በ2010 ለኢትዮጵያ ቡና ለመጫወት ፈርሞ አንድም ጨዋታ ሳይጫወት ክለቡን የለቀቀው አማካዩ ቦባን ዚሪንቱሳ ከደመወዝ ክፍያ ጋር በተያያዘ ለፊፋ ያቀረበው ክስ ተቀባይነት ማግኘቱን ተከትሎ ከክለቡ ጋር ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡
በ2010 ሁለተኛ ዙር ላይ ቡድኑን ተቀላቅሎ ከሦስት ወራት ቆይታ በኋላ የተሰናበተው ተጫዋቹ “ውል እያለኝ መሰናበቴ አግባብ አይደለም። ምላሽ ካላገኘሁ ጉዳዩን ወደ ፊፋ እወስደዋለሁ።” በማለት በወቅቱ ለሶከር ኢትዮጵያ መናገሩ ይታወሳል። የኢትዮጵያ ቡና የቦርድ ሰብሳቢ መቶ አለቃ ፍቃደ ማሞም በወቅቱ አቋሙ የወረደ ከመሆኑ በተጨማሪ በተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶት መሻሻል ባለመቻሉም ውሉን አፍርሰው ደሞዝ ከፍለው ማሰናበታቸውን ለድረ-ገፃችን ገልፀው ነበር።
በአሁኑ ወቅት ለታንዛኒያው ምቲባዋ ሹገርስ እየተጫወተ የሚገኘው ቦባን ጉዳዩን ወደ ፊፋ ወስዶ ሲሟገት ከቆየ በኃላ ለተጫዋቹ ተገቢው ክፍያ በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በኩል እንዲፈፀምለት፤ ያ ካልሆነ ግን በክለቡ ላይ የእግድ ውሳኔን እንደሚያስተላልፍ የሚገልፅ ደብዳቤ ከአንድ ሳምንት በፊት መላኩን ሶከር ኢትዮጵያ ያገኘችው መረጃ ይጠቁማል፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን እንደገለፁልን “አዎ ደብዳቤ ተልኳል፤ ፊፋ ይፈፀምለት ብሎ አዟል። ኢትዮጵያ ቡናን ጠይቀንም ለመክፈል ዝግጁ ነን በማለታቸው ለፊፋ ያሉትን ገልፀን መልስ ሰጥተናል።” በማለት ገልፀውልናል፡፡ ኢትዮጵያ ቡናም ለተጫዋቾቹ የተወሰነውን ክፍያ ለመፈፀም ከተጫዋቾቹ ጋር እንደተስማሙ ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል። በዚህም ከሁለት አመት በላይ የፈጀውም ጉዳይ ዕልባትን ያገኘ መስሏል፡፡
© ሶከር ኢትዮጵያ
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!