የዘመናችን ከዋክብት ገፅ | ከአበባየው ዮሐንስ ጋር

ከ2011 ጀምሮ በሲዳማ ቡና እየተጫወተ የሚገኘው አማካዩ አበባየው ዮሐንስ የዛሬው የዘመናችን ከዋክብት አምድ ዕንግዳችን ሆኗል።

ትውልድ እና ዕድገቱ ሀዋሳ ባህል አዳራሽ (ቤርሙዳ) እየተባለ በሚጠራው ሠፈር ውስጥ ነው፡፡ ኳስን የጀመረው በሠፈር ውስጥ በግብ ጠባቂነት ነበር። በአንድ አጋጣሚ ተረፈ ፋንቱ ቄራ እየተባለ በሚጠራው ሜዳ ጨዋታ ኖሯቸው አሰልጣኙ በአማካይ ስፍራ ይጫወት የነበረ አንድ የቡድኑ አባል ለጨዋታው ባለመድረሱ ግብ ጠባቂ ሊሆን የሄደውን ታዳጊ ወደ መሐል ስፍራ አምጥቶ አጫወተው። ኳስን ለመጫወት ከትውልድ ቀዬው ሲነሳ ግብ ጠባቂ የነበረው አበባየሁም ከዛች ዕለት ጀምሮ የመሐል ሜዳ ተጫዋች በመሆን ቀጠለ፡፡

የታዳጊነት ጊዜውን በአሰልጣኝ ይልማ ገለታ ወይንም ኢንስትራክተር ተገኝወርቅ ፕሮጀክት ውስጥ ከተማሪነቱ ጎን ለጎን ሲሰለጥን ቢቆይም አሰልጣኙ በሞት በመለየታቸው ቡድኑን ለቆ ለጥቂት ጊዜ በአሰልጣኝ እታትሽ በመቀጠልም በቀድሞው የኒያላ አሰልጣኝ መለሰ ከበደ እና የሀዋሳ የሴቶች ቡድን አሰልጣኝ ዮሴፍ ገብረወልድ ፕሮጀክቶች ውስጥ በተከታታይ ዓመታት የልጅነት ጊዜውን አሳልፏል፡፡ በመቀጠል 2004 ላይ በአሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ አማካኝነት ደቡብ ፖሊስን በመቀላቀል ከክለብ እግር ኳስ ጋር ተዋወቀ። ራሱን እያሻሻለ በመምጣትም ለስልጤ ወራቤ እና ቡታጅራ ከተማ የተጫወተ ሲሆን ወደ ኢትዮጵያ ቡና ለመጠቃለል ከጫፍ ደርሶ ዝውውሩ በመሰናከሉ በ2008 በአሰልጣኝ ግርማ ታደሰ ሀዲያ ሆሳዕና ከተጫወተ በኋላ በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት በድጋሚ ለስልጤ ወራቤ እና ደቡብ ፖሊስን አገልግሎ ከ2011 ጀምሮ በሲዳማ ቡና መለያ እየተመለከትነው እንገኛለን። በተለይ ዘንድሮ ሊጉ እስከተሰረዘበት ጊዜ ድረስ ለሲዳማ ቡና የአማካይ ክፍል አስደናቂ ብቃቱን እያሳየ ይገኝ የነበረውን ይህን አማካይ ከአዝናኝ ጥያቄዎች ጋር ይዘንላችሁ ቀርበናል።

በኮሮና ሊጉ ከቆመ በኃላ ጊዜህን እንዴት እያሳለፍክ ነው ?

“ጊዜዬን እያሳለፍኩ የነበረው ልምምዶችን በመስራት ነው፡፡ ልምምዶችንም ስንሰራ ተራርቀን ነው፡፡ ፕሪምየር ሊጉም ከተቋረጠ ብዙ ጊዜ ሆኖታል። በእኔ በኩል ሰውነቴም እንዳይጨምር የተለያዩ ልምምዶች እየሰራሁ ነው። ከማህበረሰቡም ጋርም ሆነ ከቤተሰብ ጋር ባለው ግንኙነታችን እየተጠነቀቅን ነው።”

ውድድሩ የተቋረጠበት ጊዜ መራዘም አልከበደህም ?

