አጫውተከኛል። ለምን አልገፋህበትም?
ልክ ነው። በአስራዎቹ የእድሜ ክልል እያለሁ እግርኳስ ተጫዋች ነበርኩ። እንደገለፅኩልክም የታዳጊ ፕሮጀክት ውስጥ ነበርኩ። ከፕሮጀክት በተጨማሪ የክልል ሻምፕዮና እና የአማራ ክልል ምርጥ ቡድን ውስጥ ተመርጬ ተጫውቻለሁ። ከዚህ ውጪ የነገ ተስፋ በሚባል ቡድን ተስፋ ተጥሎብኝ ተካትቼ ነበር። ግን አልገፋሁበትም። የምጫወተው ግብ ጠባቂ ሆኜ ነበር። እንደምታቀኝ ደሞ ቁመቴ ብዙም ረጅም አደለም። ከዚህ መነሻነት ብዙም አልገፋሁበትም።
ለመጀመሪያ ጊዜ የባህር ዳርን ጨዋታ የተመለከትክበትን ጊዜ ታስታውሳለክ?
በጣም ልጅ ነበርኩ። ቀድሜ እንዳልኩት ስታዲየም ስለማልጠፋ ብዙ ጨዋታዎችን ገና ታዳጊ እያለሁ ተመልክቻለሁ። አሁን ላይ የመጀመሪያ የባህር ዳርን ጨዋታ የተመለከትኩበትን አጋጣሚ ባላስታውስም ጊዜው 16 ዓመታትን ያስቆጠረ ይመስለኛል። ግን ታዳጊ እያለሁ እነ ሁሴን ሰማን ሲጫወቱ አይቻለሁ። ያኔ ስታዲየም እንኳን መግባት ሳንችል ስንቀር ዛፍ ላይ እየተንጠለጠልን ጨዋታዎችን እናይ ነበር።
ቡድንህን በደገፍክባቸው እና ጨዋታዎችን ባየህባቸው በእነኚህ 16 ዓመታት ውስጥ የባህር ዳርን ማልያ የለበሰ ያንተ ምርጡ ተጫዋች ማነው?
በቦታ በቦታ ብመርጥ ደስ ይለኝ ነበር ግን አንድ ብቻ ምረጥ ካልከኝ ቴዲ ፋንታን እመርጣለሁ። ይህ የአጥቂ መስመር ተጫዋች ከፕሮጀክት ጀምሮ ብዙ ሰዎችን ሲያስደምም ነበር። እሱ ያለበት ጨዋታ ላይ እኔ እንደምናሸንፍ አቃለሁ። በጣም ድንቅ ተጫዋች ነበር።
ምርጡስ አሰልጣኝ ላንተ ማነው?
ልታቀያይመኝ ነው መሰለኝ (እየሳቀ)። ቡድናችንን ምርጥ ምርጥ አሰልጣኞች መርተውታል። አሁን ያለው ፋሲል ተካልኝን ጨምሮ። እንደ ተጫዋቹ አንድ ምረጥ ካልከኝ መኮንን እመርጣለሁ። ምክንያቱን በደንብ አላቅም ግን ብዙ ደጋፊዎች በእሱ ጊዜ ስለሆነ ወደ ክለቡ በደንብ የቀረብነው ለመኮንን ጥሩ ስሜት አለን።
አሁን ላይ ስላለ የስታዲየም የድጋፍ አሰጣጥ እሱባለው ምን ይላል?
ድጋፍ አሰጣጡ ደስ የሚል ነገር እንዳለው ሁሉ መጥፎ ነገሮችም በዛው ልክ እንዳሉት እየተመለከትን ነው። በተለይ ፖለቲካዊ ነገሮች እግርኳሱ ውስጥ ሲገቡ አደጋገፉ ፍፁም መስመሩን ስቶ ነበር። ሲሆን ሲሆን በፖለቲካ የተቃረኑ አካላትን እግርኳሱ ማቀራረብ እና ማስማማት ነው ያለበት። ግን እኛ ሃገር ለዚህ አልታደልንም። ከዚህ ውጪ አደጋገፉ ጋር ያለው ነገር ጥሩ ነው። ለአብዛኞቹ ክለቦች የኢትዮጵያ ቡና እና የቅዱስ ጊዮርጊስ ደጋፊዎች ተምሳሌት ናቸው። ብዙ ነገር ከእነርሱ ወስደናል። አሁን ላይ ባለ የድጋፍ አሰጣጥ ግን የባህር ዳር ደጋፊዎች ልዩ ነን። አንድም ቀን በሜዳችን ችግር ተፈጥሮ አያውቅም። በተጨማሪም ደግሞ ቡድናችንን ስናበረታታ በጣም ጀግኖች ነን። እንደኛ 90 ደቂቃ ቡድኑን የሚያበረታታ እና ስታዲየሙ ውስጥ የሚጨፍር ደጋፊ የለም። ይህ ደግሞ በሁሉም ክለቦች እንዲለመድ እሻለሁ። አንድ ቡድን ተሸነፈም፣ አሸነፈም፣ አቻ ወጣም ደጋፊው ከክለቡ ጎን መቆም ነው ያለበት። በቅርቡ ደግሞ በሊጉ ክለቦች የደጋፊዎች ማኅበር ተቋቁሞ እየተሰራ ያለው ስራ በጣም ደስ ይላል።
ገና ወደ ማኅበሩ ፕሬዝዳንትነት ከመጣህ ጥቂት ጊዜክ ነው። አዲሱ ስራ አስፈፃሚ ወደ ቦታው ከመጣ በኋላ ምን ምን ስራዎች ተሰርተዋል?
