የሴቶች ገፅ | ቆይታ ከእመቤት አዲሱ ጋር…

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በክለብ እና ብሔራዊ ቡድን ደረጃ ምርጥ ብቃቷን እያሳየች የምትገኘው እመቤት አዲሱ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር አጭር ቆይታ አድርጋለች።

በአርባምንጭ ከተማ ልዩ ስሙ ዳገት ሰፈር በሚባል ቦታ ላይ ተወልዳ ያደገችው እመቤት ለእግርኳስ ልዩ ፍቅር እንደነበራት ትናገራለች። የነበራትን ልዩ ፍቅር ለማስታገስም ፆታ ሳትመርጥ ኳስን እጅግ አዘውትራ ትጫወት ነበር። በተለይ በወላጅ እናቷ አበረታችነት መክሊቷን ፍለጋ ሜዳ ላይ መክረምን ያዘች። እርግጥ ወላጅ አባቷ በቀለም ትምህርቷ ገፍታ እንድትሄድ ቢሹም እመቤት ግን “እምቢኝ” ብላ ኳስን የሙጥኝ አለች።

እድሜዋን በሰፈር ውስጥ የእግርኳስ ጨዋታዎች የጀመረችው እመቤት የአስራዎቹን እድሜ ስትቀድ ግን አሰልጣኝ ስለሺ ሃይሉ በሚባል የፕሮጀክት ቡድን አሰልጣኝ እይታ ውስጥ ገባች። በአሰልጣኙ በሚመራው የከተማው የፕሮጀክት ቡድን ውስጥ ለ2 ዓመታት እድገትን ካሳየች በኋላ ደግሞ የከተማዋ የሴቶች ቡድን ሲመሰረት ጉዞዋን ወደእዛ አድርጋ ከተማዋን በፕሪምየር ሊግ ደረጃ መወከል ቀጠለች። በአርባምንጭ ከተማም ከ2005-2007 ዓ/ም ድረስ ጥሩ ግልጋሎት በአምበልነት ከሰጠች በኋላ መከላከያን ተቀላቀለች። በአሰልጣኝ ኑረዲን አዳም አማካኝነት መከላከያን የተቀላቀለችው ይህቺ አይደክሜ አማካይ በጦሩ ቤት ለ4 ዓመታት ያቅሟን ካበረከተች በኋላ እያገባደድን ባለነው ዓመት ወደ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አመራች። በኢትዮጵያ ንግድ ባንክም ሊጉ እስከተሰረዘበት ጊዜ ድረስ ከአሰልጣኝ ብርሃኑ ግዛው ጋር መልካም ጉዞን እያደረገች ትገኝ ነበር።

በ2008 በብሄራዊ ቡድን ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ ሃገሯን እንድትወክል በአሰልጣኝ አስራት አባተ አማካኝነት ከ17 ዓመት በታች ቡድን ውስጥ እንድትካተት የሆነችው ተጫዋቿ ከዛ የዓለም ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታ በኋላ ወዲያው ወደ ዋናው የኢትዮጵያ ሴቶች ብሄራዊ ቡድን ስብስብ ውስጥ እንድትካተት ሆች። በመቀጠልም በቋሚነት በብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝነት በሚሾሙ አሰልጣኞች ጥሪ እየቀረበላት ሃገሯን ወክላለች። ይህቺ አይደክሜ የአማካይ ተጫዋችም ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር በ”ዘመናችን ኮከቦች” ገፅ ጥሩ ቆይታ አድርጋለች።

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ በኮቪድ-19 ምክንያት ከተቋረጠ በኋላ እመቤት ጊዜዋን በምን እያሳለፈች ነው?

እንደ ስፖርተኛ ጊዜው ትንሽ ከባድ ነው። በተለይ አሰልጣኝ ከጎንህ ሳይኖር ልምምድ ለመስራት መጣር ትንሽ ፈታኝ ነው። ስላልተለመደ። አሁን ላይ የራሴን የአካል ብቃት መቆጣጠር ላይ ትኩረት አድርጌ ስራዎችን ስሰራ ነው ጊዜው የሚያልፈው። በዚህም በሳምንት አራት ጊዜ ልምምዶችን እሰራለሁ። ከዚህ ውጪ መፅሃፍ በማንበብ፣ ፊልም በማየት እንዲሁም ከረጅም ጊዜ በኋላ ያገኘሁትን የቤተሰብ ፍቅር በማጣጣም ጊዜዬን አሳልፋለሁ።

መጽሐፍት በማንበብ ጊዜዬን አሳልፋለሁ አልሽኝ። አንባቢ ነሽ? እስቲ እግረመንገድ አንድ መጽሐፍ ጋብዢን?

