የተጨናገፈው የሰርክል ብሩዥ ዝውውር – የገብረመድኅን ኃይሌ ትውስታ

ባለፈው ሳምንት የአሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ ሦስት አይረሴ የተጫዋችነት ዘመን ትውስታዎችን ማቅረባችን ይታወሳል። ለዛሬ ደግሞ አጥቂው በአንድ ወቅት ወደ ቤልጅየሙ ክለብ ሰርክል ብሩዥ ሊያደርጉት የነበረውን ዝውውር እና ሒደቱ የከሸፈበት መንገድን በራሳቸው አንደበት እናቀርብላችኋለን።

” በእግርኳስ ሕይወቴ ከማልረሳቸው አጋጣሚዎች እና በጣም ከምቆጭባቸው ነገሮች አንዱ ይህ የሰርክል ብሩዥ ዝውውር ነው። ክለቡ የአቋም መለኪያ ጨዋታ ለማድረግ ወደ ኢትዮጵያ መጣና ሁለት ጨዋታዎች አደረገ። አንድ ከቅዱስ ጊዮርጊስ አንድ ደግሞ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጋር ነበር ያደረገው። በዛ ምክንያት ከክለቡ ጋር ሁለት ጨዋታዎች የማድረግ ዕድል አጋጠመኝ። በሁለቱም ጨዋታዎችም በጣም ጥሩ እንቅስቃሴ አድርጌ በሁለቱም ጨዋታዎች ግብ አስቆጠርኩ። ክለቡ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ሁለት ለሁለት ሲለያይ አንድ ግብ አስቆጠርኩ ጨዋታውም ሁለት አቻ ተጠናቀቀ። ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ጋር በነበረው ጨዋታም ቡድናችን አሸንፎ እኔም በድጋሚ ግብ አስቆጠርኩባቸው።

” ከጨዋታው በኃላ ክለቡ እንደፈለገኝ አመራሮቹ ነገሩኝ። እኔም ስለ ውጭ ዝውውር የማውቀው ነገር አልነበረም ወኪልም አልነበረም በዛ ሰዓት ከዛ ፌደሬሽኑን ጠይቁ አልኳቸው። ከዛ ተያይዘን ወደ ፌደሬሽን ሄድንና ነብሳቸው ይማርና የወቅቱ ከፌደሬሽኑ ምክትል ፕሬዝዳንት ስለ ዝውውሩ ስንጠይቃቸው እንደዛ የሚባል ነገር እንደማይፈቀድ ገልፀው አምባረቁብን፤ ምንም አወንታዊ ምላሽ ሳይመልሱልንም ከፅህፈት ቤቱ በር መለሱን።

” ክለቡ በሁለቱም ጨዋታዎች ባሳየሁት ብቃት ስለተማረከ ሌሎች መንገዶች ቢያፈላልግም ነገሩ ሊሳካ አልቻለም፤ እኔም የጓጓሁለት ዝውውር ስላልተሳካ በጣም አዘንኩ። በዛ ሰዓት ክለቡ የትላልቅ ተጫዋቾች ማረፍያ ነበር። ዛምቢዊያው ታላቅ ተጫዋች ካሉሽያ ቡዋልያም በክለቡ ውስጥ ነበር። በዛ በዛ ምክንያት ዝውውሩ አጓጉቶኝ ነበር፤ ግን አጋጣሚ ሆኖ አልተሳካም። ዝውውሩ ቢሳካ ኖሮ ግን በቤልጅየም ፕሮ ሊግ ከትላልቅ ተጫዋቾች ጋር የመጫወት ዕድል ይገጥመኝ ነበር።”

© ሶከር ኢትዮጵያ


👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም

👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ

👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!