“ከተቋረጠ አሁን ሰባት ወር ይሆናል። በፊት ቢሆን በዚህ ሰዓት ክለቦች ለቀጣይ ዓመት ልምምድ የሚጀምሩበት ነበር፡፡ አሁን ግን ይሄ በሽታ ከገባ በእኛ ሀገር አምስት ስድስት ወር ሆኖታል፡፡ በተጫዋቹም ሆነ በክለቡ ላይ ተፅዕኖ አለው። እንደ ሀገርም በፋይናንስ ሁሉም ክለብ በሚያስብል ደረጃ ተጎድቷል፡፡ አንዳንድ ክለቦች ደመወዝ መክፈል ችግር የሆነባቸውም ከኮቪድ ጋር በተያያዘ ነው፡፡ ተጫዋቹ እንደ ተጫዋች ብዙ ነገር ነው የሚጎዳው። አንደኛ ከልምምድ መውጣት አንድ ጉዳት ነው፡፡ ሁለተኛ የነበረበትን የአካል ብቃት ያጣበት ነው፡፡ አሁን ላይም ስፖርተኛው በግሉ ብቻ ነው ሊሰራ የሚችለው። ይሄ መሆኑ ደግሞ በእኛ ተጫዋቾች ላይም ሆነ በክለቦች ላይ በጣም ነው ጫና ያለው። ይሄ ዓለማችን ላይ የተከሰተ ስለሆነ አምነን ተቀብልነው እንጂ አዕምሮ ላይም ጉዳት አለው። ወድድር ላይ ሆነን ቢሆን ለተጫዋቾቹም ፣ ለክለቡም ፣ ለማህበረሰቡም የተሻለ ነበር ብዬ ነው የማስበው። በቀጣይ ቢጀመር እንኳን ተጫዋቹ በሥነ-ልቦና እና አካል ብቃት መውረድም ያመጣል፤ ብቻ ከባድ ነው፡፡”

እግርኳስ ተጫዋች ባትሆን ኖሮ ምን ሙያ ላይ ትገኝ ነበር ?

“ኦ…(እየሳቀ) ይሄ ከባድ ጥያቄ ነው፡፡ ግን ያው አላውቅም (በመገረም) እንደዚህ ነው ብዬ ልገምት አልችልም ። እሱ ፈጣሪ የፈቀደውን ነው የሆንኩት። ከዛ በፊት የተለየ ሀሳብ አልነበረኝም ፤ እንደዚህም የምለው የለኝም፡፡ ”

አብሬው ሜዳ ላይ ብጣመር ደስ ይለኛል የምትለው ተጫዋች ?

“ስሙን በተደጋጋሚ አንስቼዋለሁ ፤ ሚካኤል ለማ ነው፡፡ ሀዋሳ ተወልዶ ያደገ ነው፡፡ በዚህ ዓመት መጀመሪያ ወልዋሎ ነበር። በሁለተኛው ዙር ወላይታ ድቻ ነው ያለው። በእግርኳስ ህይወቴ አብሮኝ ተጫውቷል፡፡ ደስ ባለኝ እና ደቡብ ፖሊስን ወደ ፕሪምየር ሊጉ ባስገባንበት ዓመት አብረን ተጣምረን ተጫውተናል፡፡ እኔ እና እሱ ሜዳ ላይ ተነጋግረን እንኳን አናውቅም። ኳሱ ነው አግባብቶን ስንጫወት የነበረው። በድጋሚ አብሬው ብጫወት ዕድለኛ ነኝ ብዬ ነው የማስበው። ክለቦችም እሱ ላይ ያላቸውን እይታ የተሻለ ቢያደርጉ ከእርሱ ብዙ ነገርን ያገኛሉ ብዬ አምናለሁ። ”

በተቃራኒው ሆኖ ስትገጥመው የከበደህ ተጫዋች ?

“እንደዚህ ብዬ የማስበው ተጫዋች ባይኖርም ሜዳ ላይ ብዙ ጊዜ ስገባ ያሉትን ተጫዋቾች ለማሸነፍ እና ለመብለጥ ነው የምገባው። ከብዶኛል ብዬ የማስበው ተጫዋች የለም።”

ቤተሰብ መስርተሀል፤ ትዳር እንዴት ነው ?