እውነት ለመናገር ጎበዝ አንባቢ አደለሁም። አልፎ አልፎ ነው የማነበው። በተለይ ኮቪድ-19 ከመጣ በኋላ ቤት ስለምውል መጽሐፍትን አነባለሁ። ግን አንድ መጽሐፍ ጠቁሚን ካልከኝ ‘ሌላ ሰው’ የሚለውን እመርጣለሁ።

የእግርኳስ አርዓያሽ…?

ኤደን ሽፈራው። ኤደን ምርጥ ተጫዋች ነች። እኔም ተጫዋቿን እንደ አርኣያ ነበር የማያት። ከውጪ ደግሞ የሰርጂዮ ቡስኬትን እንቅስቃሴ በጣም አስተውል ነበር። ምንም እንኳን ቡስኬትን በዐይን ባልመለከተውም በቴሌቪዥን በማየው እንቅስቃሴ ተጫዋቹን እንደ አርኣያ እወስደው ነበር። ከዚህ ውጪ ወይንሸት ፀጋዬንም በአካባቢዬ እየተመለከትኳት ስላደኩ እሷንም እንደ አርኣያ ሳይ ነበር።

በግልሽ ጥሩ ጊዜ ያሳለፍሽበት ዓመት መቼ ነው?

ስኬታማ ጊዜ ያሳለፍኩት መከላከያ እያለሁ ነው። በተለይ 2008 ለእኔ ልዩ ዓመት ነበር። እርግጥ ለእኔ ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ ለቡድኑም ዓመቱ ምርጥ ነበር። ጊዜው ለዋንጫ ጫፍ የደረስንበት ዓመት ነበር። ከዚህ መነሻነት 2008 ጥሩ ጊዜ ነበረኝ። ከዚህ በተጨማሪ ዘንድሮ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቤት ጥሩ ጊዜን እያሳለፍኩ ነበር።

እመቤት እግርኳስ ተጫዋች ባትሆን በምን ሙያ እናገኛት ነበር?

ነጋዴ ነዋ (እየሳቀች)። በአካባቢዬ የሚገኙ አብዛኛዎቹ ሰዎች ነጋዴ ስለሆኑ እኔም እነሱን የምከተል ይመስለኛል። ይህ ካለሆነ ደግሞ ሰዓሊ የምሆን ይመስለኛል። ስዕል አልፎ አልፎ እሞክራለሁ። ከዚህ መነሻነት ወደ ጥበቡ እገባ ይሆናል።

አብሬያት ተጣምሬ መጫወት እፈልጋለሁ የምትያት ተጫዋች ትኖር ይሆን?

ብዙ ናቸው። ግን አፍሪካ ዋንጫ ላይ የነበረው የቡድን ስብስብ ውስጥ ከነበሩ ተጫዋቾች ጋር ሁሌ ነበር መጫወት የምፈልገው። እንደ እድል ሆኖ ከግማሽ በላይ የሚሆኑትን አግኝቻቸዋለሁ። በተለይ ረዒማ፣ ቡርቱካን እና ሽታዬ ጋር መጫወት እፈልግ ነበር። ይህንንም አሳክቻለሁ። ከዚህ ውጪ ያመለጡኝ ቢኖሩም አብሬያቸው የተጫወትኳቸው ስለሚበዙ እፅናናለሁ።

በተቃራኒ ስትገጥሚያት የምትከብድሽ ተጫዋትስ አለች?

በፍፁም። እስካሁን ከገጠምኳቸው ቡድኖች ውስጥ የከበደችኝ ተጫዋች የለችም።

በእግርኳስ በጣም የተደሰትሽበት አጋጣሚ መቼ ነው?

መከላከያ እያለሁ ጥረትን ጎንደር ላይ ገጥመን ያሸነፍንበት ጨዋታ ልዩ ስሜት ይሰጠኛል። በተለይ እኔ እና ፍቅርተ ተናበን ፍቅርተ ጎል ያስቆጠረችበት ክስተት በጣም ታስደስተኛለች። ጎሉ ተቀርፆ ስላልተቀመጠ ነው እንጂ ምርጥ ጎል ነበር። ተከላካዮች ኳሱን እኔ እንደምመታው እያሰቡ ፍቅርተ ኳሱን መታ አስቆጠረችው። እርግጥ ጨዋታውን በሰፊ ጎል ብናሸንፍም እኔ እና ፍቅርተ ተናበን ያስቆጠርነው ጎል እስካሁን ዐይኔ ላይ አለ።

የተከፋሽበትስ ጊዜ ይኖር ይሆን?

