Soccer Ethiopia

መንግሥቱ ወርቁ ሲታወሱ (፭) | የጫማው ታሪክ በሁለተኛው የአፍሪካ ዋንጫ

Share

በህይወት የሌሉ የእግርኳስ ሰዎችን በምናስታውስበት አምዳችን የቀድሞው እና በበርካቶች ዘንድ የምን ጊዜውም ታላቅ እግርኳስ ተጫዋች እንደሆኑ የሚነገርላቸው መንግሥቱ ወርቁን እያሰብን እንገኛለን። የታላቁን የእግርኳስ ሰው ዕድገት ፣ የእግር ኳስ አጀማመር ፣ የቅዱስ ጊዮርጊስን ቆይታ እና በክለብ ጨዋታዎች የተፈጠሩ የሜዳ ላይ ገጠመኞችን አንስተናል። ዛሬ ደግሞ የመንግሥቱ ወርቁን የብሔራዊ ቡድን አመራረጥ ፣ የመጀመሪያ ውድድር እና በውድድሩ ስለተፈጠረው አጋጣሚ እናነሳለን።

ማስታወሻ ፡ በገነነ ሊብሮ በመፅሀፍ መልክ የተዘጋጀው ከመንግሥቱ ወርቁ ጋር የተደረገው ቃለ ምልልስ እና ልሣነ-ጊዮርጊስ ጋዜጣ የታላቁን ሰው ህልፈት ተከትሎ በተከታታይ ያወጣቸው ፅሀፎች ዋነኛ ግብዓት እንደሆኑ እንገልፃለን።

የካቲት 09 1949 ኢትዮጵያ በመጀመሪያው የአፍሪካ ዋንጫ ተሳትፎዋ የአህጉሪቱን ታላቅ ውድድር ጅማሮ በግማሽ ፍፃሜው ደቡብ አፍሪካን በፎርፌ አልፋ ከግብፅ ጋር ለዋንጫው የተጫወተችበት ዕለት ነበር። በጨዋታውም የግብፁ መሀመድ ዲያብ አራት ግቦችን አስቆጥሮ ኢትዮጵያም 4-0 ተሸንፋ በሁለተኝነት ውድድሯን አጠናቀቀች። ይህ ሲሆን ታላቁ ስምንት ቁጥር ፣ የወደፊቱ የሀገሩ ብሔራዊ ቡድን ታላቅ አጥቂ ገና ትምህርት ቤት ሆኖ በእረፍት ጊዜው በጉለሌው አባሲዮን ሜዳ ላይ ብቻ ነበር የኳስ ፍቅሩን የሚወጣው። ሆኖም መንግሥቱ ወደ እግር ኳሱ ብቅ ያለው ግን የዛን ዓመት መጨረሻ ክረምት ላይ ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ አንገቱን አስገብቶ ከቡድኑ ጋር ወደ ድሬዳዋ እና ናዝሬት በመጓዝ ባደረጋቸው ጨዋታዎች ነበር። በወቅቱ ድሬዳዋ ላይ የመጀመሪያ ጨዋታውን ከኮተን ጋር ካደረገ በኋላ ናዝሬት እንደ ፖሊስ ፣ ጦር ሠራዊት ፣ ኦሎምፒያኮስ ፣ ጄቬንቱስ ፣ ዳኛው እና ሌሎች ቡድኖችም በነበሩበት አዲሱ ታዳጊ መንግሥቱ ወርቁ ለቅዱስ ጊዮርጊስ ግቦችን እያስቆጠረ በቶሎ መታወቅ ችሎ ነበር።

በእነዚህ ጨዋታዎች መስተጋባት የጀመረው የመንግሥቱ ዝና አዲስ አበባ ደርሶ ስለጉብዝናው ይወራ ነበር። በዚሁ ጊዜ በቀጣዩ ዓመት 1951 ላይ በሁለተኛው የአፍሪካ ዋንጫ ላይ ለሚካፈለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ምርጫ ይካሄድ ነበር። ሆኖም በወቅቱ በምርጫው መካተት የሚችሉ ተጨዋቾች ከአንድ ዓመት በፊት (በ1949 መሆኑ ነው) በአዲስ አበባ ስታድየም በነጥብ ጨዋታ ላይ የተሳተፉ ብቻ ነበሩ። ይህ መስፈርት ገና በኳሱ ጅማሮ ላይ ያለው መንግስቱ ሊያሟላው የማይችለው ነበር። ሆኖም የናዝሬቱን ገድሉን ሜዳ ውስጥ ሆነው በተመለከቱት በእነ ጋሽ ይድነቃቸው ተሰማ ሙግት በአንደኛው የአፍሪካ ዋንጫ የተሳተፉ ተጫዋቾች በብዛት ባልተመረጡበት እና ቡድኑ በአመዛኙ በአዲስ ትውልድ በሚዋቀርበት ወቅት ላይ መንግሥቱ በምርጫው ውስጥ ሊካተት ቻለ። የብሔራዊ ቡድኑን መለያ መልበስ ግን እንዲህ ቀላል አልነበረም። ከአዲስ አበባ 25 እንዲሁም ከአስመራ 25 ተጫዋቾች ተመርጠው አስመራ ላይ በሚደረገው ከፍተኛ ፍትጊያ ባለበት የዝግጅት ጊዜ ቁጥራቸው ወደ 22 ዝቅ ማለት ነበረበት። ይህ ከባድ የዝግጅት ጊዜ የሁለት ወራት ርዝማኔ ነበረው። በርካታ ግጥሚያዎች ተደርገውም የመጨረሻዎቹ ተጫዋቾች ሲታወቁ መንግሥቱ አንዱ መሆን ቻለ። በዚህም ገና በተማሪነቱ እና ለክለቡ ብዙ ጨዋታዎችን ሳያደርግ በፊት ለብሔራዊ ቡድን ተመርጦ ከሀገር ውጪ በአህጉራዊ ውድድር ላይ የመጫወት ዕድልን ማግኘት ችሏል።

