የቤተሰብ አምድ | ሽሮ ሜዳ ያበቀለችው ቤተሰብ

ከአንድ ቤተሰብ ወጥተው በእግርኳሱ ትልቅ ስም ያገኙ ተጫዋቾችን በምናነሳበት አምዳችን ከሽሮ ሜዳ ተነስተው ለስኬት የበቁትን የታፈሰ ተስፋዬ እና ወንድሞቹን ጉዞ እናስቃኛችኋለን።

ተወልደው ያደጉት አዲስ አበባ ሽሮ ሜዳ አካባቢ ነው፡፡ የቤተሰቡ ቁጥር በርከት ያለ ቢሆንም ሦስቱ የአንድ እናት እና አባት ልጆች በኢትዮጵያ እግር ኳስ ውስጥ ስማቸውን ያሰፈሩ ናቸው፡፡ እግርኳስ ወደ ቤተሰቡ የተዋወቀው በታምራት ተስፋዬ አማካኝነት ነው፡፡ ለታምራት እርሻ ሠብል የእግርኳስ ህይወቱን የጀመረበት ክለብ ሲሆን በመቀጠል ደግሞ ለአዲስ አበባ ፖሊስ ተጫውቶ አሳልፏል፡፡ ታምራት እግርኳስ ተጫዋችነትን የጀመረው በ1980ዎቹ መጨረሻ በትምህርት ቤቶች ውድድር ካሳየው ድንቅ አቋም መነሻነት እንደነበር ይነገራል፡፡

በመቀጠል ከቤተሰቡ ቀድሞ ከኳሱ ጋር ትውውቅ የነበረው ታምራት ለታናሽ ወንድሙ ታፈሰ ተስፋዬ መንገዶችን ከፈተለት። በኢትዮጵያ እግርኳስ ውስጥ ስኬትን ያጣጣመው ታፈሰም 1993 ላይ የአሁኑ ኢትዮ-ኤሌክትሪክ የያኔው መብራት ኃይልን ተቀላቅሎ የክለብ ህይወቱን ጀመረ። ይሁን እና በመጀመሪያዎቹ ዓመታት የያኔው ታዳጊ የመብራት ኃይል ቡድን የመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ በቀላሉ መግባት አልቻለም። “1992 ክረምት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከባንክ የወዳጅነት ጨዋታ ነበረው። ያኔ እኛ ፕሮጀክት የመክፈቻ ጨዋታ ያደርግ ነበር። ያን ጨዋታ ያዩና መብራት ኃይል ፣ ኢትዮጵያ ቡና እና ባንክ ወደ እነሱ እንድገባ ጠየቁኝ። እኔም መብራት ኃይል ብዙ ጊዜ ወጣቶች ላይ ስለሚያዘነብል እዛ ብገባ የተሻለ ነገርን አሳያለሁ ብዬ መረጥኩት። መብራት ኃይል ዋናው ቡድን ነበር የገባሁት። ሆኖም እነ ዮርዳኖስ አባይ ፣ ስምኦን አባይ እና መስፍን ታደለ በጣም ጎበዝ ጎበዝ ተጫዋቾች ስለነበሩ ልምድም ያግኝ ተብዬ ወደ ‘ቢ’ ተመለስኩኝ።” ሲል ወደ መብራት ኃይል ከገባ በኃላ የገጠመውን ሁኔታ ይናገራል፡፡

