በሀገራችን የግብጠባቂዎች ታሪክ አንቱታ ካተረፉ ድንቅ ግብጠባቂዎች መካከል የሚመደበው እና በጥረቱ፣ በልፋቱ እና በጥንካሬው ስኬታማ መሆን የቻለው የዘጠናዎቹ ምርጥ ግብጠባቂ ደያስ አዱኛ ማነው ?
ደያስ አዱኛ በልጅነት እድሜው የሚሠራውን የመካኒክነት ሥራ አቋርጦ ከነ ሥራ ልብሱ (ቱታው) አንድ የሚወደውን፣ የሚያደቀውን ግብጠባቂ ለመመልከት እና ከጎል ጀርባ አልፈው የተመቱ ኳሶችን ተወርውሮ ለመያዝ የሚጥር በጅማ ከተማ ኩሎበር አካበባቢ ተወለደ። አባቱ አቶ አዱኛ ጉርሙ የታወቀ ትልቅ የመኪና ገራዥ በጅማ ከተማ ነበራቸው። ልጃቸው እርሳቸው በያዙት የመኪና መካኒክነት ሙያ ከስር እስራቸው እየተማረ ጥሩ መካኒክ እንዲሆን ይፈልጉ ነበር። የልጃቸው ልብ ግን የሸፈተው መካኒክነት ሳይሆን ከብዙ በጥቂቱ ለውሃ ሥራ፣ ጅማ ከተማ፣ መከላከያ፣ አውስኮድ፣ ባህር ዳር ከተማ የተጫወተው ግብጠባቂ ጥላሁን ዘለቀን መሆን ነበር። እርሱን አርዓያ አድርጎ ሌላኛው ጥላሁን ለመሆን ይመኝ የነበረው ይህ ታዳጊ ህልሙን ዕውን ለማድረግ የመጀመርያ ክለቡ ለሆነው በጅማ ለሚገኘው በአሰልጣኝ መታሰቢያ ለሚሠለጥን ውሃ ልማት ለሚባል ክለብ መጫወት ጀመረ።
በመቀጠል ለጅማ ምርጥ፣ ለኦሮሚያ ምርጥ እና ለዝዋይ ኢትኮ ከተጫወተ በኃላ በቀድሞ አሰልጣኙ መታሰቢያ ጥቆማ አማካኝነት ጋሽ ሀጎስ ደስታ ለሙከራ መብራት ኃይል ወሰዱት፣ ሙከራውን በተሳካ ሁኔታ አጠናቆ የመብራት ኃይል ግብጠባቂ ቢሆንም በወቅቱ የነበሩት ስመጥር የሆኑ ግብጠባቂዎች ፀጋዘአብ አስገዶም እና በለጠ ወዳጆን አስቀምጦ መጫወት ከባድ የነበረ በመሆኑ በተጠባባቂ ወንበር አብዛኛውን ጊዜ ከሚያሳልፍ ራሱን ወደሚያሳይበት ሙገር ስሚንቶ በ1990 አምርቶ ለሁለት ዓመት ተጫውቷል።
ደያስ በልጅነቱ እያየው፣ እያደነቀው እና አርዓያ የሚያደርገው የቀድሞ ግብጠባቂ ጥላሁን ዘለቀ ስለደያስ ይሄን ይናገራል ” ምንም ብዬ ልንገርህ ቃል የሚገልፀው አይደለም። በጣም ከፍተኛ አቅም የነበረው። ግብጠባቂ ለመሆን ከልጅነቱ ጀምሮ የነበረውን ከፍተኛ ፍላጎት ለማሳካት ጠንክሮ ልምምዱን የሚሰራ፣ በጣም ታራሪ፣ ሰርቶ የማይደክም፣ ደፋር እና ለመለወጥ የሚለፋ ሰው ነው። ያ ከህፃንነቱ ጀምሮ የማቀው ልጅ አድጎ ጠንክሮ በትልቅ ደረጃ ሲጫወት ሳየው የተሰማኝ ደስታ ምን ብዬ ልግለፅልህ በጣም ነው ደስ ያለኝ።” ብሏል።
በሙገር ባሳለፈው ጥሩ ጊዜ ዳግመኛ ወደ ክለባቸው እንዲመጣ የፈለጉት መብራት ኃይሎች የደያስ አዱኛን የሦስት ዓመት አገልግሎት አግኝተዋል። ለሙያው ያለው ክብር፣ ራሱን ለማብቃት የነበረው ጥረት ከፍተኛ እንደሆነ የሚነገርለት ደያስ ከመብራት ኃይል ጋር በነበረው ቆይታ የ1993ቱ የሦስትዮሽ ዋንጫ ባለ ክብር እንደነበረ ይታወቃል።