እኔ እና ጓደኞቼ ወደ ደጋፊ ማኅበሩ አመራርነት ከመጣን 8 ወር አልሞላንም። ግን በዚች አጭር ጊዜ ብዙ ስራዎችን ሰርተናል። ወደ ቦታው ገና ስንመጣ በአጭር፣ መካከለኝ እና ረጅም ጊዜ እቅድ ውስጥ ያሰብናቸው ተግባራት ነበሩ። በዚህም ብዙዎችን ስራዎች በጥሩ አፈፃፀም አገባደናል። እየሰራንም ያለናቸው አሉ። በቅድሚያ ለመስራት አስበን የተሳካለን ነገር ክለቡን በፋይናንስ የማጠናከር ስራ ነው። እኛ ወደ ቦታው የመጣን አካባቢ ባህር ዳርን ጨምሮ በርካታ ክለቦች በገንዘብ እጥረት ለተጫዋቾቻቸው ደሞዝ መክፈል ተስኗቸው ነበር። በዚህ መነሻነት ክለባችንን ከገባበት የገንዘብ ችግር ለማውጣት ቴሌቶን አዘጋጀን። ቴሌቶኑንም አዲስ አበባ በሚገኘው ኢንተርኮንቲኔንታል አዲስ ሆቴል አዘጋጀን። በቴሌቶኑም 45 ሚሊዮን ብር ቃል ተገባልን። ከዛም ቃል የተጋውን ገንዘብ እየሰበሰበን ለክለባችን ቶሎ ደረስንለት። የሰበሰብነውንም ገንዘብ ለየተጫዋቾቹ የ4 ወር ደሞዝ ከፈልንበት። ይህንንም ደግሞ በማድረጋችን ከኢትዮጵያ የመጀመሪያዎቹ የደጋፊ ማኅበሮች የሚያደርገን ይመስለኛል። ይህንን ግን አናቆምም። በደንብ ቀጣይነት ኖሮት ክለባችንን በፋይናንስ ለማጠናከር እንተጋለን። ኮቪድ-19 መጣ እንጂ ባህር ዳር ላይም ሌላ የሩጫ ዝግጅት ልናደርግ እየተዘጋጀን ነበር። በሁለተኛ ደረጃ እኛ ወደ ቦታው ከመጣን በኋላ በማህበራዊ ሃላፊነት በኩል ጥሩ ስራዎችን ሰርተናል። ለምሳሌ በኮሮና ጊዜ እንኳን ነብሳችንን ሰጥተን በከተማችን ብዙ ስራዎችን ስንሰራ ነበር። አቅመ ደካሞችን እና የጎዳና ተዳዳሪዎችንም ስንደግፍ ነበር። እነዚህን ወገኖቻችንን ምግብ ከማብላት ውጪ የአፍ እና አፍንጫ መሸፈኛዎችን በቅናሽ ስንለግስ ቆይተናል። በተጨማሪም እምቦጭ ላይ ደጋፊዎቻችንን አስተባብረን ትልቅ ስራ ሰርተናል። በተለይ ከፋሲል ከነማ ደጋፊዎች ጋር በመተባበር ጣናን ለመተሰደግ ለፍተናል። እርግጥ እምቦጭን እኛ ብቻችንን እንደማናጠፋው እናቃለን ግን ከፌደራል መንግስት ጋር ተባብረን ትኩረት እንዲሰጠው ትልቅ አስተዋጽኦ አበርክተናል። ከምንም በላይ ደግሞ በዚች አጭር ጊዜ የክለቡን መብት ስናስጠብቅ ነበር። ይህ ማለት ከጥቅማጥቅም እና ማሊያ ጋር በተያያዘ ማለት ነው። በተለይ ከክለቡ እውቅና ውጪ የተለያዩ ማሊያዎች እኛ ከመምጣታችን በፊት ይሸጡ ነበር። እኛ ከመጣን በኋላ ግን በየፋብሪካው እየዞርን ህገወጥ ማሊያዎችን እንዳይመረቱ እና ክለቡ እንዳይጎዳ አድርገናል።
ማኅበሩ ራሱን ወደፊት ለማሻሻልስ ምን አይነት ስራዎች ለመስራት አልሟል?