በ1993 በመብራት ኃይል ዋናው ቡድን ልምምዱን እየሰራ ውድድሮች ሲኖሩ ወደ ‘ቢ’ ቡድን በመሄድ ጨዋታዎችን ማድረግ የቀጠለው ታፈሰ በዋናው ቡድን ውስጥ የቋሚነት ዕድል ለማግኘት 1994ን መሻገር ግድ አለው። 1995 ላይ ግን ዮርዳኖስ አባይ ወደ ኢትዮጵያ ቡና መሄዱን ተከትሎ የያኔው ተስፈኛ አጥቂ በቡድኑ ውስጥ በቋሚነት የመሰለፊያው ጊዜ ደረሰ። በቶሎም ግቦችን የሚያስቆጥር ወሳኝ ተጨዋች መሆን ቻለ። ታፈሰ በወቅቱ ስለነበረው ዕድገት ይህን ይላል። “ዮርዳኖስ አባይ ወደ ኢትዮጵያ ቡና ከሄደ በኃላ የቋሚነትን ዕድል እያገኘው መጣሁ። 1996 ላይ የማስታውሰው ኮከብ ግብ አግቢነትን እየመራሁ እግሬ ላይ ስብራት አጋጠመኝ። ጉዳቴም የከፋ በመሆኑ ኢትዮጵያ ቡና 1997 ላይ ጠይቆኝ አንዳንድ ሰዎች ጋር መረጃው ስለነበር ‘ አልተሻለውም ያነክሳል’ በሚል ሳይሳካ ቀረ። 1998 ላይ ግን ወደ ቡና ሄድኩኝ።” ምንም እንኳን ኢትዮጵያ ቡናን ከ1998 እስከ 2002 ድረስ የሊጉን ዋንጫ ባያነሳም ታፈሰ በግሉ ከከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት እስከ ኮከብ ተጫዋችነት ደምቆ ታይቶበታል።

በዚህ ሂደት ታፈሰ ከታላቅ ወንድሙ የወረሰው ጥልቅ የእግር ኳስ ፍቅር ለታናሹ ተክሉ ተስፋዬም ተርፏል። በመሆኑም የታፈሰ ተስፋዬ ቤተሰብ ሦስት ተጫዋቾችን በማፍራት ሀት-ትሪክ መስራት ቻለ፡፡ ተክሉ የአማካይ ስፍራ ተጫዋች ነው ፤ የኢትዮጵያ ቡና የታዳጊ ቡድን ደግሞ መሠረቱ፡፡ በ1997 የኢትዮጵያ ቡናን ታዳጊ ቡድን ተቀላቅሎ መጫወት የጀመረው አማካዩ 2000 ላይ ወደ ዋናው ቡድን ካደገ በኃላ ከታላቅ ወንድሙ ታፈሰ ተስፋዬ ጋር የአንድ ክለብ መለያን በመልበስ ለመጫወት በቅተዋል፡፡ ታፈሰ ስለ ወንድሙ ተክሉ ሲናገር ” እኔ በኢትዮጵያ ቡና እስካለው ድረስ ጥሩ ጊዜን አሳልፈናል። ወደ የመን ከሄድኩኝ በኃላ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ 2003 ላይ ሲመጣ የመሰለፍ አጋጣሚውን አላገኝም። ከዛ በፊት ግን የመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ ይገባ ነበር። ከዚያ በኃላ ግን 2003 ቡና ቻምፒዮን ሲሆን ብዙም አልተጫወተም። ‘ጉዳት ነው’ እያለ አሰልጣኙ ያስቀምጠው ነበር። በመሀላቸው አለመግባባት ነበር። እኔ ከየመን ተመልሼ ቡና ስጫወትም እዛ ነበር ፤ 2006 ላይ ግን አብረን ወጣን። 2007 እና 2008 እሱ በንግድ ባንክ እየተጫወተ አሳለፈ” ይላል።