“ትዳር አሪፍ ነገር ነው። በዚህ ሰዓት ሁሉም ሰው ቢኖረው ብዬ ነው የማስበው ነገር ነው ፤ የሰው አመለካከት ቢለያይም፡፡ ብዙ ሰው በሚሰማው ወሬ ይፈራል፡፡ ግን በዚህ ሙያ ውስጥ ላሉ ተጫዋቾች ጥሩ አነቃቂ ነገር ነው ብዬ ነው የማስበው። ብዙ ጊዜ በተጫዋችነት ህይወት ውስጥ ስትሆን ቤት ውስጥ አብሮ የመገናኘት ነገርህ በጣም አናሳ ነው፡፡ ሁሌም ትኩረት የምታደርገው በስራህ ላይ ነው፡፡ ልጆች ወልደህ ከሆነ ደግሞ ኃላፊነቱ የሚሆነው የባለቤትህ ነው፡፡ ባለቤትህም የምትሰራውን ስራ ትረዳኅለች። ደግሞም ኃላፊነትም ስለሚኖርብህ ትዳር ይበልጥ ጠንክረህ እንድትሰራ ያደርግሀል።”

በእግርኳሱ የተለየ ስሜት የሚሰጥህ የተደሰትክበት ጊዜ መቼ ነበር ?

“ደስተኛ የሆንኩበት ዓመት መጀመሪያ በኢትዮጵያ ቡና ጥሪ ሲደረገልኝ ነበር ፤ ማመን ሁሉ አቅቶኝ ነበር። ምክንያቱም 2005 ክረምት ደቡብ ፖሊስ ብሔራዊ ሊግ ነበርኩኝ። እና ብሔራዊ ሊግ ሆኜ ደውለው ሲጠይቁኝ በጣም ደስ ያለኝ። አንደኛ ሁሉም ሰው ጊዮርጊስም ሆነ ቡና መግባት ይፈልጋል ፤ ትልልቅ ቡድኖችም ስለሆኑ። በመቀጠል ደግሞ 2010 ከደቡብ ፖሊስ ጋር ፕሪምየር ሊግ የገባንበት ዓመት በእግር ኳስ ህይወቴ በጣም ደስ የተሰኘሁበት ጊዜ ነበር።”

ያዘንክበት ወቅትስ ?

“ዐምና ከሲዳማ ቡና ጋር የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ያጣንበት ዓመት ያስቆጨኛል። ቻምፒዮን የመሆን ዕድሉ ከሁሉም ክለብ የእኛ ይሰፋ ነበር፡፡ በራሳችን እጅ ነው ዋንጫውን ያጣነው። የብቃት ፣ የጨዋታ እና የማሸነፍ ችግር የለብንም ነበር። ነገር ግን ጥቃቅን ስህተቶች መጨረሻ ላይ ዋጋ ያስከፈሉን። እስከ 30ኛው ሳምንት ድረስ ነው ፉክክሩ የሄደው ፤ በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ እንደዚህ ዓይነት ነገር አልተለመደም። የእኛም ደጋፊ በደንብ ወደ እኛ የመጣበት ዓመት ነበር። ዋንጫውን ባለማንሳታችን በጣም አዝኛለሁ።”

በፕሪምየር ሊጉ የመጀመሪያ ጎልህን ማን ላይ ነበር ያስቆጠርከው ?

“2008 ሀዲያ ሆሳዕና እያለሁ ሀዋሳ ሜዳ ሀዋሳ ከተማ ላይ ነበር የመጀመሪያ ጎሌ። 4-3 በተሸነፍንበት ጨዋታ እየተመራን አንድ ዕኩል የሆንነው እኔ በማስቆጠርኩት ግብ ነበር ፤ የተሻማ ኳስ በግንባር አግብቼ። ብንሸነፍም ለተመልካች በጣም ደስ የሚል ጨዋታ ነበር። ያኔ በማግባቴም ደስተኛ ነበርኩኝ፡፡”

አመጋገብ ላይ እንዴት ነህ ? ምን ዓይነት ምግብ ይመችሀል ?

“አሁን በዚህ ጊዜ ኪሎዬም እንደዳይጨምር ልምምዶችን እሰራለሁ። ከዛ በኃላ ፓስታ ፣ ሩዝ ፣ መኮሮኒ ዓይነት ገሮችን አዘወትራለሁ ፤

የተጠበቀ ሰውነት እንዲኖረኝ ስለምፈልግ። በክለብ ደረጃ የሚሰጠን ልምምድም ስለሌለ የግድ ኪሎዬን ስለምጠብቅ ያንን አዘወትራለሁ። በእርግጥ ምግብ አልመርጥም ውድድር ላይ ሆኜ ማንኛውንም ምግብ እጠቀማለሁ። እንደዚህ የምለው የምግብ ዓይነትም የለም፡፡”

ሰዎች ማወቅ ይኖርባቸዋል ብለህ የምታስበው የተለየ ባህሪ አለህ?