በ1996 በ30 ሺህ ብር የፊርማ ብር ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስን አምርቶ የእጅ ጓንቱን እስከሰቀለበት ጊዜ ድረስ ለተከታታይ አምስት ዓመታት አገልግሏል። በፈረሰኞቹ ቤት በነበረው ቆይታ ሦስት የፕሪምየር ሊግ ዋንጫንም አንስቷል። በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በተጫወተባቸው ዓመታት በተለይ በአርጀንቲና የዓለም ወጣቶች ዋንጫ ላይ በሦስቱም ጨዋታ ላይ አሰልጣኝ ዲዬጎ ጋርዝያቶ የተጠቀሙት ደያስ አዱኛ ነው። በ1994 የሴካፋ ዋንጫ ላይ ለብሔራዊ ቡድን ተጠርቶ በመጨረሻ መቀነሱ ቢቆጨውም የ1997 የሴካፋ ዋንጫን ባነሳው ቡድኑን ውስጥ በግብጠባቂነት በማገልገል ስኬታማ መሆን ችሏል።
ለኢትዮጵያ ታዳጊ ቡድን ከአስራ ሰባት ዓመቱ ጀምሮ በመምረጥ እና በማሰልጠን ለደያስ አዱኛ እድገት መነሻ የሆኑት ጋሽ ሰውነት ቢሻው ስለ ደያስ ሲናገሩ ” ደያስ በጣም ጠንካራ ፣ አንድ ለአንድ ጎል የማታስቆጥርበት ብዙ ግብጠባቂዎች መሬት ለመውደቅ የሚፈሩ ሆነው እርሱ ጋር ምንም መፍራት የሌለበት። ሁሉን ነገር ሜዳ ውስጥ የሚሰጥልህ እጅግ ደፋር ግብጠባቂ ነበር”። ብለዋል።
ብዙ መጫወት እየቻለ በጊዜ ራሱን ከግብጠባቂነት ማግለሉ አስገራሚ ውሳኔ እንደሆነ በወቅቱ የስፖርት ቤተሰቡ መነጋገርያ ሆኖ ነበር። ከሀገሩ ከወጣ 11 ዓመት የሆነው ደያስ ኑሮውን በአሜሪካ በማድረግ በውጪ ሊጎች ለመጫወት በተለያዩ ክለቦች ሙከራዎችን ቢያደርግም ሳይሳካለት ቀርቷል። የረጅም ዓመት የፍቅር አጋሩ ሆና ከቆየች የአሁኑ ሚስቱ እፀገነት ተሰማ አንድ የ10 ዓመት ሴት ልጅ ያፈራው ባለ መልካም ስብዕናው የቀድሞ የዘጠናዎቹ ድንቅ ግብጠባቂ ደያስ አዱኛ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ይሄን ቆይታ አድርጓል።
“በመጀመርያ አክብራቹ ስለጋበዛችሁኝ በጣም አመሰግናለው። በግብጠባቂ ለመሆን ከፍተኛ ፍላጎትን ከልጅነቴ ጀምሮ ነበረኝ ጥረት እና ድካም እዛ የማስበው በሀገሪቷ ትልልቅ ክለቦች በመጫወት በዋንጫ የታጀበ ቆይታ ማድረጌ ለኔ ትልቅ ስኬት ነው። በተለይ የ1997 የምስራቅ አፍሪካ (ሴካፋ) ዋንጫን ያነሳንበትን ቀን ሁሌም በግብጠባቂነት ዘመኔ ትልቁ ስኬት ነው።
“በግብጠባቂነት ዘመኔ ማድረግ ሲገባኝ አላደረኩትም ብዬ ወደ ኋላ ሳስበው የሚቆጨኝ ነገር የአርጄንቲናው የዓለም ዋንጫ ላይ የነበሩ ስህተቶች አንዱ ነው። ቁጭ ብዬ የጨዋታውን እንቅስቃሴ ቂጭ ብዬ በቪዲዮ ስመለከት ማድረግ የምችለው ብዙ ነገሮች ነበሩ። ይሄን ባለማድረጌ የተፈጠሩ ስህተቶች በጣም ይቆጨኛል። ይሄም ቢሆን በእግር ኳስ ህይወቴ ከፍ ያለውን ቦታ የምሰጠው፣ ፍፁም የማልዘነጋው ሁሌም እንደ አዲስ የማስታውሰው ምርጥ የሆነውን ጊዜ ነው። ሌላው በ1994 ከሀገር ውጭ የሴካፋን ዋንጫን ይዞ በመጣው ብሔራዊ ቡድን ተይዤ
መጨረሻ ተቀንሼያለሁ፤ ያ ቡድን ግን ወደ