ከ1998 እስከ 2002 ድረስ ለተከታታይ አራት ዓመታት ያህል በኢትዮጵያ ቡና የቆየው ታፈሰ ተስፋዬ 2003 ላይ ወደ የመን ተጉዞ በየመን ሊግም አንድ ዓመት ካሳለፈ በኃላ 2004 ላይ በድጋሚ ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ቡናን አገልግሏል። ለኢትዮጵያ ቡና የተለየ ፍቅር እንደዳለው የሚናገረው ይህ አንጋፋ አጥቂ እሱ በሌለበት ዓመት ቡና የሊጉን ክብር ማግኘቱ የፈጠረበትን ስሜት እንዲህ ይገልፀዋል። “ኢትዮጵያ ቡና ጥሩ ጊዜ አሳልፊያለሁ። ሁሉም ነገር የእግዚአብሔር ስጦታ ነው። በዋንጫው ጊዜም ባለመኖሬ አልከፋም። የምወደው እና የማከብረው ክለቤ ስለሆነ እኔም ዋንጫውን ያገኘሁ ያህል ነው የምቆጥረው። የመንም ሆኜ እከታተል ነበር። እንደውላለሁ ፣ እከታተላለሁ ‘ከምን ደረሰ ? ውጤት እንዴት ነው ? ‘ ብዬ እጠይቃለሁ። ክለቡን የምትወደው ከሆነ መራቅም የለብህም ፤ ተክሉ ስለነበርም አይደለም። ‘ያንን ደጋፊ አንድ ቀን እንኳን ዋንጫ በልቶ ባየው ደስ ይለኛል’ ብዬ አስብ ነበር። እነሱም ለእኔ ጥሩ ናቸው። እኔም ያለኝን አቅም ነው የምከፍለው እና የማደርገው የነበረው። በክለቡ በቆየሁባቸው ወቅቶች ጥሩ ጊዜ አሳልፌ ነው የለቀኩት።”

ታፈሰ ተስፋዬ የመን ከመሄዱም በፊትም ሆነ ከመጣ በኃላ በድምሩ ለሰባት ዓመታት ያህል አስደናቂ አቋሙን አሳይቷል፡፡ 2007 ላይ ወደ ወደ ሀዋሳ ከተማ አምርቶ በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ ስር ለሁለት የውድድር ዓመታት ጥሩ ግልጋሎትን ከሰጠ በኃላ በ2009 ወደ አዳማ በመሄድ እስከ 2011 ግማሽ ዓመትን ድረስ ያልተቋረጠው የግብ አስቆጣሪነቱን ገፍቶበታል። በመቀጠል በውድድሩ አጋማሽ ወደ አሳዳጊ ክለቡ ኢትዮ-ኤሌክትሪክ ተመልሶ በመጫወት ላይ ይገኛል፡፡ ተክሉ ታፈሰ በበኩሉ ከወንድሙ ታፈሰ ጋር ቡናን ከለቀቀ በኃላ ወደ ንግድ ባንክ በመሄድ ሁለት ዓመታትን አሳልፏል፡፡ ቀጥሎ ደግሞ በዳሽን ቢራ ሲጫወት ከቆየ በኃላ የቡድኑን መውረድ ተከትሎ ከ2010 እስከ 2011 ድረስ በኤሌክትሪክ ቆይቶ ዘንድሮ በከፍተኛ ሊጉ ለአዲስ አበባ ከተማ እየተጫወተ አሳልፏል።

ይህ ቤተሰብ ሦስት ወንድማማቾችን ያፍራ እንጂ የቤተሰቡ አንድ አካል እንደሆነ የሚነገርለት አንጋፋው አጥቂ በረከት አዲሱም በዚህ ቤተሰብ ውስጥ የልጅነት ጊዜውን አሳልፏል፡፡ ምንም እንኳን የስጋ ዝምድና ባይኖራቸውም በ1990ዎቹ አጋማሽ በረከት የባንክ ‘ቢ’ ቡድን ተጫዋች እያለ ለሰባት ዓመታት በነታፈሰ ቤት አድጓል። ከባንክ ወጥቶ ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ እስካመራበት ጊዜ ድረስም እዚሁ ቤተስብ ውስጥ ኖሯል። በረከት አዲሱ በቅዱስ ጊዮርጊስ ፣ አዳማ ከተማ እና ሲዳማ ቡና በፕሪምየር ሊጉ በመጫወት ያሳለፈ ሲሆን በአሁኑ ወቅትም በከፍተኛ ሊጉ ሀምበሪቾ እየተጫወተ ይገኛል፡፡