እንደ እቅድ የያዝናቸው በጣም በርካታ ስራዎች አሉን። የመጀመሪያው እቅዳችንም ደቡብ አፍሪካ እና አሜሪካ የባህር ዳርን የደጋፊዎች ማኅበር መስርተን ክለቡ ገቢ የሚያገኝበትን መንገድ መፍጠር ነው። እርግጥ ሁለቱም ቦታ ማኅበሩን ለማቋቋም ስራዎች ተጀምረዋል ግን በደንብ አፋጥነን ለቀጣይ ዓመት ማድረስ አለብን። በተለይ አሜሪካ ማኅበሩን ለመመስረት ጥሩ መንገድ ተጉዘናል። ግን እንዳልኩት በደንብ ማፋጠን አለብን። ከዚህ ውጪ ክለባችንን በፋይናንስ ለመደገፍ የምንችልበትን መንገድ ለመቀየስ እቅድ አውጥተናል። በተጨማሪም ከእኛ በፊት የነበሩት የደጋፊ ማኅበር አመራሮች ያቋቋሙት ጥሩ የስታዲየም አስተባባሪ(ስቴዋርድ) ሃይል አለ። ይህንን ሃይልም በደንብ ለማጠናከር እናልማለን። ከምንም በላይ ደግሞ ስራ የሌላቸውን የክለባች ቀንደኛ ደጋፊዎች ስራ ለማስገባት እንጥራለን። እነዚህ ደጋፊዎች መተዳደሪያ መደበኛ ስራ የላቸውም። ግን ክለባቸውን ከሃገር ሃገር እየዞሩ ይደግፋሉ። ስለዚህ እኛም ለነዚህ እንቁ ደጋፊዎች መድረስ አለበን። በዚህም 40 የሚሆኑ ደጋፊዎችን አጣርተን በዶክመንት ይዘናል። ስለዚህ በቀጣይ ለነዚህ ደጋፊዎች ስራ ፈጥረን የምናግዛቸው ይሆናል።
ደጋፊ ማኅበሩ ሁለት መቀመጫዎች የክለቡ ቦርድ ውስጥ እንዳለው አቃለሁ። ከክለቡ ጋር ያላችሁ መደበኛ ግንኙነት ምን ይመስላል?
ክለቦች ህዝባዊ መሰረት ቢኖራቸው መልካም ነው። ለዚህም ደግሞ ጠንክረን እንሰራለን። ከቦርዱ ጋር ጥሩ ግንኙነት አለን። የደጋፊ ማኅበሩ ሰብሳቢ እና ምክትል ሰብሳቢ ቦርዱ ውስጥ መቀመጫ አለን። በዚህም ሁል ጊዜ መከባበር ላይ የተመሰረተ ጠቃሚ ንግግሮችን በየስብሰባዎቻችን እናደርጋለን። ሁሌም ተስማምተን ነው የምንሰራው። የቦርዱንም ሚስጥር አናወጣም። እንደ ታላቅ እና ታናሽ ወንድም ነው ተከባብረን ስራዎችን የምንሰራው። በሚያዙን እና በሚፈልጉን ሰዓት ሁሌም ከጎናቸው ነን። በአጠቃላይ ከክለቡ ጋር በጣም መልካም ግንኙነት ነው ያለን።
በደጋፊዎች በኩል የሚነሳውን የማሊያ ጉዳይ በተመለከተ የምትነግረን ነገር ይኖር ይሆን? በደጋፊዎች ዘንድ የጥራት እና የብዛት ጥያቄ በተደጋጋሚ ስለሚነሳ…
ማሊያ ክለቡ ነው የሚያስመጣ። የቀጣይ ማሊያም ከታዘዘ በኋላ ነው እኛ የደረስነው። ግን እንደ አጋጣሚ ሆኖ የታዘዘውን ማሊያ አይተናል። እጅግ በጣም ውብ ማሊያ ነው የታዘዘው። በማሊያ ረገድ እኛ የደጋፊውን ስሜት እና ጥያቄ ለቦርዱ ነው የምናቀርበው። ግን ማሊያው ቶሎ እንዲመጣ እና ጥሩ ጥራት ኖሮት እንዲመረት ቦርዱን እንገፋለን። ከመጣም በኋላ ክለቡ ሽጡልኝ ካለ እንሸጣለን። አይ እራሴ እሸጣለውም ካለ ችግር የለም እኛ እናስተባብራለን። አንድ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ግን 30 ሺ ማሊያ ክለባችን ይረከባክ። በደጋፊ ማኅበሩ ጫና ስታዲየም ዙሪያ ክለባችን ቢሮ አግኝቷል። ምናልባት ነገሮች ጥሩ የሚሆኑ ከሆነ ሽያጩን እዛ እናደርጋለን።
የሙዚቃ ባለሙያ ነህ መሰለኝ?