“የተለየ ባህሪ የለኝም። ከማንኛውም ሰው ጋር የመግባባት አቅሜ ከፍተኛ ነው፡፡ ተግባብቶ የመጫወት ፣ ከሰው ጋር የመግባባት ፣ ከትልቅ ከትንሹም ጋር የማሳለፍ ልምድ አለኝ።”

ቅፅል ስም አለህ ?

“ብዙ ጊዜ ‘ገንቦ’ ብለው ይጠሩኛል። ይሄን ስም ያወጣልኝ ደግሞ አሁን አብሮኝ የሚጫወተው ግብ ጠባቂው ፍቅሩ ወዴሳ ነው፡፡ በ2001 ከ15 ዓመት በታች የፕሮጀክት ውድድር ሀላባ ሄደን ነው ያወጣልኝ፡፡ በወቅቱ ምግብ አብረን ነበር የምንመገበው። እና ምግብ አዘን የሱ ምግብ ሲመጣ እኔ በላሁበት እና ያኔ ያኔ ‘አንተ ገንቦ’ በሚል ስሙን አወጣልኝ፡፡ ”

ከእግር ኳስ ተጫዋች ሚስጥሬን የማጋራው ጓደኛዬ የምትለው አለ ?

“የለኝም !”

እዚህ ለመድረስህ ምሳሌ የሆነህ ተጫዋች ?

“ቢኒያም አድማሱ ወይም ዓይናማው ይባላል። ደቡብ ፖሊስ በሚጫወት ሰዓት በደንብ አስታውሰዋለሁ። ሁለት ቁጥር መለያን ለብሶ በሚጫወት ሰዓት እሱን ለማየት ከትምህርት ቤት ሸውጄ እወጣ ነበር። በፕሮጀክት ስጫወት አማካይ ሆኜ ስለምጫወት እሱን ለማየት ሜዳ ገባለሁ። በዛን ሰዓት የነበረው ችሎታ ፣ ወኔ ፣ የሚያገባው ጎል ፣ ኳስ የሚያቀብልበት መንገድ ፣ መሀል ሜዳን በልጦ መጫወቱን ሳየው በጣም ደስ አለኝ። ዕድሉንም አግኝቼ አብሬው 2010 ላይ ተጫውቻለሁ። ያኔም ያለው ነገር አልወረደብኝም። ስብዕናውም አስገራሚ ነው። አሁንም ድረስ በጣም የምወደው እና የማከብረው ጓደኛዬ ነው፡፡”

ከእግርኳሱ ውጪ በምን ትዝናናለህ ?

“ከእግር ኳስ ውጪ ቲቪ በማየት እና ቤት ውስጥ ሙዚቃ በማዳመጥ አሳልፋለሁ፡፡ በይበልጥ ግን ስፖርቱ ነው የሚያዝናናኝ። በግሌም ልምምዶችን መስራት በጣም ነው የሚያዘዝናናኝ ፤ ይሄንንም ነው ማስቀጠል የምፈልገው፡፡”

በመጨረሻ ምስጋናህ ለነማን ይድረስልህ ?

“ከሁሉም በፊት እዚህ ያደረሰኝ አምላኬን ከምንም በላይ ማመስገን ፈልጋለሁ። ለወደፊትም እግዚአብሔር ከጎኔ ሄኖ እንዲረዳኝ ነው የምፈልገው፡፡ በመቀጠል በጨርቅ ኳስ ላሰለጠነኝ ተረፈ ፋንቱ ፣ ጥላሁን ፣ አሰልጣኝ ዮሴፍ ፣ ገብረወልድ (ወፍዬ) ፣ አሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ ፣ ለእኔ ትልቅ አክብሮት ያለው እና ትልቅ ተጫዋች እንደምሆን የሚነግረኝ የደቡብ ፖሊስ የግብ ጠባቂ አሰልጣኝ ጆንን ማመስገን እፈልጋለሁ። ለአሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉም ትልቅ ክብር አለኝ። ቤተሰቦቼን ፣ ባለቤቴን እና ጓደኛዬ ብቻ ሳይሆን ወንድሜም የሆነው ሰብስቤ ኃይለማርያም ወይም ማሜን ከልጅነቴ ጀምሮ ትጥቅ በመግዛት ጨዋታዬን እያየ ይመክረኝ ቆይቷል እና በጣም ማመስገን እፈልጋለሁ፡፡ ያልተጠራዋቸውም ካሉ ለሁሉም ዕድሜ እና ጤና ይስጥልኝ እላለሁ፡፡”

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