ሩዋንዳ ሄዶ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ከሀገር
ውጪ ዋንጫ አመጣ፤ ዋንጫ በማግኘታቸዉ
ከህዝቡ የተደረገላቸውን አቀባበል ሳይ በጣም
ተቆጨሁ፡፡ ምነው ባልቀነስና በዚህ ስብስብ
ውስጥና የዚህ ትልቅ ታሪክ አካል በሆንኩ ብዬ
በጣም ተቆጨሁ፤ ግን በ1997 በነበረው ስብስብ ውስጥ ተካትቼ የሴካፋን ዋንጫ በማግኘቴ ተደስቻለሁ፡፡
“እንደነበረኝ ጥረት በውጪ ሀገራት የመጫወት ትልቅ ህልም ነበረኝ። ይህንን ለማሳካት ደግም ትልቁ አጋጣሚ የአርጀንቲናው የዓለም የወጣቶች ዋንጫ ነበር። በወቅቱ ያለመብሰል ሆኖ የነበረውን ዕድል ሳንጠቀምበት ቀርተናል እንጂ እድሎች ነበሩ። በወቅቱ አጋጣሚውን ለመጠቀም ግንዛቤውም እውቀቱም አልነበረንም። ፌዴሬሽኑም በዚህ በኩል ያመቻቸልን የከፈተልን መንገድ አልነበረም። ሁላችንም ማለት በሚቻል መልኩ በውጪ ክለቦች መጫወት እንችል ነበር። ሆኖም በዚህ ክፍተት የተነሳ ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ ወደ አሜሪካ ከሄድኩ በኋላም አጋጣሚው ተመቻችቶልኝ ለተለያዩ ክለቦች ለመጫወት ሙከራ አድርጌ የነበረ ቢሆንም ከወረቀት እና አንዳንድ ጉዳዮች ጋር ተያይዞ ሳይሳካልኝ ቀርቷል።
“በሀገራችን ግብጠባቂ ግቡን መጠበቅ እንጂ ጎል ያስቆጥራል ተብሎ አይታሰብም። እኔ ግን ግብ እንዳይገባ ከመጠበቄ ባሻገር ሩዋንዳ ላይ በተካሄደው በአሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው በሚመራው ቡድን ውስጥ የሶማሊያ
ብሄራዊ ቡድን ላይ የጨዋታ ዘመኔ ብቸኛ የሆነች አንዲት ግብ በፍፁም ቅጣት ምት አስቆጥሬያለሁ።
“ብዙ መጫወት እየቻልኩ ነው ድንገት ኳስን አቁሜ ወደ አሜሪካ የሄድኩት። አሜሪካን ከሄድኩ በኋላ በዓመታዊ ውድድር ላይ ስጫወት የሚያዩኝ ሁሉ አሁንም ለምን ለክለብ አትጫወትም? ማቆም አልነበረብህም እያሉ ሲጠይቁኝ ያለ ጊዜዬ ማቆሜን አስባለው። ነገር ግን የእንጀራ ጉዳይ ሆኖ ለማቆም ተገደድኩ፡፡
“በተለያዩ ጊዜያት ለየት ያሉ ቅፅል ስሞች ወጥተውልኝ ነበር። በተለይ ጋሽ ሰውነት ቢሻው ያወጣልኝ “ጎመን” የምትለው መጠርያ አንዷ ናት ። ጋሽ ሰውነት ጎል ሲገባብኝ “ጎመን” ይለኛል። ተጨዋቾቹም ያንን ይዘው “ጎመን” አሉኝ ይጠሩኝ ጀመር።
“በእግርኳሱ ከነበሩኝ ገጠመኞች መካከል ቅዱስ ጊዮርጊስ እያለሁ ለጨዋታ ወደ አርባምንጭ ሄደን ስንመለስ በጣም የምንወድደው ሹፌራችን በየነ መጠነኛ የሆነ የሆድ ህመም ያጋጥመውና መኪናውን መንዳት ያቅተዋል፡፡ አጋጣሚው ሁሉም ያልጠበቀው ስለነበር ምን ልንሆን ነው ብለው