አለ። በተለይ 2008 ዓ/ም ላይ የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድን ውስጥ እያለሁ በካሜሩን የተሸነፍንበት ጨዋታ ከአምሮዬ አይጠፋም። በግጥሚያው በደርሶመልስ ውጤት አቻ ተለያይተን አዲስ አበባ ላይ በፍፁም ቅጣት ምት ነው ወደ ቀጣይ ዙር ማለፍ ሳንችል የቀረነው። ደግሞ ካሜሩኖች ከእኛ ቀድመው ፍፁም ቅጣት ምት ስተው ነበር። ነገር ግን እኛ አጋጣሚውን መጠቀም ሳንችል ቀርተን ወደቅን። በጊዜው የቡድኑ አምበልም ስለነበርኩ በጣም ተሰምቶኝ ነበር። ያለቀስኩትን ለቅሶ እራሱ እስካሁን አልረሳውም።

እስቲ በእግርኳሱ ካጋጠሙሽ ገጠመኞች አንዱን አጫውቺን…?

በእግርኳስ ብዙ ገጠመኞች ይገጥሙሀል። ግን በወረዳ ደረጃ ስጫወት ያደረኩትን አንድ ነገር ላጫውትክ። ፕሮጀክት ከመግባቴ በፊት በወረዳ ደረጃ ተመርጬ ተጫውቻለሁ። እዚህ ቡድን ውስጥ እያለሁም አንድ ወሳኝ ጨዋታ ነበረብን። በጨዋታው ላይም ጎል አስቆጠርኩ። ጎሉን እንዳስቆጠርኩ ምንም ሳልፈራ ማሊያዬን አውልቄ ራቁቴን ደስታዬን መግለፅ ቀጠልኩ(እየሳቀች)። በጊዜው የአስራዎቹ አጋማሽ የእድሜ ክልል ልጅ ነበርኩ። ግን ደስታዬ የማረገውን እንዳላቅ አድርጎኝ ማሊያዬን አወለኩ።

እመቤት ምግብ ላይ እንዴት ናት? የምትወጂው እና የምትጠይው ምግብ?

እመቤት ምግብ ላይ ደህና ናት። በተለይ እንቁላል በጣም እወዳለሁ። በተቃራኒው ደግሞ ሩዝ አልወድም። እንደውም ስፖርተኛ ስለሆንኩ አሁን አሁን ትንሽ መመገብ ጀመርኩ እንጂ በፊት ጭራሽ አልወድም ነበር።

አርባምንጭ እያለሽ ከሽታዬ ሲሳይ ጋር በተያያዘ አንድ አጋጣሚ እንደነበረሽ ሰምቻለሁ። እስቲ አጋጣሚውን አስታሺኝ?

ቀድሜ እንደገለፅኩልክ 2004 ዓ/ም ላይ ለአፍሪካ ዋንጫ ላለፈው ቡድን ጥሩ ስሜት አለኝ። በጣም ነበር ስብስቡን የማደንቀው። በተለይ እነ ቡርቱካን፣ ሽታዬ እና ረዒማን በጣም እወዳቸው ነበር። የብሄራዊ ቡድኑ አብዛኛው ስብስብ ደግሞ በጊዜው በባንክ ቤት ነበር የሚገኘው። ከዛ 2005 ላይ እኔ አርባምንጭ እያለሁ ያ የምወዳቸው እና የማደንቃቸውን ተጫዋቾችን የያዘው የባንክ ቡድን እኛን ሊገጥም ሃዋሳ መጣ። ከዛ እንደ አጋጣሚ ከጨዋታው በፊት የባንክን አውቶብስ አየሁት። ከዛም ሳላመነታ ቀጥ ብዬ ወደ ባሱ ገባሁ። ስገባ ባስ ውስጥ ተጫዋቾቹ የሉም። ሹፌሩ ብቻውን ቁጭ ብሎ ነበር። ከዛ ሹፌሩን ሽታዬ የምትቀመጥበትን ቦታ ጠየኩት። እሱም ጉጉት የተቀላቀለበት ጥያቄዬን ተቀብሎ ቦታውን ጠቆመኝ። እኔም ሄጄ ቦታው ላይ በደስታ ተቀመጥኩ። ይህንን ያደረኩት ሽታዬን በጣም ስለማደንቃት ነው።

በመጨረሻ…?

ከምንም በላይ እዚህ እንድደርስ ያደረገኝ ፈጣሪን ማመስገን እፈልጋለሁ። በመቀጠል ወላጅ እናቴን። በሶስተኛ ደረጃ ለእግርኳስ ህይወቴ ጉልህ ድርሻ የነበረው አሰልጣኝ ስለሺ ሃይሉን አመሰግናለሁ። ከዚህ ውጪ በእግርኳስ ህይወቴ እድገት እንዳሳይ ለረዱኝ ሁሉ ትልቅ ክብር እና ምስጋና እንዳለኝ መግለፅ እፈልጋለሁ።

👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!


© ሶከር ኢትዮጵያ