በዚህ ረጅም የዝግጅት ጊዜ አልፎ ከጨዋታው ጥቂት ቀናት ብቻ ቀደም ብሎ ግብፅ የገባው ብሔራዊ ቡድኑ ግን አንድ ችግር ገጥሞት ነበር። በብዙ ትግል በመጨረሻው ምርጫ ውስጥ ለመካተት በአሻዋማው የራስ አሉላ ሜዳ ላይ የተደረገው እልህ አስጨራሽ ዝግጅት የተጫዋቾቹን ጫማ ጨርሶት ነበር። በመሆኑም ግብፅ እንደገቡ ከመጀመሪያው ጨዋታ አስቀድሞ ጫማቸውን ማሳደስ የግድ ሆነባቸው። ጫማቸውን በጆንያ ሞልተውም ካይሮ ውስጥ ላለ ጫማ ጠጋኝ ይሰጡታል። ጫማዎቹም ተሰሩና ለመጀመሪያው ጨዋታ ደረሱ። ጣጣቸው ግን እንዴት የቡድኑ ውጤት ላይ ትልቅ ተፅዕኖ እንዳመጣ መንግሥቱ ወርቁ ለገነነ ሊብሮ እንዲህ ተርኮለት ነበር።

” ጫማው ተሰርቶ መጣ። ምንም ሳንሞክረው ወደ ሜዳ ይዘነው ሄድን። የተንኮላቸው ብዛት ከስር እንደጡት የሚያገለግለውን እንጨቱን በአንድ ሚስማር ነው ያያዙት። ወደ ሜዳ ለመግባት ስናሟሙቅ ጡቱ እየተነቀለ ከስር ባዶ ሆነ። ሜዳው ደግሞ እርጥበት ያለው ሳር ስለሆነ ያንሸራትታል። ዳኛው ደግሞ አጣድፎ ‘ቶሎ ግቡ’ አለ። ጫማው ከስር መቆንጠጫ የለውም ፤ ሌጣ ሆነ። ኳስ ለመምታት ስንሰነዝር ያኛው እግራችን እያዳለጠን መውደቅ ሆነ። ሮጠን መቆም ደግሞ አንችልም። ሁኔታችንን እያየ ህዝቡ ይስቅብናል። እንደዛም ሆኖ አራት አገቡብን ፤ በቃ ተናደድን። ስንወጣ ‘የተሸነፍነው በተንኮል ነው’ በማለት ለሕዝቡ ጫማው ጉጠት የሌለው መሆኑን የውስጥ እግራችንን ሁላችንም ስናሳያቸው ሕዝቡ አበደ። ‘ ባለጌዎች ! ‘ እያለ ሰደበን። አየህ ልንግባባ አልቻልንም። እኛ ያንን ያሳየናቸው እንደዚህ ጉድ አድርጋችሁን እንዴት ትስቃላችሁ ነው። እነሱ ደግሞ ‘የውስጥ እግር ማሳየት ነውር ነው’ ነው የሚሉት። ያኔ የኛ ስብስብ ደግሞ ጥሩ ስለነበር አያሸንፉንም ብለን እልህ ያዘን። ከዚያ ወቀሳ አቀረብን። እነሱም አባበሉን። የአፍሪካ ዋንጫ የቀረብነው ሦስት ነን። እኛ ከሱዳን ግብፅም ደግሞ ከሱዳን ይጫወታል። ሱዳን ከድሮም ግብፅን አይፈራም። ግብፆች ከበፊትም የሚፈሩት ሱዳንን ነው። እኛ ሱዳንን እንድናሸንፍላቸው ጫማችሁን ካልሰራንላችሁ ብለው ይለምኑን ነበር። እኛ ደግሞ ሁኔታው ስለሚገባን እምቢ አልናቸው። ሱዳን እኛ ላይ ብዙ ካገባ ግብፅ ዋንጫውን ለማግኘት ይቸገራል። ከዛያ እንደምንም አባብለው ጫማችንን አስርተው መጡ። የሚገርምህ በደንብ ነው ያሰሩት። ያንን ጫማ ሁለት ጨዋታ ተጫውተንበታል። ”

ይህ አጋጣሚ ከተፈጠረ በኋላ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በሱዳኑ ጨዋታ 1-0 ተሸነፈ። አካሄዱን ለውጦ በዙር በተካሄደው ውድድርም ግብፅ ሱዳንንም 2-1 በመርታት እንደመጀመሪያው ሁሉ ሁለተኛውንም የአፍሪካ ዋንጫ አነሳች። ሁለተኛ ተሳትፎዋን ያደረገችው ኢትዮጵያ እና ለመጀመሪያ ጊዜ ለሀገሩ የመጫወት ዕድሉን ያገኘው መንግሥቱ ወርቁም ውጤት እና ግብ ሳይቀናቸው ተመለሱ።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ

ሶከር ኢትዮጵያ

ሶከር ኢትዮጵያ በ ‘አብርሀም ገ/ማርያም የማስታወቂያ ድርጅት’ ስር የሚሰራ ድረገፅ ሲሆን በኢትዮጵያ እግርኳስ ላይ በሚያተኩሩ ዜናዎች፣ ቁጥራዊ መረጃዎች፣ ታሪኮች፣ ጥልቅ ዘገባዎች፣ አስተያየቶች እና ትንታኔዎች ላይ ትኩረቱን ያደርጋል።

ዘርፍ

ማኅደር

top