በዛሬው ይህን ያውቁ ኖሯል? አምዳችን የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 9ኛ ክፍል ጥንቅራችን አሰልጣኞችን የተመለከቱ እውነታዎችን ይዘን ቀርበናል።
– ከ2005 እስከ 2008 ድረስ በተደረጉ 4 ተከታታይ የውድድር ዓመታት የሊጉን ዋንጫ ያነሱ ክለቦች በአንድ አሰልጣኝ ብቻ እየሰለጠኑ አይደለም። እርግጥ 2004 ላይ ዋንጫውን ያገኘው ቅዱስ ጊዮርጊስ በዓመቱ 2 አሰልጣኞችን ቢቀጥርም ዓመቱን የጀመሩት ዱሳን ኮንዲች ሊጉ ሳይጀመር ነበር ከመንበራቸው እንዲነሱ የተደረገው። ከ2004 የውድድር ዓመት በመቀጠል በነበሩት 4 ተከታታይ ዓመታት ግን ደደቢት (2005) እንዲሁም ቅዱስ ጊዮርጊስ (2006፣ 2007 እና 2008) ከአንድ በላይ አሰልጣኞችን በዓመቱ ተጠቅመው ነው ዋንጫ ያገኙት።
– በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ በምክትልነት የሰሩ የውጪ ዜጎች ሁለት ናቸው። በ2003 ዳኒሎ ፔርሉጂ በቅዱስ ጊዮርጊስ የጁሴፔ ዶሴና ምክትል የነበሩ ሲሆን በዚሁ ዓመት ጋናዊው ሱሌይ መሐመድ በደደቢት የመህመት ታይፈን ምክትል ሆነው ሰርተዋል።
– በሊጉ ታሪክ ብቸኛ ሴት አሰልጣኝ መሠረት ማኒ ናት። አሰልጣኟ በ2008 ዓ/ም ድሬዳዋ ከተማን በዋና አሰልጣኝነት በመምራት ታሪክ ሰርታለች።
– አንድን ቡድን ለረጅም ዓመት የመሩ አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም ናቸው። አሰልጣኙ ሐረር ቢራን በ1998 አጋማሽ ተረክበው እስከ 2004 ድረስ ለ7 የውድድር ዓመታት መርተዋል።
– በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ22 ዓመታት ቆይታ 20 የውጪ ዜጋ አሰልጣኞች በሊጉ ቢያንስ አንድ ጨዋታ መርተዋል። እነርሱም ጁሴፔ ፔትሬሊ፣ ጁሴፔ ዶሴና፣ ዳኔሎ ፔርሉጂ (ጣሊያን)፣ ሃንስ ቫንደር ፕሊዩም፣ ማርት ኑይ፣ ሬኔ ፌለር፣ ማርቲን ኩፕማን (ሆላንድ)፣ ሚቾ፣ ፖፓዲች፣ ኒቦሳ ቪሴቪች፣ ኮስታዲን ፓፒች፣ ሰርዳን ዝቪጅኖቭ (ሰርቢያ)፣ ኬን ሞርተን፣ ስትዋርት ሃል (ብሪታኒያ)፣ ቫስ ፒንቶ (ፖርቹጋል)፣ ፋህረዲን ዚንኮይቪች (ቦስኒያ)፣ ሜህመት ታይፈን (ቱርክ)፣ ሚኬል ክሩገር (ጀርመን)፣ ኔይደር ዶሳንቶስ (ብራዚል) እና ዮርዳን ስቶይኮቭ (ቡልጋሪያ) ናቸው። ከእነዚህ 20 አሰልጣኞች በተጨማሪ ጆሴ ፌሬራ ፒንቶ እና ዱሳን ኮንዲች በሊጉ እንዲያሰለጥኑ ቢቀጠሩም ሊጉ ሳይጀመር ተሰናብተው ስለነበረ ዝርዝር ውስጥ መግባት አልቻሉም።
– በርካታ አሰልጣኞች የታዩበት የውድድር ዓመት 2000 ነው። 25 ክለቦች በተሳተፉበት የሚሌኒየሙ ውድድር 37 አሰልጣኞች ከሙሉ (24 ጨዋታ) እስከ 1 ጨዋታ ድረስ መርተዋል።
– በሊጉ ታሪክ ከአንድ ክለብ ጋር ከወረደ በኋላ ቡድኑን መልሶ ወደ ፕሪምየር ሊግ ያሳደገ አሰልጣኝ የለም።
– በአንድ ዓመት በርካታ አሰልጣኝ የቀየረ ቡድን አዳማ ከተማ ነው። ክለቡ በ2004 በሲሳይ አብርሀም ጀምሮ ፣ መስፍን ጌታቸው (ጊዜያዊ) እና ወንድማገኝ ከበደን ከቀጠረ በኋላ ሲሳይ አብርሀምን በድጋሚ በመቅጠር ዓመቱን ጨርሷል።
– በርካታ ጊዜ ክለቦችን ወደ ፕሪምየር ሊግ ያሳደጉ አሰልጣኞች ሦስት ናቸው። ተስፋዬ ገብሩ ፐልፕ (1989) ሙገር (1990) እና አዳማ (1991)፣ ደረጄ በላይ ሰበታ ከተማ (2000)፣ ጅማ አባ ቡና (2008)፣ ወልቂጤ (2011) እና ግርማ ታደሰ ሆሳዕና (2007 እና 2011)፣ ደቡብ ፖሊስ (2010) ናቸው።
– በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ከ10 የተለያዩ ሀገራት ዓለማት የመጡ የውጪ ሃገር አሰልጣኞች ክለብ ይዘዋል። ከእነርሱ ውስጥም ሰርቢያ ከኢትዮጵያዊያን በመቀጠል በአሰልጣኞቿ አማካኝነት በሊጉ ብዙ ዋንጫዎችን ያስገኘች ሃገር ነች። በዚህም ሰርቢያ 5 ጊዜ (በሚቾ)፣ ሆላንድ 3 ጊዜ (ሬኒ ፌለር፣ ማርት ኑይ*2) እንዲሁም ጣሊያን 1 ጊዜ (በዳኔሎ ፔርሉጂ) ዋንጫዎችን በሊጉ አስገኝተው በቅደም ተከተል ተቀምጠዋል።
© ሶከር ኢትዮጵያ
👉እጅዎን በተደጋጋሚ በሳሙና በአግባቡ በመታጠብ አልያም አልኮል እና ሳኒታይዘር በመጠቀም
👉ከሰዎች ጋር ንክኪ በማስወገድ
👉ከአላስፈላጊ እንቅስቃሴ በመገደብ፣ አካላዊ ርቀት በመጠበቅ እና በቤት በመቆየት ራሳችንን ከኮሮና ቫይረስ እንጠብቅ!