የሙሉ ሰዓት ስራዬ ሙዚቀኛነት አደለም። አስጎብኚ ነኝ። ግን ለሙዚቃ ጥሩ ስሜት አለኝ። ግጥም እና ዜማ እሞክራለሁ። የውስጤን ስሜት በሙዚቃ ማስተላለፍ ስለሚያስደስተኝ እና ስለሚቀለኝ ነው ሙዚቃን በትርፍ ጊዜዬ የምሰራው።
በዚህ ሙያህ ለክለብክ ምን አበርክተካል ታዲያ? ወደፊትስ?
ገና የጤና ቡድን እያለሁ የእግርኳስ መዝሙሮችን እሰራ ነበር። ወደ ባህር ዳር አስጨፋሪነትም ከመጣሁ በኋላ አንድ መዝሙር መጀመሪያ ላይ ሰርቻለሁ። መዝሙሩን የሰራነው ከእሱባለው ይታየው ጋር በመሆን ነው። እሱባለው ልክ እንደ ወንድሜ ነው። እኔ ግጥሞችን ፅፌ ላኩለት እሱ ደግሞ ለመዝሙር አድርጎ አስተካክሎ ላከልኝ። ዜማም ላይ አገዘኝ። ከዛ እራሴ ፕሮዲውስ አድርጌ መዝሙሩን ለቀቅነው። በዚህም ደጋፊዎች በጣም ተደሰቱ። ከዛም በኋላ 4 መዝሙሮችን ሰርቻለሁ። ግን እስካሁን አላወጣናቸውም። በቅርቡ ደግሞ የባህር ዳር ደጋፊዎች በዋናነት ከሚዘምሩት አራት ተወዳጅ መዝሙሮች ውስጥ ሁለቱ የእኔ ናቸው። እነሱም “እኛ ባላገሮች” እና “የሜዳው ጀግና ነው ንጉሱ” የሚሉት ናቸው። እኔ የሰራሁትን መዝሙር ደግሞ ደጋፊዎች ሲዘምሩት በጣም እደሰታለሁ። እኮራለሁም። በመዝሙር ብቻ ሳይሆን ግን ከበሮዎች እና የተለያዩ መሳሪያዎችን ለደጋፊዎች በማበርከት ከክለቡ ጎን ነበርኩኝ። ወደፊትም በዚህ እቀጥላለሁ። የደጋፊዎች አልበምም እየሰራሁ ነው።
በመጨረሻ?
ደጋፊውን ወደ ክለቡ ለማቅረብ በደንብ እየሰራን ነው። በየመንግስት እና የግል መስሪያ ቤቶች እየሄድን ደጋፊዎችን አባል እያደረግን ነው። አባልም ስናደርገ በተለያዩ ደረጃዎች ከፋፍለናቸዋል። የፕላቲኒየም፣ የወርቅ ምናምን እያልን ደጋፊዎች በአቅማቸው የማኅበሩ አባል እንዲሆኑ እያደረግን ነው። ከዚህ ውጪ አሁን ክለቡ እየተጓዘበት ያለው መንገድ እጅግ መልካም ነው። አሁን ላይ ያለውን የተጫዋቾች የዝውውር ሂደት ብቻ እንኳን ብትመለከት ያለው ነገር ደስ ይላል። በተጨማሪም በክለቡ ስር ከ140 በላይ ሰራተኞች አሉ። ይህ በጣም ትልቅ ቁጥር ነው። ሁሉም ሰራተኞች ሃላፊነታቸውን በደንብ ነው የሚወጡት። ይህንን ደግሞ ሌሎች ክለቦችም ቢከተሉ መልካም ነው። በአጠቃላይ የባህር ዳር ደጋፊዎች በአሁኑ ሰዓት በሊጉ ላይ ከሚገኙ የክለብ ደጋፊዎች ምርጦቹ ናቸው። ይህንንም ደጋፊ በማየቴ ደግሞ በጣም እድለኛ እና ደስተኛ ነኝ። ሁሉንም ደጋፊዎች እንደማከብራቸው እና እንደምወዳቸው በመናገር ሃሳቤን ላገባድ።
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!
© ሶከር ኢትዮጵያ