ታላቅ ወንድማቸው ታምራት እግርኳስን ካቆመ ረጅም ዓመታትን ቢያስቆጥርም የሱን ፈለግ የተከተሉት ሁለቱ ወንድሞቹ ታፈሰ እና ተክሉ ግን አሁንም በመጫወት ላይ ይገኛሉ፡፡ ታፈሰ ተስፋዬ እግርኳስ ተጫዋች እንድንሆን ወንድማችን ታምራት መሠረት ቢሆንም እየመከረ እየገሰፀን ለዚህ ያደረሰን ግን ትልቁ ወንድማችን ነው ይላል። “የታላቄ ታምራት ታላቅ ቦዲ ቢውልደር ነው ፤ ተሾመ ተስፋዬ ወይንም ፎጎ ይባላል። እሱ የሁላችንም መሠረት ነው። እዚህ ደረጃ እንድንደርስ ብዙ አስተዋጽኦ አድርጎልናል። በረከት ጊዮርጊስ እያለ ሲጎዳ በቶሎ አገግሞ ወደ ሜዳ እንዲመለስ እና አዳማ እንዲገባ ትልቁን አስተዋጽኦ ያደረገለት ተሾመ ነው። አሁን ካፒታል ሆቴል የአካል ብቃት አሰሪ ነው። ቢያንስ ለሃያ ዓመታት የኢትዮጵያ ቻምፒዮንም ነው። በባህሪም በስፖርቱም አንፆ በማሳደግ ትልቁን አስተዋጽኦ ያደረገልን እሱ ነው። እናት እና አባት ቢኖሩንም እንደነሱ ሆኖ እየመከረን ባለው ነገር እያሳየገ እዚህ ያደረሰን እርሱ ነው። ስታድየም ገብቶ እኛ ስንጫወት ስህተት ሲያይ ይነግረናል። እኔ አሁን ከጊዮርጊስ ደጋፊ ጋር ስነቋቆር ይቆጣኛል። ‘ተው እንደዚህ አትሁን ፤ ነገ የሚፈጠረው አይታወቅም’ እያለ ይመክረኝ ነበር።”

የእኛ ቤተሰብ በስራ የሚያምን ነው፡፡ እናታችን ከልጅነታችን ጀምራ የምትሰራ ናት። ቤተሰባችን ከልጅነታችን ጀምሮ በንግዱ ዓለምም የሚታወቅ ነው። ሌላው ተክለ ሰውነታችንም ከዘርም ያለ ነገር ነው፡፡ ታላላቆቼን ብታይ በተክለ ሰውነት ከእኔ የተሻሉ ናቸው፡፡ እንደ ቤተሰብ በስፖርቱ የምናምን እና በስፖርቱ ውስጥ የኖርን ነን። ” የሚለው ታፈሰ ተስፋዬ በመጨረሻም ሠፈሩ ሽሮሜዳ ተጫዋቾችን ለማፍራት ምቹ ስለመሆኗ ይህንን ብሏል። “አካባቢያችን ለኳስ የተሰጠ ነው። እንደ ናይጄሪያ ዓይነት መልክ አለው። ከጉቶ ሜዳ ጀምሮ እነ በላያ የሚባሉ ታዋቂ ተጫዋቾች ወጥተውበታል። ለልምምድም የሚመች ነው፡፡ እንጦጦ ጋራው ላይ ያለ ስለሆነ ብዙ ወጣቶች ቢሰሩበት በጣም መውጣት የሚችሉ ልጆች ይኖራሉ፡፡ ግን አንዳንድ ትውልዱ ላይ ምታየው ነገር አለ። ስትመክረው አይቀበልህም ፤ አስቸጋሪ ነው። ብዙ ተጫዋቾችን ማውጣት ትችላለህ ግን ብዙ ፈተና ይጠይቃል። ተክለ ሰውነታቸውም ጥሩ ነው። አሁን ወጣቶችን ስታይ ግን በትንሽ ነገር ይሸወዳሉ። ከተሰራ ብዙ ልጆችን ማፍራት ይቻላል። ከእኛ በኋላ ለምሳሌ እንደ አማኑኤል ዮሀንስ እና ስንታየው ዋልጬ ወጥተዋል። በመብራት ኃይል ሌሎችም ተስፋ የሚጣልባቸው ብዙ አሉ። በእርግጥ ሠፈሩ ትንሽ ይሸውዳል። ለምሳሌ ተሽመ ኦሼ መጥቶ ጠፍቷል። አሁን ከተሰራ ግን ብዙዎች ይቀየራሉ።”

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