ብዙዎች ይደነግጣሉ። መንገድ ላይ ቆመን ልንቀር ነው እያሉ። በዚህን ጊዜ እኔ ብድግ ብዬ የሹፌሩ መቀመጫ ላይ ተቀመጥኩ። በዚህ ሰዓት ብዙዎቹ ደነገጡ፣ ፈሩ መኪናውን እስከማስነሳው ማንም አላመነም ነበር፡፡ መጨረሻ ላይ ዘና አድርጌ እየነዳው አዲስ አበባ አደረስኳቸው፡፡ ያው በልጅነቴ ከአባቴ ጋር ጋራዥ ስላደግኩ ከባድ መኪና አሸከረክር ስለነበር ብዙም አልተቸገርኩም፡፡ ይህ በእግርኳስ ህይወቴ ካጋጠሙኝ ገጠመኞች አንዱ ነው።
“በአሁኑ ወቅት በሀገራችን የግብጠባቂዎች ችግር አለ። ይሄም የሆነው የሀገራችን ክለቦች በኢትዮጵያውያን ግብጠባቂዎች ላይ ብዙ ትኩረት አለማድረጋቸው ነው። ብዙውን ጊዜ በውጭ ሀገር ግብጠባቂዎች ላይ ነው ትኩረታቸው። ይሄን ነገር በተለያዩ ጊዜአት እናገረዋለው፤ አስተያየትም ሰጥቼበታለው። ለኛ ሀገር ግብጠባቂዎች ቅድሚያ የሚሰጥበት እና ሌሎች ህጎች የሚፈጠሩበት ዕድል መመቻቸት አለበት። በዚህ ሁኔታ ከቀጠለ ብሔራዊ ቡድናችን በጣም ነው የሚቸገረው። ስለዚህ ክለቦች ብዙ መስራት አለባቸው። ከዚህም አልፎ ፌዴሬሽኑ ይሄን ማሰብ አለበት። በአንድ ወቅት በጣም የማደንቀው ግብጠባቂ ደሳለኝ ገብረጊዮርጊስ የሰጠው አንድ አስተያየት አለ ‘በእግርኳሱ ያነሱ ሀገሮች ለምሳሌ የመን ለውጭ ሀገር ግብጠባቂዎች እድል አይሰጡም። ቅድሚያ ላገራቸው ነው።’ ያለውን እኔም በዚህ ሀሳብ ነው የምስማማው። የሀገር ግብጠባቂዎች ጥሩ እስኪመጡ ድረስ ጊዜ ያስፈልጋቸዋል። ወይም ዕድሉ ሊሰጣቸው ይገባል። ከእኛ ሀገር በረኞች የማይሻሉ መጥተው እድሉ ሲሰጣቸው የእኛን መንገፍ ተገቢ አይደለም። ብዙ መሠራት ያለበት ጉዳይ ነው።
“ጅማ ከተማ እግርኳስ አሁን ያለበት ሁኔታ በጣም ያሳስበኛል። ጅማ አባ ጅፋር እና አባቡና የሁለቱ ክለቦች አመራሮች የሚያምኑት ወይም ትኩረታቸውን ያደረጉት ተጫዋች ግዢ ላይ ነው። ይሄንን ጅማ በነበርኩበት ጊዜ ተናግሬዋለው። ከታች እንደ ተስፋ ቡድን አይነት የተሰራ ነገር የለም። ሁሉም ተጫዋች በመግዛት እና አንዳንድ ነገር ነው የሚያደርጉት በዚህ ሁኔታ እግርኳሱ ሊያድግ አይችልም። እኔ ማስተላለፍ የምፈልገው ነገር ከታች የተስፋ ቡድን በማቋቋም ታዳጊ ላይ ቢሰሩበት በጣም ጥሩ ነው። አካባቢው ላይ በጣም አቅም ያላቸው ታዳጊዎች አሉ። እነዚህን መጠቀም ያስፈልጋል። ታዳጊዎችም ይህን እድል ለመጠቀም ጠንክረው መስራት አለባቸው።
“አሁን ላሉት የሀገራችን ግብጠባቂዎች ከልምዴ ማስተላለፍ የምፈልገው። ግብጠባቂነት ጥረትን ይፈልጋል። ብዙ መስራትን ይፈልጋል። እኔ በጣም ብዙ ጥረት አድርጌ ነው። ለፍቼ ነው እዚህ የደረስኩት። ስለዚህ አሁን ያሊ በረኞችም ብዙ መታገል፣ መልፋት አለባቸው እላለሁ።
” ወደፊት ሀገሬ መጥቶ በአሰልጣኝነት የመስራት እስካሁን ሀሳብ የለኝም። ወደ ፊት የሚሆነውን አብረን እናያለን። ሆኖም ግን ያለኝን ልምድ ሀገሬ መጥቼ የማካፈል መቼም ቢሆን የማልተወው ነገር ነው።”
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!
© ሶከር ኢትዮጵያ